በኔፓል የመንገደኞች አውሮፕላን ተከስክሶ ቢያንስ 40 ሰዎች ሞቱ

የአውሮፕላኑ አደጋ የደረሰበት ሥፍራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በማዕከላዊ ኔፓል ፖክሃራ አየር ማረፊያ አቅራቢያ 72 ሰዎችን አሳፍሮ ይበር የነበረ አውሮፕላን ተከስክሶ እስካሁን የ40 ሰዎች አስክሬን መገኘቱን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ንብረትነቱ የየቲ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላኑ ከመዲናዋ ካትማንዱ ወደ ቱሪስት ከተማዋ ፖክሃራ እየበረረ የነበረ ሲሆን ለማረፍ ሲሞክር ነበር የተከሰከሰው።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት አውሮፕላኑ በድንገት አቅጣጫውን ከመለወጡ በፊት በርካታ ሕዝብ በሚኖርበት አካባቢ ዝቅ ብሎ ሲበር ነበር።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ቢያንስ 15 የውጭ ዜጎችና አራት የበረራ ቡድን አባላትን ጨምሮ 68 መንገደኞች ተሳፍረው ነበር።

አደጋው የደረሰው ከአየር ማረፊያው 1.5 ኪሎ ሜትር በሚርቀው የሴቲ ወንዝ ሸለቆ ውስጥ ሲሆን 200 የሚሆኑ የኔፓል ወታደሮች የነፍስ አድን ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።

ከአደጋው ቦታ የወጡ ቪዲዮዎች ጥቁር የሚንቦለቦል ጭስ እና የተቃጠሉ የአውሮፕላን ስብርባሪዎችን አሳይተዋል።

የጦሩ ቃል አቀባይ፣ አውሮፕላኑ በመሰባበሩ “ተጨማሪ አስክሬኖችን ይገኛሉ ብለን እየጠበቅን ነው” ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

የኔፓል ጠቅላይ ሚኒስትር ፑሽባ ካማል ዳኻልም ካቢኔያቸውን ለአስቸኳይ ስብሰባ የጠሩ ሲሆን የመንግሥት ተቋማት በነፍስ አድን ሥራ ላይ እንዲሰማሩ አሳስበዋል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ከተሳፈሩት መንገደኞች መካከል 53ቱ ኔፓላውያን እንደሆኑ ተነግሯል። አምስት ሕንዳውያን፣ አራት ሩሲያውያን እና ሁለት ኮሪያውያን በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረው ነበር። ከአየር ላንድ፣ አውስትራሊያ፣ አርጀንቲና እና ፈረንሳይ የተሳፈሩ መንገደኞችም ይገኙበታል።

በኔፓል ወጣ ባሉ የማሽኮብኮቢያ ቦታዎች እና ድንገተኛ አየር ጠባይ ለውጥ ሳቢያ በተለያዩ ጊዜያት የአውሮፕላን አደጋ ተከስቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ ግንቦት 2022 የታራ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን በሰሜን ኔፓል አካባቢ ተከስክሶ የ22 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

በ2018ም እንዲሁ ከባንግላዲሽ ዲሃካ ሲበር የነበረ የዩኤስ-ባንግላ አውሮፕላን በካትማንዱ ለማረፍ ሲሞክር በእሳት ተያይዞ 51 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።