በደቡብ አፍሪካ ታጣቂዎች ቤተክርስቲያን ገብተው በጸሎት ላይ የነበሩ ምዕመናንን ዘረፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታጣቂዎች ጆሃንስበርግ በሚገኝ አንድ የአምልኮ ስፍራ በመገኘት በጦር መሣሪያ አስፈራርተው ምዕመናንን ዘረፉ።
ታጣቂዎቹ ኤስዲኤ በሚባል ቤተክርስቲያን በመገኘት ሲካሄድ የነበረውን የጸሎት ሥነ ሥርዓት እንዲቋረጥ ካደረጉ በኋላ የምዕመናኑ ገንዘብ እና ንብረት መዝረፋቸው ተነግሯል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ዘራፊዎቹ ወደ ቤተክርስቲያኑ ገብተው እየተካሄደ ያለውን ሥነ ሥርዓት ሲያቋርጡ የነበረው ሁኔታ በቤተ ክርስቲያኑ የቀጥታ ስርጭት ላይ ለዕይታ በቅቷል።
የቤተክርስቲያኗ ኃላፊ ለምዕመናን መጽናናትን ተመኝተው በሚቀጥለው ቀን የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ አስፍረዋል።
“በእንዲህ ዓይነት ወቅት ቤተክርስቲያን አንድ እንድትሆን እና በሞራል እና በተግባር መደጋገፍ እንድንኖር እንጸልያለን” የሚል መልዕክት ቤተክርስቲያኗ ዝርፊያው የተከሰተበትን አጋጣሚ ከሚያሳይ ቪዲዮ ጋር ይፋ አድርጋለች።
የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ድርጊቱን ኮንነው ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ እንደሚጥሩ አስታውቋል።
ፖሊስን ጠቅሶ ኒውስ24 እንደዘገበው ከሆነ ታጣቂዎቹ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ተሰብስበው ከነበሩ ምዕመናን የግል ንብረቶቻቸውን ተዘርፈዋል።
የደቡብ አፍሪካው የጋውቴንግ ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ ከንብረት ዝርፊያው ባሻገር በምዕመናኑ ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን አስታውቀዋል።
የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ስድስት ታጣቂዎች ቤተ ክርስቲያኗ አገልጋይ ከመድረክ ላይ ሆነው በሚሰብኩበት ወቅት መግባታቸውን ጠቁመዋል።
በቅዳሜው ዘረፋ ወቅት ታጣቂዎቹን የተመለከቱት ሰባኪ በድንጋጤ ስብከታቸውን አቁመው አትሮኖሱን ለቀው ወደ መቀመጫቸው ሲያመሩ ታይተዋል።
ከቀናት በፊት በሌላ ቤተክርስቲያን በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት አንድ ፓስተር ሲገደሉ ሁለት ምዕመናን መቁሰላቸው ተነግሮ ነበር።
እንደ 'ዘ ስቲዝን' ዘገባ ከሆነ አምስት ታጣቂዎች ዲፕስሎት በመባለው አካባቢ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተው ተኩስ ከፍተዋል።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለው የወንጀል ድርጊት የእምነት ተቋማትን ኢላማ እያደረገ መሆኑ በርካቶችን አሳስቧል።
በአገሪቱ ውስጥ በትጥቅ የተደገፉ ዘረፋዎች፣ ግድያዎች እና የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች በስፋት የሚያጋጥም ሲሆን መንግሥት ይህንን ለመዋጋት እያደረገ ያለው ጥረት እምብዛም ውጤት አላስገኘም።
የእምነት ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አፍሪካ ውስጥ አዲስ አይደለም።
በነሐሴ ወር ኛንዳሩአ በሚባል ኬንያ አካባቢ ዘራፊዎች የካቶሊክ ቤተ ክስርስቲያንን ሰብረው በመግባት የተለያዩ ቁሳቁሶችን ዘርፈዋል።












