ከአፍሪካ ወደ ስፔን እየተጓዘ በነበረ የስደተኞች ጀልባ ላይ ልጅ ተወለደ

ሕጻኑና እናቱ እንዲሁም ስደተኞቹንም ጠባቂዎቹ በሕይወት ማትረፍ ችለዋል።

የፎቶው ባለመብት, SALVAMENTO MARITIMO/REUTERS

የምስሉ መግለጫ, ሕጻኑንና እናቱን እንዲሁም ሌሎቹንም ስደተኞቹን ጠባቂዎቹ በሕይወት ማትረፍ ችለዋል

ከአፍሪካ ወደ ስፔን እየተጓዘ በነበረና በስደተኞች በተጨናነቀ ጀልባ ላይ ልጅ መወለዱን የስፔን ባሕር ዳርቻ ጠባቂዎች ገለጹ።

ሕጻኑንና እናቱን እንዲሁም ሌሎቹንም ስደተኞቹን ጠባቂዎቹ በሕይወት ማትረፍ ችለዋል።

በስደተኞች የተጨናነቀው ጀልባ መጀመሪያ የታየው ከሦስት ቀናት በፊት ላንዛሮቴ ደሴት አካባቢ ነበር።

ልጁ እንደተወለደ ወደ ባሕር ዳርቻው መድረሳቸው ተገልጿል።

ስደተኞቹን ያዳናቸው ጀልባ ካፕቴን ዶሚንጎ ትሩጂሎ እንዳለው ነፍሰ ጡር ሴት ከስደተኞቹ አንዷ መሆኗን አውቀው ነበር።

"ከ15 ወይም 20 ደቂቃ በፊት የተወለደ ጨቅላ ስናይ ግን ተገረምን" ብሏል።

ጀልባው ጋር ሲደርሱ እናትየዋ በተጨናነቀው ጀልባ መሬት ላይ ተኝታ፣ ልጇን ሌላ ስደተኛ አቅፎት ነው ያገኟቸው።

እናትና ልጅ በላንዛሮቴ ወደሚገኝ ሆስፒታል በሄሊኮፕተር ተወስደዋል።

ጨቅላው ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበት ተገልጿል።

የሄሊኮፕተሩ ኮማንደር አልቬሮ ሴራኖ ፔሬዝ ለሮይተርስ እንደተናገረው በስፔን ሰባ ሰገል ኢየሱስ ክርስቶስን ከጎበኙነት በዓል ጋር በተያያዘ ለልጆች ስጦታ የሚሰጥበት በዓል የሚከበርበት ቀን ስለሆነ "ትልቅ ስጦታ" ደርሷቸዋል።

የስፔን ልጆች በበዓሉ ዋዜማ ጫማቸውን ጠርገው ያስቀምጡና በጫማቸው ውስጥ ስጦታ ይቀመጥላቸዋል።

ከአፍሪካ ወደ ስፔኗ ካናሪ ደሴት የሚደረገው ጉዞ አደገኛ ነው።

አምና ከ46,800 በላይ ሰነድ አልባ ስደተኞች በዚህ መንገድ አቋርጠዋል ሲል የስፔን መንግሥት ተናግሯል።