የእስራኤል ጦር ግብጽ ከፍልስጤም ከምትጋራው ድንበር እንደማይለቅ ኔታኒያሁ አረጋገጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የሀገራቸው ጦር ጋዛና ግብጽ ከሚጋሩት እና ስልታዊ ጠቀሜታ ካለው የፊላደልፊ ‘ኮሪደር’ እንደማይለቅ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእየሩሳሌም ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ወደፊት በሚኖር ዘላቂ የተኩስ ማቆም ስምምነት ውስጥ በጋዛና ግብጽ ድንበር የእስራኤል ወታደሮችን ለማስፈር ሌላ አማራጭ ካለ “ለመቀበል ዝግጁ ነኝ” ካሉ በኋላ “ግን ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኔታኒያሁ በዚህ ነጻ የድንበር ቀጠና የመሳሪያ ዝውውርን ለመግታት እና ታጋቾች ወደ ሌላ ስፍራ እንዳይወሰዱ የእስራኤል ጦር ወታደሮች መቆየት ይኖርባቸዋል ሲሉ ተከራክረዋል።
እስራኤል ከፊላደልፊ ‘ኮሪደር’ ወታደሮቿን አላስወጣም ማለቷ የተጀመረውን ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት የማደናቀፍ ሙከራ ነው ሲል ሀማስ መቃወሙን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ጨምሮም እስራኤል ላይ ጫና የማሳደሪያ ጊዜው አሁን ነው ብሏል።
ትላንት ረቡዕ መግለጫ የሰጡት ኔታኒያሁ ወደፊት ማንኛውም ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚኖር ከሆነ በፊላደልፊ ኮሪደር በኩል “ምንም ዓይነት ክፍተት” የሚተው ሊሆን አይችልም ብለዋል።
“በጽሑፍ ወይም በቃል ሳይሆን መሬት ላይ በተግባር በዚያ ኮሪደር ላይ እየሆነ ያለውን ለመከላከል የሚያስችል ሌላ አማራጭ ካለ ለመቀበል ዝገጁ ነን” ያሉት ኔታኒያሁ “ይህ ሲሆን አይታየኝም። እሱ እስከሚሆን ደግሞ በዚያ እንቆያለን” ብለዋል።
ኔታኒያሁ ደጋግመው እያሳዩት ያለው ፍላጎት በደቡባዊ ጋዛ የሀገራቸው ጦር የመውጣት ‘ቅንጣት’ ፍላጎት እንደሌለው ማረጋገጫ የሰጠ ነው።
ይህንን ፍላጎታቸውን አስረግጠው የተናገሩ ሲሆን በድንበሩ የእስራኤል ጦር መቆየትን አስፈላጊነት “ቀይ መስመር’ ሲሉ ገልጸውታል።
“ሰዎችን ይህ ውሳኔ [ከድንበሩ የእስራኤል ጦር መውጣት] ስምምነቱን ያኮላሸዋል ይላሉ። እኔ ደግሞ ይህ ከሆነ እኛን ያኮላሸናል እላለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ኔታኒያሁ ባለፈው ሳምንት ሀማስ 6 ታጋቾችን መግደሉን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “ምክንያቲዊ ያልሆነ፣ ኢ-ሞራላዊ እና ጤነኝነት የሚጎድለው” ተግባር ነው ብለዋል።
“ቀይ መስመሮች አሉን። እነዚህን ቀይ መስመሮችን አልቀየርናቸውም። ይዘናቸው እንቆያለን” ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒሰትሩን በጋዛ-ግብጽ ድንበር ወታደሮቹን የማቆየት ፍላጎት፤ የደኅንነት ጉዳዮች ኃላፊያቸው እና የመከላከያ ሚኒስትሩ በሌሎች አማራጮች እንዲተኩ ማሰባቸውን በተመለከተ በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል።
በአካባቢው ያለውን ሁኔታ የሚቃኝ በቴክኖሎጂ የታገዘ መፍትሔ ወይም የእስራኤል አጋር የሆኑ ሀገራት ወታደሮች እንዲሰፍሩ ማድረግን እንደ አማራጭ ቀርበዋል።
ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በጉዳዩ ላይ በነበረ ውይይት በመከላከያ ሚኒስትሩ እና በኔታኒያሁ መካከል በኃይለ ቃል የተሞላ ምልልስ ነበር። በዚህ ምልልስ ኔታኒያሁ ድርድር ‘ጭራሽ አትፈልግም የሚል’ ወቀሳ እንደቀረበባቸው ተሰምቷል።
ኔታኒያሁ ጦርነቱ ከማቆሙ በፊት የሀማስ መሪው ያህያ ሲናዋር እንዲገደሉ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው በርካቶች ያማናሉ።
ኔታኒያሁ ስምምነት እንዳይደርስ እንቅፋት የሆነው ሀማስ ነው ሲሉ ይተቻሉ።
በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከፍ ያለ ፍላጎት የታቀደው የተኩስ ማቆም ስምምነት ሊጀመር የሚችለው እስራኤልና ሀማስ ሲስማሙ ብቻ ነው።
የእስራኤል ብሔራዊ የሬዲያ ጣቢያ ስማቸውን ያልተጠቀሰ ከፍተኛ ባለስልጣን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የእስራኤል ዋነኛ ተደራዳሪ እና የሞሳድ ኃላፊው ዴቪድ ባሪን የእስራኤል ጦር ከጋዛ-ግብጽ ድንበር የመውጣት ጉዳይ በድርድሩ ሂደት የሚመጣ ሊሆን ይገባል ብለው ያምናሉ።












