ቤተልሔም አትፊልድ ፡ ከኤቨረስት ተራራ ግርጌ የኢትዮጵያን ምግቦችና ሥነ ጽሑፍ የምታስተዋውቀው ኢትዮጵያዊት

የፎቶው ባለመብት, Bethelhem Attfield
ደቡብ እስያዊቷ አገር ኔፓል በሂማሊያ ተራራዎች የተከበበች ናት።
የምድራችን ትልቁ ተራራ ኤቨረስትም የሚገኘው ከቻይና ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ነው።
ኤቨረስት ከባህር ጠለል በላይ 8 ሺህ 849 ሜትር ከፍታ አለው። ይህንን በበረዶ ግግር የተሸፈነ ተራራ ለመውጣት በየዓመቱ በርካታ ተራራ ወጪዎች ወደ ኔፓል ይጎርፋሉ። ያኔ የኔፓል ዋና ከተማ ካትማንዱ በጎብኝዎች ትጨናነቃለች።
ካትማንዱ ከኤቨረስት የምትርቀው በ200 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው። የካትማንዱ ከባቢ ከጠራ ተራራውን በአሻጋሪ ማየትም ይቻላል።
ተራራውን ለመውጣት 5 ወርና ከዚያ በላይ ሊወስድ ይችላል። እንዲሁ ብድግ ብሎ መውጣት የማይታሰብ ነው። በተራራው ላይ በተወሰነ ርቀት በተሰሩ ካምፖች ማረፍን እና ሰውነትን ማለማመድ ይጠይቃል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ታልፎም በሰላም የሚመለሱት የታደሉ ናቸው። በኦክስጅን እጥረት፣ አጥንት ሰርስሮ በሚገባው ቅዝቃዜ፣ በበረዶ መንሸራተትና መሰንጠቅ አስክሬናቸውን እንኳን ለማንሳት በማይቻልበት ሁኔታ እዚያው የበረዶ ሲሳይ ሆነው የሚቀሩ ተራራ ወጪዎች ጥቂት አይደሉም።
በኔፓል በኩል ወጥተው በቻይና በኩል አስክሬናቸው የሚገኝም አሉ።
በኔፓል ተራራ በሽ በሽ ነው። በርካቶች ኤቨረስትን ለመውጣት ከመሞከራቸው በፊት በሌሎች የሂማሊያ ተራራዎች ልምምድ ማድረግን ይመርጣሉ። ይህም ቢሆን ግን ቀላል አይደለም።
ታዲያ ወይና ደጋማ የአየር ጠባይ ያላት ካትማንዱ ለእነዚህ ተራራ ወጪዎች እፎይታ ማግኛ ናት።
ጎብኝዎች ወደ ኤቨረስት ለመሄድ ካትማንዱን ከመሰናበታቸው በፊት በ'ቶፕ ኦፍ ዘ ዎርልድ ሬስቶራንት' በሚገኘው 'አዲስ ኢትዮጵያን ኩዚን' ተገኝተው የኢትዮጵያን ምግቦች ያጣጥማሉ። ሲመለሱም ቢሆን ማረፊያቸው ነው።
እዚህ ላይ የኢትዮጵያን በቅመም ያበደ ዶሮ ወጥ ከእነ ጤፍ እንጀራው ኤቨረስት ድረስ ማን ወሰደው ማለታችሁ አይቀርም።
እርሷ ቤተልሔም ባዩ ትባላለች።
ከሌላ ኢትዮጵያዊት ጓደኛዋ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ምግቦችን አዘጋጅታ የምታቀርበው እርሷ ናት። ዶሮ ወጥ፣ ሥጋ ወጥ፣ በየዓይነት አትክልቶች፣ አይብ ፣ ከመጠጡም ጠጅ ሳይቀር ለእንግዶች ታሰናዳለች።
"ጎብኝዎችም ሆኑ የአገሬው ሰው ምግባችንን ወድደው፣ አጣጥመው ነው የሚመገቡት" ትላለች።
ለመሆኑ ቤተልሔምን ከኤቨረስት ተራራ ግርጌ ምን እግር ጣላት ?
