የኬንያ የቀድሞ ፍትህ ሚኒስትር ከታንዛንያ "ተባረሩ"

ማርታ ካሩዋ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማርታ ካሩዋ በታንዛኒያ ባለስልጣናት ለብዙ ሰዓታት ምርመራ እንደተደረገባቸው ፓርቲያቸው ገልጿል

ኬኒያዊቷ ጠበቃ እና የቀድሞ ፍትህ ሚኒስትር ማርታ ካሩዋ በታንዛንያ የተቃዋሚውን ቱንዱ ሊሱ የችሎት ሂደት እንዳይከታተሉ ከአገር መባረራቸውን ገለፁ።

እርሳቸውን ተከትለው የሄዱ ሁለት ባልደረቦቻቸውም በቁጥጥር ስር ውለው ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸውን ተናገረዋል።

የታንዛንያ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ የሰጡት ማብራርያ የለም።

የታንዛንያ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ቻዴማ ሊቀ መንበር የሆነው ሊሱ ባለፈው ወር በአገር ክህደት ወንጀል ከተከሰሰ በኋላ ዛሬ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ይቀርብ ነበር።

ካሩዋ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሲሆኑ "ወደ ኋላ እየተንሸራተተ ያለ" ሲሉ የሚጠሩትን የምሥራቅ አፍሪካ ዲሞክራሲ በይፋ በመተቸት ይታወቃሉ።

ጠበቃዋ ባለፈው ዓመት ከኬንያ ወደ ኡጋንዳ ተወስደው የአገር ክህደት ወንጀል የተመሰረተባቸውን የኡጋንዳ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኪሳ ቤሲጌ ጠበቃ ናቸው።

ልክ እንደ ሊሱ ሁሉ ኪዛም የቀረበበትን ክስ ፖለቲካዊ ነው ሲል ውድቅ አድርጓል።

ካሩዋ የኬንያ ፍትህ ሚኒስትር በመሆን እአአ ከ2005 እስከ 2009 ድረስ ያገለገሉ ሲሆን በ2022 በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ደግሞ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ጋር ምክትላቸው በመሆን ተወዳድረው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህ ዓመት የራሳቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ ፒፕልስ ሊብሬሽን ፓርቲ (ፒኤልፒ)ን አቋቁመዋል።

ፓርቲያቸው ፒኤልፒ ካሩዋ እና ባልደረባቸው ግሎሪያ ኪማኑኢ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ሊን ንጉጊ "ለሰዓታት የዘለቀ ምርመራ" ከተደረገባቸው በኋላ ከአገር እንዲወጡ ተደርገዋል ሲል ገልጿል።

በሕግ ባለሙያዎቹ ላይ የተፈጸመውን ያወገዙት የቻዴማ ዋና ጸኃፊ ጆን ምንዪካ "መፍትሔው በሐሰት የቀረበን የአገር ክህደት ወንጀል እፍረት ለመሸፈን የውጪ አገር ጠበቆችን ማሰር አይደለም። ክሱን እርግፍ አድርጎ መተው እንጂ" ብለዋል።

የታንዛንያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ጥምረት በበኩሉ "በዘፈቀደ በተፈፀመው እስር" መደንገጡን ገልጾ፣ ሊሶ ሚያዝያ 15 ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ካሩዋ ታዛቢ ሆነው አንዲገኙ ተፈቅዶ ነበር ብሏል።

በታንዛንያ በጥቅምት ወር ከሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ በፊት መንግሥት ተቃዋሚዎችን ማሰር መጀመሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ስጋት መጨመሩ ተገልጿል።

ሊሱ የተከሰሰው በሞት ሊያስቀጣ በሚችለው በአገር ክህደት ወንጀል በመሆኑ ዋስትና ሊፈቀድለት አይችልም።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ከተደረገበት የግድያ ሙከራ ተርፏል።

ባለፈው ሚያዚያ ወር የተቃዋሚ መሪው "ማሻሻያዎች ሳይደረጉ ምርጫ አይታሰብም" የሚል ዘመቻ ማካሄዱን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ውሏል።

የታንዛንያ ሕግ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ለማድረግ የተመቸ አይደለም በሚል ስር ነቀል ለውጥ እንዲደረግ እየጠየቀ ነበር።

መንግሥት ግን የሚቀርብበትን ውንጀላ ያስተባብላል።

ቻዴማ ፓርቲ የመሪውን መታሰር ተከትሎ በአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን እንዲፈርም የተጠየቀውን የሥነ ምግባር ደንብ አልፈርመም በማለቱ በጥቅምቱ ምርጫ እንዳይሳተፍ ታግዷል።

የሥነ ምግባር ሰነዱ ፓርቲዎች እና ደጋፊዎቻቸው "ተገቢውን ሥነ ምግባር እነዲያሳዩ" እንዲሁም በምርጫ ወቅት "ሠላም እና አብሮነትን" እንዲያከብሩ ይጠይቃል።

ቻዴማ የሥነ ምግባር ደንቡ ተቃዋሚዎችን ለማፈን እና የመንግሥት አፈና እንዲቀጥል የተዘጋጀ ነው ብሎ ያምናል።

ታንዛንያን ከ1977 ጀምሮ እያስተዳደራት ያለው ሲሲኤም ፓርቲ አሁን ያለውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት በሚቀጥለው ምርጫ አሸንፎ አገሪቱን ማስተዳደር ይቀጥላል ተብሎ ይታመናል።

ፕሬዝደንት ሳሚያ ስሁሉ ፕሬዝደንታዊ እጩ ሆነው ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በ2021 የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊን ሞት ተከትሎ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት በታንዛንያውያን ዘንድ የፖለቲካ ነጻነት በመስጠት ከፍተኛ ውዳሴ እና ሙገሳ አግኝተው ነበር።

ተቃዋሚዎቻቸው ታንዛንያ ዳግም በማጉፉሊ የሥልጣን ዘመን ወደነበረው ጨቋኝ አስተዳደር ተመለሰች ሲሉ ይተቿቸዋል።

መንግሥት ግን የሚቀርብበትን ክስ ያጣጥላል።