በእሳት ከተያያዘው የአሜሪካው አውሮፕላን በክንፉ በኩል መንገደኞችን ማስወጣት ተቻለ

የአሜሪካ አየር መንገድ አውሮፕላኑ እሳት መያያዙን ተከትሎ ተሳፋሪዎች በክንፉ በኩል እንዲወጡ በማድረግ ከአደጋው እንዲያመልጡ ተደረገ።
በአደጋው ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም።
ተሳፋሪዎቹ በኮሎራዶ አየር ማረፊያ ማኮብኮቢያ ላይ እንዲቆዩ መደረጉም ተገልጿል።
አደጋውን ለመከላከል የተደረገውን ጥረት በሚያሳይ ቪዲዮ ላይ ተሳፋሪዎች በቦይንግ አውሮፕላኑ ክንፍ ላይ ቆመው፤ እሳት እየተቀጣጠለም የተወሰኑ ተጓዦች ቦርሳዎቻቸውን ይዘው ታይተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ አቪዬሽን ኤጀንሲ (ኤፍኤኤ) በዴንቨር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተሳፋሪዎች ከአውሮፕላኑ ለመውጣት በቀላሉ የሚዘረጉ መንሸራተቻዎችን መጠቀማቸውን ጠቅሶ፤ የችግሩን መንስኤ አጣራለሁ ብሏል።
የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰ ሪፖርት ቢደረግም አየር ማረፊያው 12 መንገደኞች ቀለል ባለ ጉዳት ሆስፒታል መወሰዳቸውን አክሏል።
አውሮፕላኑ ከኮሎራዶ ስፕሪንግስ ተነስቶ ቴክሳስ ወደሚገኘው ዳላስ ፎርት ዎርዝ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየተጓዘ ነበር ሲል ኤፍኤኤ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ሠራተኞቹ "የሞተር ንዝረት" መኖሩን ሪፖርት ካደረጉ በኋላ አውሮፕላኑ ሌሊት 7፡15 ሰዓት አካባቢ ወደ ዴንቨር አቅጣጫ መቀየሩን ኤፍኤኤ ተናግሯል።
አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ ወደ ማቆሚያው በሚያቀናበት ወቅት ማኮብኮቢያው ላይ ሲጓዝ በእሳት ተያይዟል።
የአሜሪካ አየር መንገድ በበኩሉ አውሮፕላኑ 172 መንገደኞች እና ስድስት የበረራ ሠራተኞችን አሳፍሮ እንደነበር እና ሁሉም በሰላም መውጣታቸውን ገልጿል።
አውሮፕላኑ የቦይንግ ስሪት 737-800 እንደሆነ እና "ከሞተር ጋር የተያያዘ ችግር" አጋጥሞታል ብሏል።
የአየር ማረፊያው ቃል አቀባይ ማይክል ኮኖፓሴክ እንዳሉት በአውሮፕላን ማረፊያው በሚገኙት የተለያዩ በሮች ጭስ እና ነበልባል ይታይ ነበር። እሳቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን እና በሌሎች በረራዎች ላይ መጓተት አለማስከተሉን ገልጸዋል።
አየር ማረፊያው ውስጥ ከነበሩት መካከል አንዳንዶች ጥቁር ጭስ አየሩን በሞላበት ወቅት የአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች ክንፉ ላይ በመውጣት ከእሳቱ ሲሸሹ የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ለቀዋል።
ምድር ላይ የነበሩ ሠራተኞች ወደ ክንፉ መሰላል ለማድረስ ሲጣደፉ ታይተዋል።
በአውሮፕላኑ የቀኝ ሞተር ስር ነበልባል በሚታይበት ወቅት አውሮፕላኑ የኋላ በር በኩል ተሳፋሪዎች እንዲወጡ መንሸራተቻዎች ተዘርግተው በአንድ ቪዲዮ ላይ ታይቷል።
ክስተቱ በሰሜን አሜሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ አደጋዎች የአቪዬሽን ደህንነት ላይ ስጋትን መፍጠራቸውን የተከተለ ነው።
የአሜሪካ አየር መንገድ አውሮፕላን ከአሜሪካ ጦር ብላክ ሃውክ ሄሊኮፕተር ጋር በዋሽንግተን ዲሲ በአየር ላይ በመጋጨቱ በደረሰ ከባድ አደጋ የ67 ሰዎች ህይወት አልፏል።
በዩናይትድ ስቴትስ መዲና የተከሰተው አደጋ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን እጥረት እና በሥራ ጫናዎቻቸው ጥያቄ አስነስቷል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የመንግስት ወጪ ቆጣቢ ጥረቶች አካል በማድረግ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኤፍኤኤኤ የሙከራ ጊዜ ሠራተኞችን ውል አቋርጧል።
ውሉ ተቋረጠው ከዋሽንግተን ዲሲ አደጋ ከሳምንታት በኋላ ነው።
ውላቸው ከተቋረጡ የኤፍኤኤ ሠራተኞች መካከል የጥገና መካኒኮች፣ የአካባቢ ጥበቃ ሠራተኞች እና የቴክኒክ ረዳቶች ይገኙበታል።












