ትግራይ በጦርነቱ ከ70 በላይ አትሌቶችን አጥታለች - የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በትግራይ ከሁለት ዓመታት በላይ በቆየው ደም አፋሳሽ ጦርነት ከ70 በላይ አትሌቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የክልሉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለቢቢሲ ተናገረ።
ከአትሌቶቹ በተጨማሪ አሠልጣኞች እና የስፖርት ኃላፊዎች መገደላቸውንም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኪዳነ ገብረ እግዚአብሔር ገልጸዋል።
“በትግራይ ከሚገኙ አሠልጣኞች፣ አትሌቶች እና የአትሌቲስ ማኅበራት ኃላፊዎች ሪፖርት ቀርቦልናል። የሟቾቹን የእያንዳንዱን ስም የያዘ ዝርዝርም ደርሶናል። አገራቸውን የወከሉ 76 አትሌቶች ተቀጥፈዋል። ሁለት አሠልጣኞች እና ሁለት የአትሌቲክስ ኃላፊዎች መገደላቸውንም መረጃ ደርሶናል” ሲሉ ተናግረዋል።
በጦርነቱ ሕይወታቸው ካለፈ አትሌቶች መካከል አብዛኞቹ በክልል፣ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳታፊ የነበሩ እንዲሁም ተስፋ የተጣለባቸው ወጣቶች ሲሆኑ፣ ከእነዚህም አንዷ ሳራ ጎይቶም አድዋ ውስጥ መገደሏን አስታውቀዋል።
በጦርነቱ ሕይወታቸው ካለፈው አትሌቶች በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ በነበሩ የስፖርት ተቋማት ላይ ውድመት መድረሱንም ላላፊው ተናግረዋል።
“በተቋም ደረጃ ሁሉም በሚባል ሁኔታ የትግራይ የስፖርት ማዕከላት ወድመዋል። ከእነዚህም መካከል 30 ሚሊዮን ብር ያህል የወጣበት የማይጨው አትሌቲክስ ማዕከል ይገኝበታል። ከባድ መሳሪያዎች ሕንጻውን አፈራርሰውታል” ብለዋል አቶ ኪዳነ።
አያይዘውም አትሌቶቹ በወታደሮች የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውንም አስረድተው አንዳንዶቹ “በትግራይ ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ ትግሉን ተቀላቅለው ሊሆን እንደሚችልም” ጠቁመዋል።
“በአጠቃላይ ጦርነቱ በአትሌቶቻችን ዋጋ አስከፍሎናል” ብለዋል።
በክልሉ በታጡ አትሌቶች፣ በወደሙ ስፖርታዊ ማዕከላት እና በአጠቃላይ በጦርነቱ ምክንያት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ሁኔታ መቀዛቀዙንም ገልጸዋል።
“ዛሬ አገራቸውን [ኢትዮጵያን] በዓለም አቀፍ ወድድር ወክለው የሚወደዳሩ የትግራይ ተወላጅ አትሌቶችን ብናይ ከጦርነቱ በፊት ከትግራይ የወጡ ናቸው። ትግራይ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለባቸው አትሌቶች ነበሯት። ከተወሰኑ ጊዜያት በፊት ጥሩ አትሌቶችን ለመልመል ውድድር አካሂደን ነበር ነገር ግን የምንፈልገውን ያህል ማግኘት አልቻልንም። ከፍተኛ አቅም የነበራቸውን አትሌቶች አጥተናል” ሲሉም ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድር በመሳተፍ በርካታ ሽልማቶችን ማግኘት ከቻሉ የትግራይ አትሌቶች መካከል ጉዳፍ ፀጋይ፣ ለተሰንበት ግደይ፣ ጎይተቶም ገብረሥላሴ፣ ሐጎስ ገብረ ሕይወት እና በሪሁ አረጋዊ ይገኙበታል።












