በአሜሪካ የታገዱ መጽሐፍት ክበብን በማቋቋም ሳንሱርን እየታገሉ ያሉት ታዳጊዎች

የፎቶው ባለመብት, VHS Banned book club
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሆኑት አሜሪካውያኑ ታዳጊዎች ኤላ ስኮት እና አሊሳ ሆይ መጽሐፍትን ለማንበብ ትግል ውስጥ እንገባለን ብለው አላሰቡም ነበር።
መምህር የሆኑት የአሊሳ እናት በቴክሳስ ግዛት የሊያንደር ከተማ የትምህርት ኃላፊዎች በርካታ መጽሐፍትን ከተቋማት እየከለከሉ መሆኑን ነገሯቸው።
ኃላፊዎቹ ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት “ከወላጆች ቅሬታ ደርሶናል” የሚል ነበር። ከመምህሯ ጋር ያደረጉት ውይይት ሁለቱን ታዳጊ ጓደኛሞች “የታገዱ መጽሐፍት” ክበብን ለማቋቋም ምክንያት ሆናቸው።
ከዚያን ጊዜም ጀምሮም በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች እና በሕዝብ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ እየጨመረ የመጣውን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሳንሱርን በመቃወም በርካታ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
ከታዳጊዎች ቡድን ወደ እንቅስቃሴ
“መጽሐፍት ስለመታገዳቸው የምናውቀው ነገር አልነበረም። ይህንንም ስንረዳ ግንዛቤን ለመፍጠር አንድ ነገር ማደረግ እንዳለብን ተሰማን” ስትል የ17 ዓመቷ ኤላ ለቢቢሲ ተናግራለች።
አክላም “ነጻነት በሰፊው ሰፍኖባታል በምትባለው አሜሪካ ውስጥ መጽሐፍት ይታገዳሉ ብሎ ማሰብ በእጅጉ ግራ የሚያጋባ ነው” ብላለች።
የኤላ እና የአሊሳ “የታገዱ መጽሐፍት ክበብ” ሲጀመር በክፍላቸው ያሉ ሴት ተማሪዎችን ያካተተ ነበር። ከዚያም አድጎ 2709 ተማሪዎች ያሉ የመንግሥት ተማሪዎች ያሉበትን የቫንደርግሪፍት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አባላትን አካቷል።
“ከተለያየ አስተዳደግ እና ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የተውጣጡ አባላት አሉን። ሁላችንንም የሚመለከተን አንድ ጉዳይ አቀራርቦን መወያየታችን ደስ ያሰኛል” ስትል አሊሳ ታስረዳለች።
በሺዎች የሚቆጠሩ የታገዱ መጽሐፍት
አወዛጋቢ ናቸው በሚል የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች የተከለሉት በሊያንደር የትምህርት ኃላፊዎች ብቻ አይደለም። በአሜሪካ በበርካታ ከተሞች እንጂ።
የአሜሪካ ቤተ መጽሐፍት ማኅበር ከትምህርት ቤቶች እና ከሕዝብ ቤተ መጽሐፍት እንዲታገዱ የተወሰኑ መጽሐፍትን መመዝገብ ከጀመረበት ባለፉት 20 ዓመታት የአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል።
የሥነ ጽሑፍ ሳንሱርን የሚከታተለው መንግሥታዊ ያልሆነው ተቋም ፔን አሜሪካ በበኩሉ የአውሮፓውያኑ 2021 እና 2022 የትምህርት ዘመንን መሠረት አድርጎ ባወጣው ሪፖርት፣ በአሜሪካ 32 ግዛቶች ውስጥ ከ2500 በላይ የመጽሐፍት ላይ እገዳ መጣሉን አመልክቷል።
ፔን አሜሪካ ውሳኔው 5 ሺህ ትምህርት ቤቶችን እንደሚሸፍን እና ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ላይም ተጽዕኖ ማድረሱን አስታውቋል።
