ግሪሊሽ በመኖሪያ ቤቴ ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ እጅግ በጣም ስሜት የሚረብሽ ነው አለ

ጃክ ግሪሊሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጃክ ግሪሊሽ

የማንቸስተር ሲቲ የክንፍ መስመር ተጫዋች ጃክ ግሪሊሽ በመኖሪያ ቤቱ ላይ ዝርፊያ መፈጸሙ ስሜት የሚረብሽ እጅግ አስደንጋጭ ክስተት ነው አለ።

እንግሊዛዊው ተጫዋች ጃክ ግሪሊሽ መኖሪያ ቤቱ የተዘረፈው እርሱ በሊጉ ከክለቡ ማንቸስተር ሲቲ ጋር በሊቨርፑል ከተማ ከኤቨርተን እየተጋጠመ በነበረበት ወቅት ነው።

የማንቸስተር ሲቲ ፖሊስ ቼሻየር ወደሚገኘው የግሪሊሽ ቤት ያቀናው በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ረቡዕ ምሽት 3፡50 ገደማ ነበር።

እንደ ዘ ሰን ዘገባ ከሆነ ዘረፊዎች ከተጫዋቹ ቤት 1 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ያላቸው የእጅ ሰዓቶችና ሌሎች ጌጣጌጦችን ወስደዋል።

“ቤተሰቦቼ ለእኔ ከምንም በላይ ናቸው። የእነርሱን ደኅንነት ከማረጋገጥ በላይ ለእኔ ትልቅ ነገር የለም” ሲል የክንፍ ተጫዋቹ በኢንስታግራም ገጹ ላይ ጽፏል።

በመኖሪያ ቤቱ ላይ ዝርፊያው ሲፈጸም የግሪሊሽ አጋር ሳሻ አትውድ እና ሌሎች የቤተሰብ አባላት በቤት ውስጥ ነበሩ። የቤተሰብ አባላቱ የዘረፊዎችን ድምጽ ከሰሙ በኋላም ፖሊስ ወደ ስፍራው እንዲመጣ አድርገዋል።

ፖሊስ በውሻ እና በሄሊኮፕተር ታግዞ ዘራፊዎቹን ፍለጋ ቢሰማራም ፍለጋው ውጤታማ አልሆነም። እስካሁንም በዝርፊያው ተጠርጥሮ የተያዘ የለም።

“ምን ያክል ሰሜቴ እንደተረበሽ ማስረዳት አልችልም። ይህ ለሁላችንም እጅግ አስደንጋጭ ከስተት ነው” ያለው ግሪሊሽ ማንም ሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚመለከተው ገልጿል።

ተጫዋቹ ጨምሮም ባለፉት 12 ወራት በእግር ኳስ ሕይወቱ እጅግ ስኬታማ የሚባል ጊዜን ማሳለፉን ገልጾ በመኖሪያ ቤቱ ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ ግን በዚህ ስኬቱ እንዳይኮራ እንዳደረገው ጨምሮ ተናግሯል።

“እነዚህን አስቀያሚ ወንጀሎች የሚፈጸሙ ሰዎች በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያደርሱትን የጉዳት መጠን ጨርሶ አያውቁትም። እኛ ያለፍንበትን ሌላ ቤተሰብ እንዳያልፍ በቁጥጥር ስር ውለው በሕግ ይጠየቃሉ ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ” ብሏል።

የብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ግሪሊሽ ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ከተጫወተበት አስተን ቪላ ከሦስት ዓመታት በፊት በ100 ሚሊዮን ፓዎንድ ወደ ማን ሲቲ መዘዋወሩ ይታወሳል።

ተጫዋቹ በፕሪሚየር ሊጉ ከከፍተኛ ተከፋይ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆን፤ አንዳንድ ሪፖርቶች ተጫዋቹ በሳምንት 300ሺህ ፓዎንድ እንደሚከፈለው ያሳያሉ።