በካሜሩን በደረሰ የመሬት መንሸራተት የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የነበሩ 14 ሰዎች ሞቱ

በአደጋው የሞቱ ሰዎች አስከሬን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በአደጋው የሞቱ ሰዎች አስከሬን

የካሜሩን ባለሥልጣናት በዋና ከተማዋ ያውንዴ በደረሰ የመሬት መንሸራተት ቢያንስ 14 ሰዎች መሞታቸውን ገለጹ።

የክልሉ ገዥ ናሴሪ ፖል ቤያ እንዳሉት ሕይወታቸው ያለፉት ሰዎች በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የነበሩ ናቸው።

የነፍስ አድን ሠራተኞች እስከ እሁድ አመሻሽ ድረስ አስከሬን እና ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ፍለጋ ላይ ተሰማርተው ነበር።

ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት በርካታ ሐዘንተኞች በቆሻሻ ክምር ላይ በተተከለ ትልቅ ድንኳን ውስጥ በተሰባሰቡበት ወቅት ነው የመሬት መንሸራተቱ የተከሰተው።

አደጋው የደረሰው ከአንድ የእግር ኳስ ሜዳ ግርጌ ላይ ሲሆን በአቅራቢያውም አስከ 20 ሜትር ይደርሳል የተባለ የአፈር ቁልል በመንሸራተቱ ነው። ይህም በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ በታደሙት ሰዎች ላይ ተደርምሶ ከአስር በላይ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል።

አደጋው የደረሰበት የካሜሩን ማዕከላዊ ክልል አስተዳዳሪ የሆኑት ናሴሪ ፖል ቢያ “አስከሬኖችን ወደ ዋናው ሆስፒታል እየወሰድን ነው” በማለት ከአደጋው ስፍራ ሆነው ለጋዜጠኞች የተናገሩ ሲሆን፣ በሕይወት የተረፉ ሰዎች ካሉና ሌሎች አስከሬኖችን የመፈለጉ ሥራ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ኤኤፍፒ እንደዘገበው ትናንት እሁድ አመሻሽ ላይ የፖሊስ የጭነት ተሽከርካሪዎች በነጭ ጨርቅ የተሸፈኑ በርካታ አስከሬኖችን ጭነው ወስደዋል።

አደጋው ከደረሰ በኋላ በመቶወቹ የሚቆጠሩ በአካባቢው የነበሩት ነዋሪዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመታደግ ጥረት ያደረጉ ሲሆን፣ የነፍስ አድን ሠራተኞችም ከአደጋው ስፍራ በመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል።

የመሬት መንሸራተት አደጋው የደረሰው ከዋና ከተማዋ ያውንዴ ዳርቻ ላይ በተለያዩ የሥራ መስክ ላይ ተሰማርተው ጠሚገኙ ሠራተኞች በሚኖሩበት አካባቢ ነው።

በዚህ ዓመት በካሜሩን የደረሰ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዘ አደጋ ይህ መጀመሪያው አይደለም።

በቅርቡ ከባድ ዝናብ በመላ ካሜሩን በርካታ አውዳሚ ጎርፍ አስከትሏል። የመሠረተ ልማቶችን ከማውደም ባለፈ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችንም አፈናቅሏል።