ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ ሰምጣ ሕጻናትን ጨምሮ 40 ሰዎች ሞቱ

የቱኒዚያ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የቱኒዚያ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች

ከቱኒዚያ የባሕር ዳርቻ ወጣ ብሎ ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ ሰምጣ ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 40 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ይህ ከአርባ በላይ ሰዎች የሞቱበት የባሕር ላይ አደጋ በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት ውስጥ በአካባቢው ከደረሱት እጅግ የከፉት መካከል መሆኑ ተነግሯል።

ጀልባዋ በማዕከላዊ ቱኒዚያ ግዛት ውስጥ በምትገኘው የሜዲትራኒያን ባሕር ወደብ ከሆነችው ማህዲያ ወጣ ብሎ ባለው የባሕሩ ክፍል ላይ በሰመጠችበት ጊዜ 70 የሚደርሱ ስደተኞችን ይዛ እንደነበር ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በሰመጠችው ጀልባ ላይ ተሳፍረው የነበሩት ሁሉም ሰዎች ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት የመጡ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ ቢጠቅሱም ዝርዝር ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።

ከሰሜን አፍሪካ የባሕር ዳርቻዎች በመነሳት ወደ አውሮፓው ለመሻገር ሲሞክሩ ከሚደርሱ ተደጋጋሚ አደጋዎች ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተከሰተቱት ይህ በርካታ ሰዎች የሞቱበት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ደርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በማዕከላዊ ሜዲትራኒያን ባሕር በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር በ2023 ከ210 ሺህ በላይ ሰዎች ሙከራ አድርገዋል።

ከእነዚህም መካከል ከ60 ሺህ የሚልቁት በባሕር ላይ ተይዘው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ሲደረጉ፣ ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ባሕር ላይ ሳሉ ሕይወታቸው አልፏል።

ረቡዕ ዕለት ተከስቶ ከአርባ በላይ ሰዎች ካለቁበት የስደተኞች ጀልባ መስመጥ አደጋ ውስጥ ወደ 30 የሚጠጉት በሕይወት ሊተርፉ ችለዋል።

አደጋውን ተከትሎ የቱኒዚያ ባለሥልጣናት ለበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት የሆነው የጀልባዋ መስመጥ አደጋ የደረሰበትን ምክንያት እና ሁኔታን ለማወቅ ምርመራ ጀምረዋል።

እየጨመረ የሄደውን ጦርነት እና ድህንትን በመሸሽ የተሻለ ሕይወት ፍልጋ አገራቸውን ጥለው በሚሰደዱ አፍሪካውያን ምክንያት ስደተኞችን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጫና ቱኒዚያ እየገጠማት ነው።

ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ በባሕር በኩል የሚደረገው የስደት ጉዞ በዓለም ላይ እጅግ አደገኛ ከሚባሉት መስመሮች መካከል አንዱ ነው።

ባለፈው ዓመት የካቲት ላይ ከቱኒዚያዋ ከተማ ስፋክ የባሕር ዳርቻ ወጣ ብሎ ከ40 በላይ ሱዳናውያንን ያሳፈረች ጀልባ ሰምጣ እንደነበር ይታወሳል።

በአውሮፓውያኑ 2023 የአውሮፓ ኅብረት ከአፍሪካ ተነስተው ወደ አህጉሪቱ የሚሻገሩትን መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞችን ለመቆጣጠር ከቱኒዚያ ጋር ስምምነት ተፈራርሞ ነበር።

ይህ ስምምነትም ስደተኞችን በድብቅ ወደ አውሮፓ እንዳይሻገሩ ለማድረግ፣ የድንበር ጥበቃን ለማጠናከር እና ወደመጡበት ለመመለስ 118 ሚሊዮን ዶላር ተካቶበት ነበር።