አራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሪዎች በፀጥታ አካላት ጫና እና ዛቻ መሰደዳቸው ተነገረ

ስደት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሪዎች በመንግሥት የፀጥታ አካላት በደረሰባቸው ዛቻ እና ወከባ ምክንያት ከአገር መሰደዳቸውን ተነገረ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ባወጣው መግለጫ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሪዎች በፀጥታ ኃይሎች “ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ እና ወከባ” እየደደረሰባቸው እንደሆነ አስታውቋል።

በዚህም ሳቢያ በአገሪቱ ያለው የሲቪል ምኅዳር ሊጠብ እና አደጋ ላይ ሊወድቅ እንሚችል ምክልቶች እየተስተዋሉ ነው አለ።

በአካል እና በስልክ ይደርሳል የተባለውን ማስፈራሪያ እና ወከባ በመስጋት አራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሪዎች አገር ጥለው መሰደዳቸውን ማዕከሉ በመግለጫ ላይ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ደረሱኝ ባላቸው አቤቱታዎች እና ጥቆማዎች ተሰደዱ የተባሉትን መሪዎች ስም ዝርዝር አውጥቷል።

የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል (ካርድ) መሥራች እና የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤደን ፍስሐ እና እሳቸውን የተኩት ወ/ት መሠረት አሊ እንዲሁም ከ30 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ በደረሰባቸው “ከፍተኛ ጫና፣ ወከባ እና ማስፈራሪያ” እንደተሰደዱ ገልጿል።

ከስድስት ዓመታት በፊት የተመሠረተው ማዕከሉ ከዚህም በተጨማሪ የኢሰመጉ ሠራተኞች በሚደርስባቸው ተመሳሳይ ዛቻ እና መስፈራሪያ ሥራቸውን ተረጋግተው ለመሥራት መቸገራቸውን ጠቁሞ፤ ሠራተኞቹ ሥራቸውን ለመልቀቅም እየተገደዱ ነው ብሏል።

ኢሰመጉ ከዚህ ቀደም ባወጣቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች ጫና፣ ድብደባ፣ ዝርፊያ እና ወከባ ሥራውን ለመሥራት እንቅፋት እየሆኑበት እንደሆነ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል መሻሻሎችን ሲጠብቅ እንደነበር ጠቁሞ ባለፈው ሳምንት በተቆጣጣሪው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የታገዱ ሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ጉዳይም አንስቷል።

የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል (ካርድ)፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ከፖለቲካ ገለልተኛ አልሆኑም በሚል ታግደዋል።

ድርጅቶቹ “ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን ሲገባቸው፣ ከዓላማቸው ውጪ በመንቀሳቀስ የአገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል” የሚል የእግድ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና መሪዎች ላይ የሚደርሱ ጫናዎች እና እገዳዎች “ምኅዳሩን የሚያጠብ፣ ፍራቻ የሚፈጥር እና ተሳትፎን የሚያኮስስ ነው” ሲል ኮንኗል።

እገዳው ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን የመደራጀት፣ የመሰብሰብ እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶችንም የሚጎዳ እንደሆነ ጠቁሟል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ከእገዳ በፊት ማስጠንቀቂያ መሰጠት እንዳለበት የሚደነግግ መሆኑንም ያነሳ ሲሆን፤ እርምጃው “ሕግን ያልተከተለ እና ግልጽነት የጎደለው” እንደሆነ አመልክቷል።

እግድ የተጣለባቸው ሦስቱም ድርጅቶች ባወጧቸው መግለጫዎች ምርመራ እንደተደረገባቸው የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረ ጠቁመው እግዱ ሕግ እና ሥርዓትን ያልተከተለ መሆኑንም አስታውቀዋል።

መንግሥት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና በአፋጣኝ እልባት እንዲሰጠውም ማዕከሉ አሳስቧል።

ከዚህ በተጫማሪም ማዕከሉ ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት ለሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ጥበቃ እንዲያደርጉ እና ለምኅዳሩ መስፋት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠይቋል።