የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ለቀጣይ አስርት ዓመታት በመሪነት መቆየት እንደሚፈልጉ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ላለፉት 20 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩት የሩዋንዳው መሪ ፖል ካጋሜ አሁንም ለቀጣይ 20 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ለመቀጠል እንደሚያስቡ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ለአንድ የፈረንሳይ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት በአውሮፓውያኑ 2024 በሚካሄደው ምርጫ ላይ እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።
ከሰባት ዓመት በፊት ካጋሜ አስከ 2034 ድረስ በሥልጣን ላይ ለመቆየት እንዲችሉ ለማድረግ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ ተደርጎበታል።
ባለፈው በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ይፋ የተደረገው ውጤት እንደሚያመክተው ካጋሜ 99 በመቶ በሆነ ድምጽ አሽንፈዋል። ነገር ግን በርካታ ከሩዋንዳ ውጪ ያሉ ይህንን ምርጫ ትክክለኛ ያለሆነ በማለት ያጣጥሉታል።
የ64 ዓመቱ ካጋሜ በቀጣይ ምርጫ ላይ ይሳተፉ እንደሆነ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ “ለቀጣይ 20 ዓመት ለመወዳደር አስባለሁ። ምርጫ ማለት የሕዝብ የሚፈልገውን መምረጥ ማለት አስከሆነ ድረስ፣ ችግር የለብኝም” በማለት መልሰዋል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ አስተያየት አያስደንቅም የሚሉት የሂዩማን ራይትስ ዋች የማዕከላዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ልዊስ ሙጄ “ሩዋንዳ የፖለቲካ ተቃዋሚ መሆን ይቅርና መንግሥትን መቃወም የማይቻልባት በጣም አደገኛ አገር ናት. . . እናም ይህ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት ለቀጣይ ዓመታት ባለበት ይቀጥላል” ብለዋል።
“ካጋሜ በሥልጣን ላይ ለቀጣይ 20 ዓመታት የሚቆዩ ከሆነ ሩዋንዳ ትክክለኛዋ ሲኦል ትሆናለች” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት ደግሞ አሜሪካ ውስጥ ጠበቃና የዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ቻርለስ ካምባንዳ ናቸው።
ጨምረውም ሩዋንዳውያን በአሁኑ ወቅት በፍርሃት ውስጥ ነው የሚኖሩት፣ ቻርለስ ከአንድ በላይ ሚኒስትሮች ነገሩኝ እንደሚሉት፣ ከአገር ቢወጡም ሊገደሉ እንደሚችሉ ስለሚሰጉ እዚያው መንግሥት ውስጥ መቆየትን እንደመረጡ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ግን በአገራቸው ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን በተመለከተ ምንም ችግር እንደሌለ አጥብቀው ይከራከራሉ።
ፖል ካጋሜ ከ25 ዓመት በፊት ሩዋንዳ ውስጥ የተከሰተውን የዝር ማጥፋት ያስቆመውን አማጺ ቡድናቸውን በመምራት ነበር ወደ ሥልጣን የመጡት።
ከዚያ በኋላ ካጋሜ እራሳቸውን የአገሪቱ ልማት መሪ አድርገው ሲያቀርቡ የቆዩ ቢሆንም፣ ተቺዎቻው ግን በአገሪቱ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓትን ዘርግተው ሥልጣንን የሙጥን ብለዋል ሲሉ ይወቅሷቸዋል።












