የኡጋንዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ 'ከአገራቸው አታልለው ያመጧትን" ወጣት በዩኬ በባርነት በማሰራት ጥፋተኛ ተባሉ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም የኡጋንዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ከአገራቸው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም "አታልለው ያመጧትን" ወጣት በመኖሪያ ቤታቸው በባርነት እንድትሰራ በማስገደድ ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ።
ሊዲያ ሙጋምቤ የተሰኙት ዳኛ "ያላቸውን ስልጣን በመጠቀም" ወጣቷን ቋሚ ስራ እንዳትሰራ በመከልከል "በነጻ የቤት ሰራተኛዋ እንዲሁም ለልጇም እንክብካቤ እንድታደርግ" ማስገደዳቸውን አቃብያነ ህግ አስረድተዋል።
በኡጋንዳ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት የ49 ዓመቷ ሊዲያ የዩናይትድ ኪንግደም የኢሚግሬሽን ህግ እንዲጣስ በመመሳጠር፣ ለብዝበዛ በሚል ጉዞን በማመቻቸት፣ አንድን ሰው በግዳጅ ስራ ላይ በማሰማራት እንዲሁም ምስክሯን በማስፈራራት ሴራ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
የኦክስፎርድ ክራውን ፍርድ ቤት የእስር ቅጣቱን በሚቀጥለው ወር የሚበይን ይሆናል።
ዳኛዋ ቀደም ብሎ በዘመናዊ የባርነት ህግ መሰረት እንደሚከሰሱ አንድ ፖሊስ ሲነግራቸው በከፍተኛ ሁኔታ መደንገጣቸውን የቴምዝ ቫሊ ፖሊስ ይፋ ያደረገው ቪዲያ አሳይቷል።
ከዚያም ከፖሊሱ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ "በአገሬ ዳኛ ነኝ። ያለመከሰስ መብት (ኢሚዩኒቲ) አለኝ። ወንጀለኛ አይደለሁም" ሲሉም በቪዲዮው ላይ ይደመጣሉ።
ያለመከሰስ መብት እንዳላቸው በድጋሚ እንዲያረግጡ ሲጠየቁም ዳኛዋ "አዎ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት አለኝ" ሲሉ ለፖሊሱ ተናግረዋል። ተከሳሿ "እዚህ የመጣሁት በተማሪነት ነው። የሚሰራልኝ ሰው አያስፈልገኝም" ሲሉም በቪዲዮው ላይ ይሰማሉ።
"ከሷ [ከቤት ሰራተኛቸው] ጋር አልመጣሁም። ከዚህ ቀደም በቤቴ ስለሰራች ጠይቃኝ ነው የመጣችው" ብለዋል ዳኛዋ።
በችሎቱ ላይ ብይን ሲሰጥ በፍርድ ቤቱ የድንጋጤ ድምጽ የተሰማ ሲሆን ተከሳሿም በመታመማቸው ሰዎች ፍርድ ቤቱን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል።
አቃቤ ህግ ካሮላይን ሃውጊ ኬሲ "ሊዲያ ሙጋምቤ ግለሰቧን በዝብዛ በደል አድርሳባታለች። ተጎጂዋ በአግባቡ ተቀጥራ ክፍያ የምታገኝበትን መብቷን አለመረዳቷን በመጠቀም እንዲሁም ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የመጣችበትን አላማም አጭበርብራታለች" ሲሉ በችሎቱ ለተሰየሙት ዳኞች ተናግረዋል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በህግ የዶክትሬት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉት ዳኛ ከኡጋንዳ ምክትል ከፍተኛ ኮሚሽነር ጆን ሊዮናርድ ሙገርዋ ጋር በመመሳጠር ወጣቷ ወደ ዩኬ እንድትመጣ ማመቻቸታቸው ፍርድ ቤቱ ሰምቷል።
ጥንዶቹ ሐቀኝነት በጎደለው ልውውጥ ወጣቷ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንድትመጣ የኡጋንዳ ከፍተኛ ኮሚሽን ስፖንሰር አንዳደረጋት አቃብያነ ህሀጉ ገልጸዋል።
ዳኛዋ በተጨማሪም ተጎጂዋ ለአቃቤ ህግ ምስክር እንዳትሆን በማስፈራራት እንዲሁም የተከሰሱበት ክስ እንዲቋረጥ በማሴር ጥፋተኛ ተብለዋል።
ዳኛዋ ወጣቷን ኡጋንዳዊ የቤት ስራ እንድትሰራ አላስገደድኩም ሲሉ ያስተባበሉ ሲሆን፤ ሁልጊዜም "በፍቅር፣ እንክብካቤ እና በትዕግስት ነው የያዝኳት" ብለዋል።
ዳኛዋ ወደ ዩኬ እንድትመጣ አታለዋታል የተባለችው እና በህጋዊ ምክንያት ስሟ የማትጠቀሰው ወጣት ለፍርድ ቤቱ "ብቸኝነት እንዲሁም መውጫ እንዳጣች ይሰማት " እንደነበር ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች።