ኤላ እና አሊሳ የሚኖሩባት የቴክሳስ ግዛት 801 መጽሐፍትን በማገድ በቀዳሚነት ስትቀመጥ፣ ፍሎሪዳ በ566 እና ፔንሲልቬንያ በ457 በተከታታይ ስፍራ ተቀምጠዋል።
ይህ ቁጥርም በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምርም ይችላል ተብሏል።
መጋቢት ወር ላይ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት በሚበዙበት የአሜሪካ የታችኛው ምክር ቤት ‘የወላጆች መብት’ ተብሎ የተጠራውን ረቂቅ ሕግ አሳልፎታል።
ይህ ሕግ ወላጆች በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ መጽሐፍትን ካልወደዷቸው እገዳ እንዲጣልባቸው መብትን የሚሰጥ ነው ሲሉም ተቺዎች ይናገራሉ።
ረቂቁ ዴሞክራቶች አብላጫ ድምጽ ባላቸው የላይኛው ምክር ቤት መጽደቅ ይጠበቅበታል።
“በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አንድ ሰው ምቾት አለመሰማት ተፈጥሯዊ ነው” የምትለው ኤላ “ነገር ግን መጽሐፍትን ለመከልከል እና ሁሉም በዚህ መልኩ ሊያስብ ይገባል ለሚል ውሳኔ መነሻ ሊሆን አይገባም” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እውነትን የማፈን ሙከራ
አብዛኞቹ እንዲታገዱ ጥሪ እየቀረበባቸው ያሉ መጽሐፍት በዘር እና በጾታዊ ማንነት ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው።
ፔን አሜሪካ በአውሮፓውያኑና 2021 እና 2022 ከ1600 በላይ የሚሆኑ ርዕሶች ሳንሱር እንደገጠማቸው አስታውቋል።
ከእነዚህ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ወይም ነጭ ያልሆኑ ገጸ ባህርያት አሏቸው።
ከእነዚህ መጽሐፍት አንዱ በጆርጅ ኤም ጆንሰን የተጻፈው ‘ኦል ቦይስ አር ኖት ብሉ’ የሚለው ጥቁር እና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ሆኖ ማደግን የሚተርከው ማስታወሻ ነው።
“ስላለህ እውነት በምትጽፍበት በማንኛውም ጊዜ ያንን እውነት ለማፈን የሚፈልጉ ሰዎች ይኖራሉ” ሲልም ፀሐፊው ጆንሰን ኤንፒአር ከተሰኘው የአሜሪካ የሕዝብ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግሯል።
ፀሐፊ እና ጋዜጠኛው ጆንሰን የአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት የነጭ ታሪኮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸው፣ ከእንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎች በስተጀርባ ያሉ ኃላፊዎች ልዩነትን እና ብዝኃነትን ለማስተናገድ የሚቸገሩ ናቸው ብለዋል።
ነጭ ታዳጊዎች አብረዋቸው ስለሚኖሩ ሌሎች ማኅበረሰቦች ቢማሩ “አደገኛ ነው” የሚል እሳቤን ይዘዋል ሲሉም ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በአሁኑ ወቅት እያደረገችው ያለው ሳንሱር ለበርካታ አስርት ዓመታት በአሜሪካውያን ሲነበቡ የቆዩ መሠረታዊ ጽሁፎችንም ይነካል።
ለምሳሌም ያህል የፑሊትዘር ሽልማት አሸናፊ በሆነው ሃርፐር ሊ በአውሮፓውያኑ በ1960 የታተመው እና በአሜሪካ ስላለው የዘር ኢፍትሃዊነት የሚያስረዳው ‘ቱ ኪል ኤ ሞኪንግ በርድ’ ይጠቀሳል።
መጽሐፉ በኦክላሆማ እና በሰሜን ካሮላይና በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥም ከሁለት ዓመት በፊት እግድ ተጥሎበታል።