ቤተልሔም ኢትዮጵያዊት ናት። የተወለደችው፣ ያደገችው፣ የተማረችውም ኢትዮጵያ ነው።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ድግሪ አግኝታለች። በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅም አጫጭር ትምህርቶችን ወስዳለች። በአዲስ አበባ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አገልግላለች።
ወደ ኔፓል የወሰዳት የሕይወቷ ጉዞ የተጀመረውም በዚሁ ወቅት ነው።
አሁን የትዳር አጋሯ ከሆነው እንግሊዛዊ ጋር ተዋወቀች።
በዚህ መሃል ወደ እንግሊዝ አገር አቅንታ በሥርዓተ ጾታ ፣ ባህልና ማኅበረሰብ ሁለተኛ ድግሪዋን ሰራች። ከዚያም ኢትዮጵያ ሳሉ ከተዋወቀችው እንግሊዛዊ ጓደኛዋ ጋር በትዳር ተጣመሩ።
የባለቤቷ ሥራ ግን አንድ ቦታ ጎጆ ቀልሶ የሚያስኖር አልነበረም። በተለያየ ጊዜ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መዛወርን የሚጠይቅ ነበር።
ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌ፣ ቪየትናም፣ ካምቦዲያ፣ እንግሊዝ ኖረዋል። አሁን ደግሞ ኑሯቸውን ኔፓል አድርገዋል። ቤተልሔም አትፊልድ ከቤተሰቦቿ ጋር ኔፓል ከከተመች አራት ዓመት ገደማ ሆኗታል።
ታዲያ ቤተልሔም በሄደችበት ሁሉ ኢትዮጵያን አዝላ ነው።
"ጊዜው እየረዘመ፤ የምኖርበት አገር እየራቀ በሄደ ቁጥር ለአገሬ ያለኝ ፍቅር እያየለ ነው የሚሄደው" ትላለች።
በኖረችበት አገር ሁሉ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ ሥራዎችን መሥራትን ትመርጣለች።
ቪየትናም ሳለች ከቆዳ የሚሰሩ የሴቶች ቦርሳ ትሰራ ነበር። የቦርሳዎቹ ዲዛይን የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ የሚያስተዋውቁ ኢትዮጵያዊነት መሠረት ያላቸው ነበሩ።
በዚምባብዌ እና ታንዛኒያ ቆይታዋም የቆዳ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጋ ትሰራ ነበር።
የምትሰራቸው የበጎ ፈቃደኝነት ተግባራት፣ ጥናታዊ ጽሑፎችም ሆኑ ዲዛይኖች ከኢትዮጵያዊነት ጋር እንዲገናኙ ትፈልጋለች።
"ሁል ጊዜም የኢትዮጵያን ነገር የማስተዋወቅ ፍላጎት አለኝ፤ ደግሞም ብዙ መተዋወቅ ያለበት ስጦታ አለን" የምትለው ቤተልሔም አሁን በካትማንዱ የኢትዮጵያ ምግቦችን አዘጋጅታ ታቀርባለች።

የፎቶው ባለመብት, Bethelhem Attfield
የሄደችባቸውን አገራት ከኢትዮጵያ ጋር የማመሳሰልና የማወዳደር ልምድ ያላት ቤተልሔም " ሁሉም አገር ስሄድ ኢትዮጵያ የጎደላት ምንድን ነው? የሞላላትስ? " እያልኩ አሰላስላለሁ ትላለች።
ኔፓልም ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስላት ብዙ እንደሆነ ትናገራለች።
"ኔፓል ልክ እንደ ኢትዮጵያ የባህር በር የላትም። በትላልቅ ተራራዎች የተከበበች ናት። ሕዝቦቿ ቅኝ ተገዝተው አያውቁም። ኃይማኖተኛ ናቸው [የቡድሂዝምና ሂንዱ እምነትን ይከተላሉ]። የነገሥታት ዘርም አላቸው።
ትሁት ፣ በራሳቸው የሚኮሩ ሕዝቦች ናቸው፤ ሕዝቦቿ ልዩነት ቢኖራቸውም ተቻችለውና ተከባብረው ነው የሚኖሩት" ትላለች ቤተልሔም።
ኔፓሎች ከቅመማ ቅመም ጋር ያላቸው ቁርኝትም ከኢትዮጵያ ጋር ይመሳሰላል።
ኔፓል ውስጥ በእግር በፈረስ ተፈልጎ የማይገኘው ቅቤ ማንጠሪያ ኮሰረት ብቻ ነው ትላለች ቤተልሔም።
