በደቡብ አፍሪካ በልደት ድግስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 8 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ አፍሪካዋ ምሥራቃዊ ኬፕ ግዛት የልደት በዓል በሚከበርበት ቤት ላይ በጅምላ በተፈጸመ ጥቃት ስምንት ሰዎች ተገድለው አራት ደግሞ ቆሰሉ።
ማንነታቸው ያልታወቁ ሁለት ታጣቂዎች በልደት በዓሉ ታዳሚ እንግዶች ላይ “በጅምላ በከፈቱት ተኩስ” ነው በአንድ ላይ ከተሰበሰቡት መካከል በርካቶች ሊገድሉ የቻሉት ሲል ፖሊስ ገልጿል።
ጥቃቱን ከፈጸሙት ሰዎች መካከል የተያዘ የለም። ፖሊስ ወንጀለኞቹን ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች መካከል የልደት በዓሉ ሲካሄድበት የነበረው ቤት ባለቤት ከሟቾቹ መካከል በመሆኑ፣ የተገደሉትን እና የቆሰሉትን ሰዎች ማንነት ለመለየት አልተቻለም።
“እነዚህ ሰዎች የተገደሉት በወንጀለኞች ነው፤ ምንም ያማያውቁ ሰዎች ላይ ይህንን የጭካኔ ጥቃት የፈጸሙትን ሰዎች እስክናገኝ ድረስ እረፍት አይኖረንም” ሲሉ የግዛቱ የፖሊስ ኮሚሽነር ተናግረዋል።
የግዛቱ እና የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ኮሚሽነሮች እሁድ ከሰዓት በኋላ ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆነው ጥቃት የተፈጸመበትን ስፍራ ይጎበኛሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በመሳሪያ የታገዘ ወንጀል ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል አንዷ ብትሆንም፣ የአሁኑ አይነት በጅምላ የሚፈጸም ግድያ ግን እምብዛም የተለመደ አይደለም።
ከወራት በፊት በተለያዩ መጠጥ ቤቶች ላይ ተከታታይ የጦር መሳሪያ ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፣ በዚህም ከ20 የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
እነዚያ ጥቃቶችም አስካሁን በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛሉ።












