የአፍጋኒስታን የቀድሞ የምክር ቤት አባል ቤቷ ውስጥ በታጣቂዎች ተገደለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞ የአፍጋኒስታን ሴት የምክር ቤት አባል እና ጠባቂዋ በዋና ከተማዋ ካቡል ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ በታጣቂዎች መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
ታሊባኖች ወደ ካቡል ተመልሰው ሥልጣን ሲይዙ ከአገራቸው ካልወጡ ጥቂት ሴት የምክር ቤት አባላት መካከል የ32 ዓመቷ ሙርሳል ናቢዛዳ አንዷ ነበረች።
በጥቃቱ ወንድሟ እና ሌላ የግል ጠባቂዋ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በታጣቂዎች የተገደለችው የቀድሞ የምክር ቤት አባል ከአገሯ የመውጣት ዕድል የነበራት ቢሆንም ሳትወጣ “ለአፍጋኒስታን ስትከራከር የማትፈራ” ደፋር ነበረች ሲል የቀድሞ ባልደረባዋ አድናቆቱን ገልጾላታል።
ከአንድ ዓመት በፊት በሽምቅ ውጊያ የበላይነት አግኝተው ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ፣ ሴቶች ከየትኛውም ሕዝባዊ ሕይወት ውጪ እንዲሆኑ አድርገዋል።
የካቡል ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ኻሊድ ዛድራን ግድያውን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች ጠንካራ ምርመራ ማድረግ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የቀድሞ የምክር ቤት አባል የሆነችው ማሪያም ሶሌይማንኻይል ስለተገደለችው የቀድሞ ባልደረባዋ “ጠንካራ፣ አደጋ ቢኖረው እንኳን ለምታምንበትን በጽናት በመቆም ምሳሌ የምትሆን ናት” ብላለች።
“አፍጋኒስታንን ለቃ እንድትወጣ ዕድል ብታገኝም፣ እዚያው ቆይታ ለሕዝቧ ለመከራከር የመረጠች ደፋር ናት” ስትል በትዊተር ገጿ ላይ አስፍራለች።
ናንጋራሃር ከተባለው የአፍጋኒስታን ምሥራቃዊ ግዛት የመጣችው ናቢዛዳ፣ ከአራት ዓመት በፊት ለአገሪቱ ምክር ቤት አባልነት ተመርጣ ታሊባን ሥልጣን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ ቆይታለች።
የምክር ቤት አባል በነበረችበት ጊዜ የምክር ቤቱ የመከላከያ ኮሚሽን አባል የነበረች ሲሆን፣ በሰው ኃይል ልማት እና ጥናት ተቋም ውስጥም ሠርታለች።
የአውሮፓ ፓርላማ አባል የሆነችው ሃናህ ኑማን ግድያውን ተከትሎ እንዳለችው “አዝኛለሁ፣ ተቆጥቻለሁ፤ ዓለም የተከሰተውን ነገር ሊያውቀው የገባል።”
ጨምራም “ታሊባን የጾታዊ የመድልኦ ሥርዓት በይፋ ገንብቷል፣ እሷ ግን የተገደለችው በጨለማ ውስጥ ነው”
በምዕራባውያን ይደገፍ የነበረው የቀድሞው የአፍጋኒስታን መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበረው አብዱላህ አብዱላህ፣ በግድያው የተሰማውን ሐዘን ገልጾ፣ “የሕዝብ ተወካይና አገልጋይ ነበረች” ያላትን ናቢዛዳን የገደሉት ቅጣታቸውን እንደሚያገኙ ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።
በአሜሪካ የተመራውን ወረራን ተከትሎ ባለፉት 20 ዓመታት አፍጋኒስታን ውስጥ በከፍተኛ ቦታዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ በርካታ ሴቶች፣ ታሊባን ወደ ሥልጣን ሲመለስ አገሪቱን ለቀው ተሰደዋል።