ኮሰረትና ጤፍ ኔፓል የሚደርሱት አገር አቆራርጠው ነው።
ቤተልሔም እንደምትለው እሷ በምትኖርበት ካትማንዱ የሚኖሩት ስምንት የኢትዮጵያ ቤተሰቦች ብቻ ናቸው። እርስ በእርሳቸው ይተዋወቃሉ። ቡናም ይጠራራሉ።
የኢትዮጵያን ምግቦች በሬስቶራንት ማቅረብ የፈለገችው ለአገሬው ሰው እና ለቱሪስቶች ለማስተዋወቅ በማለም ነው።
"ምግቡ ከኔፓሎች ምግብ ጋር ይመሳሰላል። የአገሬው ሰዎች ምግቡን ሲቀምሱት ይወዱታል" ትላለች ቤተልሔም። ደንበኞቿ ግን በአብዛኛው አሜሪካውያን ናቸው። በአገሪቷ የሚኖሩ ዲፕሎማቶችም ከጎብኝዎች በበለጠ ደንበኞቿ እንደሆኑ ትናገራለች።
ቤተልሔም ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ ከፍ ለማድረግ ትተጋለች።
"የኢትዮጵያን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በዓለም አቀፍ ቋንቋ ማስተዋወቅ እፈልጋለሁ"
ቤተልሔም አሁን ሦስተኛ ዲግሪዋን እየተከታተለች ነው። ጥናቷንም በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ነው።
"ኢትዮጵያ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ትሩፋቶች አሏት፤ ይሁን እንጂ በአፍሪካ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ስሟ ጎልቶ አይነሳም። ለዚህ ደግሞ የሚጻፍበት ቋንቋ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ተደራሽ እንዲሆን አለማስቻሉ ነው" ትላለች ቤተልሔም።
ምዕራብ አፍሪካውያን በፈረንሳይኛ፤ ሌሎች ደግሞ በእንግሊዝኛ ታሪካቸውን ፣ ባህላቸውን፣ የማኅበረሰብ ሥነ ልቦናቸውን በሥነ ጽሁፍ ያስተዋውቃሉ። የኢትዮጵያ ግን በአብዛኛው በአማርኛ ቋንቋ ስለሚጻፉ ድንበር የሚሻገሩት ጥቂቶች ናቸው።
በእርግጥ ቤተልሔም ታሪኮች እና ሌሎች የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በራስ ቋንቋ መጻፋቸው ላይ ተቃውሞ የላትም። ቢሆንም ግን በኢትዮጵያ የትርጉም ሥራ መስፋፋት አለበት የሚል አቋም አላት።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች፣ ወደ አፍሪካ የተለያዩ ቋንቋዎች እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች መተርጎም አለባቸው ትላለች።
ይህንን ሃሳቧን በተግባር ለማሳየትም መንገድ ጀምራለች።
የአዳም ረታ 'አለንጋ እና ምስር' መጽሐፍ ውስጥ 'የድንች መዋስዕት' የሚለውን ታሪክ 'Requiem for Potatoes' በሚል ተርጉማዋለች። ከደራሲው ፈቃድ ጠይቃ የሰራችው ይህ የትርጉም ሥራዋ በአማዞን ገበያ ላይ ይገኛል።
"የደራሲ ይስማዕከ ወርቁን ' ክቡር ድንጋይ' የሚለው መጽሐፍም ተርጉሜ በእንግሊዝ አገር እየታተመ ነው" ብላለች ቤተልሔም።
ከዚህም በተጨማሪ ከተለያዩ የአማርኛ መጽሐፍት ታሪኮችን እየቀነጨበች በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመተረክ በዩቲዩብ ታጋራለች።
በሥነ ጽሑፍ ረገድ የወደፊት ህልሟ የኢትዮጵያን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ወደ ሌሎች ቋንቋዎች በመተርጎም ለዓለም ሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እንደሆነም ተናግራለች።
















