“ለተራቡ ቤተሰቦቼ ገንዘብ መላክ አልቻልኩም” ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም፣ ትግራይ ለሚገኙ “የተራቡ ቤተሰቦቻቸው” ገንዘብ መላክ እንዳልቻሉ ተናገሩ።
“ቤተሰቦቼ ትግራይ ናቸው። ብር ልልክላቸው እፈልጋለሁ። ግን ገንዘብ ልልክላቸው አልቻልኩም” ብለዋል ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባደረጉት ንግግር።
ዶ/ር ቴድሮስ አክለውም “ማን እንደሞተ ማን በሕይወት እንዳለ አላውቅም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ ትግራይ እንደ ባንክ፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ መብራት ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቆራርጣ ቆይታለች።
ለወራት ጋብ ብሎ የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ዳግም አገርሽቷል።
ግጭቱን በመጀመር አንደኛው ወገን ሌላኛውን እየከሰሰ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት ኃይሎች ግጭቱን አቁመው ለድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያ የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።
እስካሁን ግን በአካባቢው ስላለው ጦርነት ከሁለቱም ወገን የሚወጣ መረጃ የለም።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ ዕቀባ በማድረግ ይከሰሳል።
የፌደራል መንግሥቱ በምላሹ ጦርነቱንና የትግራይ ኃይሎችን እንደ ምክንያት ያቀርባል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች በጦርነቱ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚጠብቁ ሲሆን፣ ለረሃብ መጋለጣቸውንም ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ያወጧቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከትግራይ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ “አሳሳቢ የምግብ እጥረት” ገጥሞታል ብሏል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትርና የአሁኑ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ ጦርነቱ ስላሳደረባቸው የከፋ ተጽዕኖ ሲናገሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ባለፈው ሳምንት፣ በትግራይ ያለው ሁኔታ “ከዩክሬን የባሰ ነው። ዓለም ለዩክሬን እና ትግራይ በእኩል መጠን ምላሽ የማይሰጠው፣ እርዳታም በበቂ ደረጃ ለትግራይ የማይቀርበው ዘረኝነት ስለሰፈነ ነው” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
“ያለ ምንም ማጋነን የትግራይ ሰብአዊ ቀውስ ከዩክሬን የባሰ እንደሆነ ልነግራችሁ እወዳለሁ። ከወራት በፊትም ይሄንን ተናግሬዋለሁ። የትግራይ ሕዝብ የቆዳ ቀለሙ ነው [ትኩረት ለመነፈጉ] ምክንያቱ” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት ዶ/ር ቴድሮስ ለትግራይ ኃይሎች መሣሪያ በማቀበል ተባብረዋል ሲል ቢከስም፣ ዋና ኃላፊው ክሱን አጣጥለዋል።
“ወገንተኝነት እንዳሳየሁ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች ሐሰተኛ ናቸው” ብለዋል።
ዛሬ አርብ ነሐሴ 20/2014 ዓ.ም. ሦስተኛ ቀኑን የያዘውን ጦርነት በመቀስቀስ አንደኛው ወገን ሌላኛውን እየከሰሰ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ቀናት ስላለው ሁኔታ የትኛውም ወገን መግለጫ አልሰጠም።
ረቡዕ ዕለት ጥቃት እንደተከፈተባቸው በትግራይ ቴሌቪዥን ያሳወቁት የትግራይ ኃይሎች፤ የአማራ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥምር ኃይል በትግራይ ደቡብ አቅጣጫ መጠነ ሰፊ ጥቃት ጀምረዋል ብሎ ነበር።
ህወሓት ለጦርነት ሲዘጋጅና ከሰላም ድርድሩ ለመራቅ ሰበብ ሲፈልግ ቆይቶ ነበር ያለው መንግሥት ደግሞ፣ ረቡዕ ማለዳ ላይ ጥቃት ፈጽሟል ሲል ከሷል።
የህወሓት ከፍተኛ አመራሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ አሁንም ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነና የትግራይ ሕዝብ እየተሰቃየ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
“አዲስ አበባ ባሉት አመራሮች በተጣለው ዕቀባ ምክንያት ሰዎች እየተራቡ ነው። ሰብአዊ እርዳታ በአፋጣኝ ሕዝቡ ያስፈልገዋል። ሕዝባችን ሰብአዊ እርዳታ እያስገለገው ጦርነት ብንጀምር ሞኝነት ይሆንብናል” ብለዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የአማራ ክልል እና የትግራይ ክልል ከሚዋሰኑበት እንዲሁም በፌደራሉ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት እየተካሄደባቸው እንደሆነ ከሚነገሩት አካባቢዎች 20 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ቆቦ ከተማ ያሉ ነዋሪዎች ረቡዕ ጀምሮ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ድምፅ እንሚሰማ ሐሙስ አመሻሽ ላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ሲሆን ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ የሚሰማው የተኩስ ድምፅ ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
አንዲት ነዋሪ “የከባድ መሣሪያ ተኩስ እየሰማን ነው። አሁንም ድረስ ተኩሱ አልተቋረጠም። ጦርነቱ ተባብሷል። ተጨማሪ ኃይልም ወደ አካባቢው እየገባ ነው” ስትል ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ ገልጻለች።
አንድ ሌላ ነዋሪ የከባድ መሣሪያ ተኩስ መሰማቱ እንደቀጠለና ይህም በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ግራ መጋባትን እንደፈጠረ ገልጿል።
አንዳንዶችም "በአቅራቢያ ወደሚገኝ ከተማ” መሄዳቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
በትግራይ ተነስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በሺዎች ሕይወታቸውን ያጡበት፣ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉበት እንዲሁም በአሜሪካ ባለሥልጣናት አሐዝ መሠረት 700,000 ዜጎች “ለረሃብ” የተጋለጡበት ነው።












