ራፐሩ ዲዲ የቀድሞ ፍቅረኛውን ሲደበድብ የሚያሳይ ቪድዮ ተገኘ

ዲዲ እና ካሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ራፐሩ ሻን “ዲዲ” ኮምብስ ድምጻዊት ካሳንድራ “ኬሲ” ቬንቱራ ላይ አካላዊ ጥቃት ሲያደርስ የሚያሳይ ቪድዮ ተገኘ።

ቪድዮው የተገኘው ከደኅንነት መቆጣጠሪያ (ሲሲቲቪ) ላይ ሲሆን ድርጊቱ የተፈጸመው እአአ በ2016 በሆቴል ኮሪደር ላይ ነው።

ሲኤንኤን ይህን ቪድዮ ያስተላለፈው የዲዲ የቀድሞ ፍቅረኛ ኬሲ በፍርድ ቤት ክስ ልትከፍትበት መሆኑ በተሰማበት ወቅት ነው።

ጠበቃዋ ቪድዮው የዲዲን “የሚረብሽ አደገኛ ባህሪ” የሚያሳይ ሲሉ ገልጸዋል።

የዲዲ ጠበቃ ለቢቢሲ ምላሽ አልሰጡም።

ቢቢሲ ቪድዮውን በገለልተኛ ወገን አላጣራም።

ሲኤንኤን እንዳለው፣ ቪድዮው በሎስ አንጀለስ በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ነው የተቀረጸው።

ኬሲ ከሆቴል ክፍል ወጥታ ወደ አሳንሰር (ሊፍት) ስትጓዝ ያሳያል። አንድ ፎጣ ወገቡ ላይ ያሰረ ሰው ይከተላታል። ሲደርስባት እጇን ጎትቶ መሬት ላይ ይጥላታል።

ስትወድቅ ሻንጣ ከእጇ ይወድቃል። መሬት ላይ እያለች ሰውየው ይደበድባትና ሻንጣውን ያነሳል። ከዚያም መልሶ ይመታታል።

ካናቴራዋን ይዞ ለመጎተትም ይሞክራል።

ከመሬት ተነስታ ወንበር ላይ ትቀመጥና የሆነ እቃ ትወረውራለች።

“ይህ አሰቃቂ ቪድዮ የሚረብሽ ማንነቱን ያሳያል። ኬሲ ይሄንን ለማጋለጥ መወሰኗ ከፍተኛ ጥንካሬ የሚጠይቅ ነው። ይህን ምሥል መመልከት ይረብሻል” ሲሉ ጠበቃዋ ገልጸዋል።

አምና በፌደራል ፍርድ ቤት በቀረበ ክስ ላይ ኬሲ እንደተናገረችው በ2016 ዲዲ ሰክሮ ደብድቧት ዐይኗ በልዞ ነበር።

ከሆቴል ክፍሉ እሱ ሲተኛ ለመውጣት ብትሞክርም ተከትሏት ድብደባ እንደፈጸመ ለፍርድ ቤት የቀረበው ሰነድ ያሳያል።

“ኮሪደር ላይ እየጮኸ ይከተላት ነበር። እጇን ይዞ ኮሪደሩ ላይ የነበረ ከመስታወት የተሠራ አበባ ማስቀመጫ ወረወረባት። ለማምለጥ ወደ አሳንሰሩ እየሮጠች ነበር” ይላል የፍርድ ቤቱ ሰነድ።

ይህን ቪድዮ ከሆቴሉ በ50 ሺህ ዶላር ዲዲ እንደገዛው ተገልጾ ነበር።

ዲዲ ላይ የቀረበው የመድፈር፣ ለወሲብ ንግድ ሰዎችን የማዘዋወር ክስ በስምምነት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ምን ያህል ገንዘብ በስምምነቱ እንደተፈረመ ግልጽ አይደለም።

የዲዲ ጠበቃ ቤንጃሚን ብራፍማን፣ ስምምነት ላይ መድረሱ “ጥፋተኛነትን ማመንን አያሳይም” ብለው ነበር።

ስምምነቱ የቀረበበትን ክስ መቃወሙን እንደማይቀለብሰው ገልጸው፣ በራፐሩና በድምጻዊቷ “የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱ አስደስቶታል” ብለዋል።

ከዚያ የፍርድ ቤት ክስ በኋላ ብዙ ሴቶች ዲዲ ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሰባቸው ገልጸዋል።

በሎስ አንጀለስ፣ ማያሚ እና ፍሎሪያ ባሉ ቤቶቹ ፖሊስ ድንገተኛ ፍተሻ አድርጓል። ይህም የፌደራል መንግሥት ከጀመረው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ ጋር በተገናኘ ነው።

ኬሲ የዲዲ ሪከርድ ሌብል የሆነው ‘ባድ ቦይ’ ካስፈረማት በኋላ ብዙ ሙዚቃዎች ለቃለች።