በመናገር ነጻነት ላይ የሚሰሩ ተቋማት እንደሚሉት በአውሮፓውያኑ 2016 እና 2020 ከፍተኛ ፉክክር ከታየበት የአሜሪካ ምርጫ ጋር ተያይዞ በተከሰተ የፖለቲካ ጽንፈኝነት ምክንያት የሚታገዱ መጽሐፍት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
ፔን አሜሪካ በየአካባቢው፣ በየግዛቶች እና በአገር አቀፍ ደረጃ እገዳዎችን የሚደግፉ ቢያንስ 50 ቡድኖችን ለይቻለሁ ብሏል።
እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአብዛኛውም የተቋቋሙት ከሁለት ዓመታት በፊት ነው።
“ወላጆች እና የማኅበረሰቡ አባላት ተማሪዎች በትምህርት ቤት የሚማሩትን በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ” ሲሉ የፔን አሜሪካ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሱዛን ኖሴል ተናግረዋል።
“ነገር ግን አሁን ያለው ሁኔታ በወላጆች እና በመምህራን መካከል ጤናማ በሆነ የትምህርት ቤት አካባቢ ውስጥ ካለው ስጋት የዘለለ ነው” ይላሉ።
እንዲሁም መጽሐፍትን ማን መቃወም ይችላል የሚለውም ደንብ በየግዛቶቹ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተለያየ ነው።
እንዲያውም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተማሪ ወላጆች ያልሆኑ ግለሰቦች ስጋታቸውን እንዲናገሩም ይፈቅዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለሥልጣናትን መገዳደር
በኤላ እና አሊሳ ክለብ ውስጥ የታገዱ መጽሐፍት ይነበባሉ። ውይይትም ይደረግባቸዋል። በቅርቡ በተደረገው የመጽሐፍት ክበብ ስብሰባቸው ላይ መወያያቸው የነበረው በተደጋጋሚ ክልከላ የደረሰበት መጽሐፍ ነው።
ይህ በአሽሊ ሆፕ ፔሬዝ የተጻፈው ‘አውት ኦፍ ዳርክነስ’ ልብወለድ በታዳጊዋ ሜክሲኮ አሜሪካዊት እና በአፍሪካዊ አሜሪካዊ ታዳጊ ወንድ መካክል በ1930ዎቹ የነበረን ፍቅር የሚዳስስ ነው።
“እንደ አሜሪካ ግለሰባዊነት ባበበት ማኅበረሰብ ውስጥ የተለያዩ ግለሰባዊነትን የሚያንጸባርቁ ታሪኮችን ለመቃወም የሚሞክሩ ሰዎች መኖራቸው ከማስገረም በላይ ነው” ስትል አሊሳ ታስረዳለች።
“አንድ ሰው መሆን ስለሚገባው ‘ምናባዊ ሰው’ እሳቤን ይፈጥራል። በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ማደግ በጣም አስፈሪ ነው” ስትልም ታስረዳለች።
የቴክሳሶቹ ታዳጊዎች የመጽሐፍ እገዳዎችን በማንበብ ከመቃወም ባለፈ ሌሎች እርምጃዎችን እየወሰደ ያለ እንቅስቃሴ አካል ናቸው።
በሚዙሪ ግዛት ሁለት ተማሪዎች የዌንትዝቪል ትምህርት ቤትን ፍርድ ቤት አቁመውታል።
ክሱም ትምህርት ቤቱ በአውሮፓውያኑ 1993 የኖቤል ሽልማት አሸናፊ በሆነችው በታዋቂዋ ደራሲ በቶኒ ሞሪሰን የተጻፈው ‘ዘ ብሉየስት አይን’ ጨምሮ “አጸያፊ ይዘት” አላቸው በሚል ስምንት መጽሐፍትን በማገዱ ነው።
በኋላም በትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ፈቃድ ሰባቱ መጽሐፍት ወደ ቤተ መጽሐፍቱ እንዲመለሱ ተደርገዋል።
ሌላኛው በአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃንን ቀልብ ስቦ የነበረው ጉዳይ፣ ከሁለት ዓመት በፊት በፔንሲልቬኒያ የተፈጠረው ነው።
