በቻይና ስለተከሰተው አዲስ ቫይረስ ምን እናውቃለን?

በቤጂንግ በመስፋፋት ላይ በሚገኘው ኤችኤምፒቪ ቫይረስ ምክንያት ብዙዎች ሆስፒታሎችን አጨናንቀዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በቻይና በሚገኙ ሆስፒታሎች ጭምብል ያጠለቁ በርካታ ሰዎች ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሠራጨቱ ሌላ ወረርሽኝ ተከስቶ ይሆን የሚል ስጋትን አስከትሏል።

ከጉንፋን ጋር የሚመሳሰለው 'ሂውማን ሜታኒሞቫይረስ' (ኤችኤምፒቪ) በተለይም በልጆች ላይ በስፋት መከሰቱን ቤይጂንግ አምናለች። የተከሰተውም ከወቅቶች መቀያየር ጋር ተያይዞ መሆኑንም ገልጻለች።

ኤችኤምፒቪ እንደ ኮቪድ-19 አይደለም ሲሉ የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ገልጸዋል። ቫይረሱ ለአስርት ዓመታት የነበረ መሆኑን በመጥቀስ ቫይረሱ ሁሉንም ልጆች በሚባል ደረጃ በተወለዱ በአምስተኛ ዓመታቸው እንደሚያጠቃ ተናግረዋል።

ቫይረሱ በአንዳንድ ህጻናት ልጆች እና የበሽታ መከላከል አቅማቸው በተዳከመ ሰዎች ላይ ከባድ ህመም ሊያስከትል ይችላል። ይህ አሁን አነጋጋሪ ስለሆነው ቫይረስ ልናውቅ የሚገቡን ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው።

ኤችኤምፒቪ ምንድን ነው? እንዴትስ ይተላለፋል?

ኤችኤምፒቪ በመለስተኛ ደረጃ የላይኛው የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ቫይረስ ነው። ለብዙ ሰዎች ከጉንፋን ብዙም አይለይም።

በአውሮፓውያኑ 2001 በኔዘርላንድስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ ሲሆን፣ ቫይረሱ በሰዎች መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት ሲኖር ወይም አንድ ሰው በቫይረሱ የተበከሉ ቦታዎችን ሲነካ ይተላለፋል።

በህመሙ ከተያዙ አብዛኞቹ ሰዎች ላይ ከሚታዩ ምልክቶች መካከል ሳል፣ ትኩሳት እና የአፍንጫ መታፈን ይጠቀሳሉ።

ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን ጨምሮ በዕድሜ የገፉ እና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ካንሰር ያለባቸው እንዲሁም የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከሙ ሰዎች ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን የተላላፊ በሽታዎች ሐኪሙ ህሱ ሊ ያንግ ገልጸዋል።

በዚህ ጊዜ "ብዙዎች የሆስፒታል እንክብካቤ ቢያስፈልጋቸውም በቫይረሱ የሚሞቱት ቁጥር አነስተኛ ነው" ብለዋል።

የቫይረሱ ሥርጭት ለምን በቻይና እየጨመረ መጣ?

እንደሌሎች የመተንፈሻ አካላት ህመሞች ሁሉ ኤችኤምፒቪ በክረምት ወራት እንደሚሠራጭ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ቫይረሱ ለሥርጭት የክረምት ወራት እንደሚመቸው እና ሰዎች ቤት ሲሆኑ የመተለላፍ ዕድሉ ስለሚጨምር መሆኑን አክለዋል።

በሰሜናዊ ቻይና የኤችኤምፒቪ ሥርጭት ከፍ ያለው እስከ መጋቢት ድረስ ይቆያል ተብሎ ከሚጠበቀው ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ጋር ይገናኛል።

በቻይና ብቻ ሳይወሰን በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ ያሉ ብዙ አገሮች የኤችኤምፒቪ ሥርጭት እያጋጠማቸው መሆኑን በአውስትራሊያው ፍሊንደርስ ዩኒቨርስቲ የበሽታ ሥርጭትን የሚከታተለው ክፍል ባልደረባ የሆኑት ጃክሊን ስቴፈንስ ተናግረዋል።

"ይህ አስጊ ቢሆንም ግን የሥርጭቱ መጨመር ምናልባትም በክረምት ወቅት በመደበኛነት የሚኖር ጭማሪ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

ከአሜሪካ እና ከዩናይትድ ኪንግደም የጤና ባለሥልጣናት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ እነዚህ አገራትም የኤችኤምፒቪ ሥርጭት ካለፈው ዓመት ጥቅምት ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እያጋጠማቸው ይገኛል።

ኤችኤምፒቪ እንደ ኮቪድ-19 ነው? ምን ያህልስ ሊያሳስበን ይገባል?

የኮቪድ-19 ዓይነት ወረርሽኝን መጠበቅ ከመጠን በላይ የተጋነነ ነው ይላሉ ባለሙያዎች። ወረርሽኞች በተለምዶ በአዳዲስ በሽታ አምጪ ተህዋስያን የሚከሰቱ ኤችኤምፒቪ ግን የተለመደ ነው።

ኤችኤምፒቪ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኝ እና ለአስርት ዓመታት ያህል ቆይቷል። ይህ ማለት በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ቀደም ሲል "በመጋለጣቸው ምክንያት በተወሰነ ደረጃ የበሽታው መከላከያ አላቸው" ብለዋል ዶክተር ህሱ።

"እያንዳንዱ ልጅ በሚባል ደረጃ አምስት ዓመት እስኪሞላው ቢያንስ አንድ ጊዜ በኤችኤምፒቪ ይጠቃል" ሲሉ በዩናይትድ ኪንግደም ኢስት አንግሊያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ሃንተር ተናግረዋል።

"ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ የሆነ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ስለመኖሩ ምልክቶች ያሉ አይመስለኝም።"

በተጨናነቁ ቦታዎች ጭንብል ማድረግ፤ በመተንፈሻ ቫይረስ ኢንፌክሽኖች ለከፋ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ ግለሰቦች ደግሞ ሰው ከሚበዛባቸው አካባቢዎች መራቅ፤ የእጅ ንጽህናን መጠበቅ እና የጉንፋን ክትባትን መውሰድ የመሳሰሉ መደበኛ ጥንቃቄዎች እንደሚመከሩ ዶክተር ህሱ አመልክተዋል።