በደቡብ አፍሪካ በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት 15 ወጣቶች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በደቡብ አፍሪካዋ ሶዌቶ በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ ዛሬ ሐምሌ 3፣ 2014 ዓ.ም በተፈጸመ የጦር መሣሪያ ጥቃት ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
ዛሬ እሁድ ጠዋት ኦርላንዶ ኢስት በተባለ መጠጥ ቤት ውስጥ የገቡ ጥቃት ፈጻሚዎች በቡድን ተሰብስበው በነበሩ ወጣቶች ላይ ተኩሰው ነው ግድያውን የፈጸሙት።
ታጣቂዎቹ ወዲያውኑ ከጥቃቱ ስፍራ በነጭ ሚኒባስ ማምለጣቸው ተነግሯል። ለተፈጸመው ግድያ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አስካሁን ያወቀው ነገር እንደሌለ የአካባቢው ፖሊስ ገልጿል።
ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ በርካቶች በጥይት ተመተው በአሳሳቢ ሁኔታ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን የቢቢሲ ዘጋቢ አረጋግጣለች።
በጥቃቱ የተገደሉትና የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሰለባዎች በ19 እና በ35 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው።
የጉዋቲንግ ግዛት ፖሊስ አዛዥ ሌፍተናንት ጄኔራል ኤሊያስ ማዌላ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በጦር መሣሪያ የተፈጸመው ጥቃት “በንጹሃን የመጠጥ ቤቱ ተስተናጋጆች ላይ የጭካኔ ግድያ ነው” ብለዋል።
ከግዛቲቱ ፖሊስ የወጣ መግለጫ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ወደ መጠጥ ቤቱ ሲገቡ ጠመንጃ እና ሽጉጥ ታጥቀው እንደነበረ አመልክቷል።
ማንነታቸው ያልታወቁትን ጥቃት ፈጻሚዎች ለመለየት እና በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ደቡብ ምሥራቅ ውስጥ በሚገኘው ክዋዙሉ-ናታል በተባለው ግዛት ውስጥ ባለ ሌላ መጠጥ ቤት ላይ ዛሬ በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት አራት ሰዎች በጥይት መገደላቸውን ፖሊስ አሳውቋል።
በመሣሪያ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያልተለመዱ አይደሉም። ጥቃቶቹ በአብዛኛው ከወሮበላ ቡድኖችና ከአልኮል መጠጥ ጋር የተያያዙ ናቸው።
ዛሬ ዕሁድ የተፈጸመው ጥቃትን ቀደም ካሉት የተለየ የሚያደርገው በርካታ ወጣቶች የተገደሉበት መሆኑ ነው።
ይህ ግድያ ያጋጠመው ከሁለት ሳምንት በፊት በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ የነበሩ 21 ወጣቶች በጭስ ታፍነው ወይም በመመረዝ ምክንያት ኢስት ለንደን በተባለ ስፍራ ከሞቱ በኋላ ነው።