በዋናነት በጥቁር እና በላቲን አሜሪካውያን የተደረሱ 300 የሚሆኑ መጽሐፍት፣ መጣጥፎች እና ፊልሞች ላይ እገዳ መጣሉን ተከትሎ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ረዘም ላለ ጊዜ ያደረጉት ተቃውሞ ነው።
የታገዱ መጽሐፍትን ማሰራጨትም የዚህ እንቅስቃሴ አካል ነው።
በፍሎሪዳ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እና ገጣሚው አዳም ትሪት የተከለከሉ መጽሐፍትን ገዝተው ካፌዎችን፣ አይስክሬም መሸጫዎችን ጨምሮ በሕዝባዊ ቦታዎች የሚያከፋፍል ‘ፋውንዴሽን 451’ የተሰኘ ተቋምም መሥርተዋል።
“ከገዛናቸው መጽሐፍት ውስጥ ወደ 3 ሺህ የሚጠጉትን ለሕጻናት እና ወጣቶች አከፋፍለናል። ህልሜም ጥረቴን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት ተጨማሪ ገንዘብ ማሰባሰብ ነው” ሲሉ አዳም ይናገራሉ።
በፓልም ቤይ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት አዳም፣ ለዘመቻው መነሻ የሆናቸው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የአካባቢው ትምህርት ቤት ኃላፊዎች ሁለት መጽሐፍትን ከማስተማር እንዲቆጠቡ መልዕክት ከላኩላቸው በኋላ ነው።
መጽሐቱ ‘ዘ ካይት ራነር’ እና ‘ስላውተር ሃውስ 5’ የተሰኙ ሲሆኑ፣ ‘ወሲባዊ ይዘት’ እና ‘ፀረ ክርስቲያን’ ናቸው በሚል ነበር ባለሥልጣናቱ ክልከላ መጣላቸውን ያስታወቁት።
“የማንቂያ ደወልም ነበር። ወዲያውኑ ነው እርምጃ እንደሚያስፈልግ የተረዳሁት” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Adam Tritt
አዳም እያደረጉ ባሉት ዘመቻ ሁለት ዓይነት ምላሾችን እያስተናገዱ ይገኛል።
በአንድ በኩል የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ማኅበረሰብ አባላትን ጨምሮ፣ ወላጆች እና ታዳጊዎች ሲያመሰግኗቸው በሌላ በኩል ደግሞ ቁጣና ዘለፋም ይደርስባቸዋል።
“ስድብ እና ዘለፋ ብቻ ሳይሆን፣ በተደጋጋሚም የሞት ማስፈራሪያ ይደርስብኛል” ሲሉም መምህሩ ይናገራሉ።
አብዛኛው አሜሪካውያን በመርኅ ደረጃ እነዚህን ነጻነቶች ቢደግፏቸውም ይታገዱ ማለታቸው በተቃርኖ የተሞላ ነው ይላሉ።
እነዚህንም ጉዳዮች ግንዛቤ ማሳደግም መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነም ያስረዳሉ።
በአገር አቀፍ ደረጃ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በሁሉም የፖለቲካ አመለካከቶች ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ አሜሪካውያን እገዳውን ይቃወማሉ። አዳም እንደሚሉት ችግሩ አብዛኛው አሜሪካዊ በዚህ ክርክር ውስጥ ተሳታፊ አለመደረጉ ነው።
“ለዚህም ነው ታዳጊዎች ሲቃወሙ ማየት በጣም አስፈላጊ የሆነው። ለመምረጥ እና ሕግ ለማስቀየር ዕድሜያቸው ላይፈቅድ ይችላል፣ ነገር ግን በሚችሉት እየታገሉ ነው” ይላሉ።
እንደ አዳም ያሉ መምህራን ለታዳጊዎቹ ኤላ ስኮት እና አሊሳ ሆይ በቴክሳስ ላለው “የታገዱ መጽሐፍት” ክበባቸው መነቃቃትን ይፈጥራል።
“ምቾት ስላልተሰማችሁ ይህንን መጽሐፍ አላነብም ማለት ችግር የለውም። ነገር ግን መጽሐፉን ሌሎችም ማንበብ የለባቸው ብሎ ማገድ ፍትሃዊ አይደለም” ስትል አሊሳ ትናገራለች።












