ኡጋንዳዊቷ አትሌት የቀድሞ ፍቅረኛዋ ነዳጅ አርከፍክፎ ባደረሰባት የእሳት ጥቃት ሞተች

የፎቶው ባለመብት, Alamy
የኦሊምፒክ ተወዳዳሪ የነበረችው ኡጋንዳዊቷ አትሌት ሬቤካ ቼፕቴጌ የቀድሞ የፍቅር ጓደኛዋ ነዳጅ አርከፍክፎ ባደረሰባት የቃጠሎ አደጋ ምክንያት መሞቷን የኡጋንዳ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
በቅርቡ በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ የተሳተፈችው የ33 ዓመቷ ኡጋንዳዊቷ የማራቶን አትሌት ባለፈው እሑድ በደረሰባት ጥቃት ምክንያት ከፍተኛ ቃጠሎ እንደደረሰባት ዶክተሯ ተናግረዋል።
ሬቤካ፤ ልምምድ እና ኑሮዋን ሰሜን-ምዕራብ ኬንያ ሲሆን ከቤተ-እምነት ተመልሳ ቤቷ ሳለች ጥቃት እንደደረሰባት የአካባቢው ባለሥልጣናት ገልፀዋል።
አንድ የአካባቢውን ባለሥልጣን አትሌቷ እና የቀድሞ ፍቅረኛዋ በመሬት ጉዳይ አለመስማማት ውስጥ እንደነበሩ መናገራቸው ተዘግቧል። ፖሊስ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ አሳውቋል።
በኬንያ በሴት አትሌቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት አሳሳቢ የሆነ ሲሆን ብዙዎቹ ጥቃቶች እስከሞት ድረስ እየደረሱ ነው።
“አትሌታችን ሬቤካ ቼፕቴጌን በደረሰባት የቤት ውስጥ ጥቃት ምክንያት ሕይወቷ ማለፉን ስናሳውቅ በታላቅ ሀዘን ነው። ፌዴሬሽናችን የሆነውን ነገር ያወግዛል፤ ፍትሕ እንዲሰፍንም ይጠይቃል። ነብሷ በገነት ትረፍ” ይላል የኡጋንዳ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኤክስ ገፁ የለጠፈው መልዕክት።
ምንም እንኳ ቤተሰቧ እስካሁን ስለሞቷ ምንም ነገር ባይሉም በኤልዶሬት ከተማ የሞይ መማሪያ እና ሪፈራል ሆስፒታል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ኦዌን ሜናሽ፤ አትሌቷ በደረሰባት ጥቃት ምክንያት መሞቷን ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
የሬቤካ የቀድሞ ፍቅረኛ የተባለው ግለሰብ በደረሰበት አነስተኛ አደጋ ተመሳሳይ ሆስፒታል እንደገባ ተነግሯል። ግለሰቡ አሁንም ከፍተኛ ክትትል የሚደረግበት ክፍል ውስጥ ቢሆንም “እያገገመ” እንደሆነ ዶክተሩ ገልፀዋል።
“ሁለቱ ሰዎች ከቤታቸው ውጭ ሲጨቃጨቁ ነበር። በዚህ ወቅት ግለሰቡ ፈሳሽ ነገር አንስቶ ካረከፈከፈባት በኋላ በእሳት አያይዟታል” ሲሉ የአካባቢው ፖሊስ አለቃ ጄሬማያህ ኦሌ ኮሲዮም መናገራቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ኬንያ እና ኡጋንዳ ከሚጋሩት ድንበር አካባቢ የመጣችው ሬቤካ፤ ትራንስ ንዞያ በተባለ አካባቢ መሬት ገዝታ ቤት በመሥራት በአካባቢው ካለ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ቀርብ ባለ ሥፍራ ነበር የምትኖረው።
“ይህ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነው። በዚህ ምክንያት አንድ ታላቅ አትሌት አጥተናል። በሥራዋ ስናስታውሳት እንኖራለን” ሲሉ የኡጋንዳ ኦሊምፒክ ኮሚቲ ፕሬዝደንት ዶናልድ ሩካሬ ፅፈዋል።
ቼፕቴጌ በቅርቡ በፓሪስ ኦሊምፒክ በተደረገው የማራቶን ውድድር 44ኛ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2022 ታይላንድ በተካሄደ የዓለም የተራራ እና የኮረብታ ሻምፒዮና አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት አግነስ ቲሮፕ እና ዳማሪስ ሙቱዋ የተባሉ ሁለት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የተገደሉ ሲሆን በሁሉቱም ግድያዎች የፍቅር ጓደኞቻቸው ቀንደኛ ተጠርጣሪዎች ናቸው።
የቲሮፕ ባል በአሁኑ ወቅት በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ሲገኛ የሙቱዋ ፍቅረኛ ደግሞ አሁንም አድራሻው አይታወቅም።












