የክሪሚያ ድልድይ በድሮን ጥቃት ምክንያት መዘጋቱን ሩሲያ አስታወቀች

 የክሪሚያ ድልድይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በክሪሚያ የጥይት ማከማቻ ላይ የተፈጸመው የሰው አልባ አውሮፕላን (የድሮን) ጥቃቶች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲስተጓጎል ማድረጉን የሩሲያ ባለስልጣናት ገለጹ።

በተጨማሪም በርካታ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው መውጣታቸውም ተገልጿል።

የክሪሚያ ግዛት አስተዳዳሪ ሰርጌይ አክስዮኖቭ ይህንን ጥቃት የፈጸመችው ዩክሬን ናት ሲሉም ወቅሰዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመበት በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎችም እየለቀቁ መሆናቸውን ሰርጌይ አክለው ገልጸዋል።

በከርች ድልድይ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትም ቆሟል ተብሏል።

የሩሲያ ባለስልጣናት ቅዳሜ ዕለት በድልድዩ ላይ የነበረውን የትራፊክ ፍሰት አቁመውት ነበር።

ነገር ግን በዚያች ቀን በኋላም መኪኖች እንዲተላለፉ ክፍት አድርገውታል።

በኋላም ላይ ድልድዩ ለመኪኖች ክፍት እንደማይሆኑም የክሪሚያ አስተዳደር አስተውቋል።

በክሪሚያ ክራስኖግቫርዴይስኪ ግዛት የሚገኙ መሰረተ ልማቶች የጥቃቱ ኢላማ እንደነበሩም ሰርጌይ አስረድተዋል።

ሆኖም በደረሳቸው መሰረት ይህ ነው የሚባል ጉዳት አልደረሰም ሲሉም አስተዳዳሪው በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ቢቢሲ ይህንን ጥቃት በገለልተኛነት ማረጋገጥ አልቻለም።

አስተዳዳሪው ጥቃት ደርሶባታል ያሏት ግዛት ከከርች ድልድይ በ160 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

ከርች ወይም ክሪሚያ ተብሎ የሚጠራው ይህ ድልድይ ሩሲያና የክሪሚያን ግዛት ያገናኛቸዋል።

በአውሮፓውያኑ 2018 አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ ድልድይ የመንገድና የባቡር ጉዞዎች ይደረጉበታል።

ክሪሚያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ባልሰጠው ህዝበ ውሳኔ ሩሲያ ከዩክሬን በጎሮጎሳውያኑ 2014 የጠቀለለቻት ግዛት ናት።

በድልድዩ ላይ ሰኞ እለት በተፈጸመው ጥቃት በመዝናናት ላይ የነበሩ ሁለት ባልና ሚስት ሲገደሉ እንዲሁም ሴት ልጃቸው ቆስላለች።

የድልድዩ የመኪኖች መተላለፊያ ቢጎዳም በትይዩ ያለው የባቡር መስመር አለመጎዳቱ ተገልጿል።

በድልድዩ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የመሰረተ ልማት አንዱ በሆነው ትራንስፖርት ላይ የተፈጸመው የሽብር ተግባር ነው በማለትም የሩሲያ መንግሥት አውግዟል።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም አገራቸው ለዚህ ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ ቃል ገብተዋል።