በመቀለ የሚገኘው ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ማቆሙ ተነገረ

የአይደር ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, AYDERE HOSPITAL

በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ የሚገኘው ዋነኛው ሪፈራል ሆስፒታል በገጠመው የግብዓት ችግር ምክንያት ለታካሚዎች ይሰጥ የነበረውን አግልግሎት ማቋረጡን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ተናገሩ።

ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በገጠመው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ እና በሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን አገልግሎት መስጠት ማቆሙን የሆስፒታሉ ቴክኒካል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ክብሮም ገብረሥላሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የእርዳታ አቅርቦቶችን ጨምሮ መሠረታዊ አቅርቦቶች በመቋረጣቸው ምክንያት በክልሉ ውስጥ በርካታ ሰዎች በምግብና በህክምና አቅርቦት እጦት ምክንያት ለችግር መጋለጣቸውን ዓለም አቀፍ ተቋማት መግለጻቸው ይታወቃል።

ከተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ በርካታ ህሙማንን ያስተናግድ የነበረው ሆስፒታሉ፤ የገጠመው ችግር ከአቅም በላይ በመሆኑ አገልግሎት ማቋረጡ ተነግሯል።

ሃያ ወራት ባስቆጠረው ጦርነት ውስጥ የህክምና መገልገያዎችና መሠረታዊ አቅርቦቶች ተቋርጠውበት የቆየው ዓይደር ሆስፒታል፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆኖ ህሙማንን ለማከም ሲጥር መቆየቱን የገለጹት ኃላፊው፣ አሁን ላይ ግን አገልግሎት መስጠት የማይችልበት ደረጃ መድረሱን ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ በመድኃኒት አቅርቦት እጦት እና በህክምና መሳሪያ ችግር ምክንያት የሚሰጠው አገልግሎት ሲቆራረጥ ቆይቷል የሚሉት ዶክተር ክብሮም “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ማደንዘዣ መድኃኒት ስለሌለ፣ ለድንገተኛ ታካሚዎች ብቻ ህክምና ስንሰጥ ቆይተናል” ብለዋል።

“አሁን ደግሞ የመብራት አገልግሎት ስለተቋረጠ ኦክስጅን አምርተው የሚሰጡን ተቋማት ሥራቸውን አቁመዋል። ሆስፒታሉ ሲሰጠው የነበረው የኦክስጅን አገልግሎት ከተበላሸ አንድ ዓመት አልፎበታል” ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር የነዳጅ አቅርቦት እንደሌለ የሚናገሩት ዶክተር ክብሮም፣ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ደሞዝ ከተከፈላቸው ረጅም ጊዜ በመሆኑ በሥራ ገበታቸው ላይ ለመገኘት እና ለታካሚዎች አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻሉ ገልጸዋል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድንና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር አብዛኞቹ የክልሉ ጤና ተቋማት በጦርነቱ ምክንያት መውደማቸው እና አገልግሎት መስጠት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

በአሁኑ ጊዜ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ከቀላል የድንገተኛ ህክምና ውጪ አግልግሎት እንደማይሰጥና በተለይ ቀናቸው ሳይደርስ ለሚወለዱ ህጻናት እርዳታ መስጠት እንደማይችል ዶክተር ክብሮም ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሆስፒታሉ ሐኪሞች ከአንድ ዓመት በላይ ደሞዝ ሳይከፈላቸው ሲሰሩ ቢቆዩም፣ አሁን ላይ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን መርዳት ባለመቻላቸው ከባድ ችግር ውስጥ ሆነ አስከ መለመን የደረሱ እንዳሉ ቢቢሲ ባለፈው ዘግቦ ነበር።

በመቀለ ዩኒቨርስቲ ስር የሚገኘው የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በመቀለና በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ 3600 ያህል ሠራተኞች እንዳሉት ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለበርካታ ወራት ወደ ትግራይ የሚገባው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ባለፈው መጋቢት የፌደራሉ መንግሥት የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የምግብና መሠረታዊ አቅርቦቶች ወደ ክልሉ መግባት መጀመራቸው ይታወሳል።