ታሊባን ከትዊተር ‘ሰማያዊ ጭረት’ መግዛት ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትዊተር የሰዎች ወይም ተቋሞች ትክክለኛ ማንነትን የሚለይበትን ‘ሰማያዊ ጭረት’ ታሊባን እየገዛ ነው።
የታሊባን አባላት ትዊተር ላይ ‘ሰማያዊ ጭረት’ (blue tick) እያገኙ እንደሆነም ተዘግቧል።
ይህ ሰማያዊ ጭረት “ታዋቂ እና በሕዝብ የሚፈለጉ” የትዊተር ተጠቃሚዎች የሚለዩበት አሠራር ሲሆን፣ በአዲሱ የትዊተር አወቃቀር መሠረት የትዊተር ተጠቃሚዎች ጭረቱን መግዛት ይችላሉ።
ቢያንስ ሁለት የታሊባን አባላት እና አፍጋኒስታን የሚገኙ የቡድኑ አራት ቀንደኛ ደጋፊዎች ጭረቱን እስካሁን አግኝተዋል።
የታሊባን “የመረጃ ተደራሽነት” ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሄዳያቶላህ ሄዳያት ሰማያዊ ጭረት ካላቸው መካከል ናቸው።
የትዊተር ገጻቸው 187 ሺህ ተከታዮች ያሉት ሲሆን፣ ስለ ታሊባን አስተዳደር አዘውትረውም መረጃ ያጋራሉ።
170 ሺህ ተከታይ ያላቸው የአፍጋኒስታን የመረጃና ባህል ሚንስትር የመገናኛ ብዙኃን ቁጥጥር ኃላፊ አብዱል ሐቅ ሐማድ ሰማያዊ ጭረት አግኝተዋል።
ቀድሞ የታሊባን አመራር የነበሩና አሁን ደጋፊ የሆኑት ሙሐመድ ጃላል ሰማያዊ ጭረት ከተሰጣቸው በኋላ “ኤለን መስክ ትዊተርን ዳግመኛ ታላቅ አድርጎታል” ብለዋል።
የጽንፈኛው ታሊባን አባላት ትዊተር ገጽ ባለቤት መሆን ሲያከራክር ቆይቷል።
ዶናልድ ትራምፕ ከካፒቶል ሂል ነውጥ ጋር በተያያዘ ከትዊተር ሲታገዱ “ታሊባን ትዊተር ላይ ሆኖ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ግን የሚባረርበት ዘመን ላይ ደርሰናል” ብለው ነበር።
ትዊተር በኤለን መስክ መተዳደር ከጀመረ ወዲህ ለሰማያዊ ጭረት በወር ስምንት ዶላር እያስከፈለ ሲሆን፣ ትዊተርን በአፕል ላይ የሚጠቀሙ ደግሞ 11 ዶላር ይከፍላሉ።
ሰማያዊ ጭረት ያለው የገጹ ተጠቃሚ በሌሎች ተጠቃሚዎች ሲፈለግ በፍጥነት የመገኘት ዕድል ሲኖረው፣ ሐሰተኛ ገጾችንም በቀላሉ ይከላከላል።
በአዲሱ የትዊተር አሠራር ወርቃማ ጭረት የንግድ፣ ግራጫ ጭረት አመራሮችን ጨምሮ ለሌሎችም ይውላል።
ታሊባን በድጋሚ ወደ ሥልጣን ሲመለስ፣ በቀድሞው ዘመን በትዊተር የነበሩ አመራሮችን እና የአስተዳደር ገጸችን ወስዷል። ገጹን ቁልፍ መልዕክቶች ለማስተላለፍም ያውሉታል።












