ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ትፈጽማለች በሚል ስጋት አሜሪካ ለዜጎቿ ማስጠንቀቂያ አወጣች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በኢራን ሊቃጣ በሚችል ጥቃት ስጋት ምክንያት ዜጎቿ በእስራኤል እንቅስቃሴ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አስጠነቀቀች።
የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞቹ ከኢየሩሳሌም፣ ቴል አቪቭ ወይም ቤርሳቤህ ከተሞች ውጪ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ አሳስቧል።
በተመሳሳይ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት ከኢራን ሊፈጸም የሚችል ጥቃት መኖሩን በመግለጽ በጉዞ ማሳሰቢያው ላይ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።
የጀርመን አየር መንገድ የሆነው ሉፍታንዛ ወደ ኢራን መዲና ቴህራን የሚያደርገውን በረራ እስከ መጪው ቅዳሜ ድረስ ሰርዟል።
ኢራን ከ11 ቀናት በፊት በሶሪያ ዋና ከተማዋ በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤቷ ላይ በተፈጸመው ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት ቆይታለች።
እስራኤል እንደፈጸመችው በሚታመነው በዚህ ጥቃት ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ጨምሮ 13 ሰዎች ተገድለው ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ከኢራን አቻቸው ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ኢራን ውጥረቱን ሊያባብስ ከሚችል ጥቃት እራሷን እንድታቅብ ጠይቀዋል።
ከሶሪያው ጥቃት በኋላ ኢራን በቀጥታ እስራኤል ላይ ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል በተደጋጋሚ ሲገለጸ ቆይቷል።
አንዳንዶች ደግሞ ቴህራን እስራኤል ጥቃት የምትፈጽመው በቀጥታ ሳይሆን በምትደግፋቸው ቡድኖች በእጅ አዙር ነው የሚሆነው ብለዋል።
ኢራን በጋዛ እስራኤልን እየተዋጋ ያለውን ሐማስን እንዲሁም በቀጠናው የእስራኤል ጠላት የሆኑትን ሄዝቦላህ እና የየመን ሁቲ አማጺያንን ታስታጥቃለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትናንት ሐሙስ ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ኢራን እስራኤል ላይ “ከባድ የሆነ ጥቃት” ለማድረስ እያዛተች ነው በማለት ይህ የሚሆን ከሆነ አሜሪካ ለእስራኤል የማይነጥፍ ድጋፏን ትሰጣችለ ብለዋል።
የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ዘመቻ አዛዥ ኤሪክ ኩሪላ በቀጠናው ስላለው የደኅንነት ስጋት ለመምከር ወደ እስራኤል ተጉዘዋል።
ፔንታገን የኤሪክ ኩሪላ ጉብኝት ቀድሞ የታቀደ ቢሆንም በቅርቡ ያጋጠሙ ክስተቶችን ተከትሎ ጉዞው በቶሎ እንዲደረግ ተወስኖ አዛዡ ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር መጓዛቸውን አረጋግጧል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢራን አጸፋዊ እምጃ ለማንም የሚጠቅም አይደለም ሲሉ ለቻይና፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተናግረዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በውጭ አገራት የሚገኙ የእስራኤል ኤምባሲዎች ደኅንነት “ከአሁን በኋላ የተረጋገጠ አይደለም” ሲሉ ተናግረው ነበር።
የዚህ ባለሥልጣን ንግግር ምናልባት የኢራን የጥቃት ዒላማዎች የእስራኤል ቆንስላዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት በበኩላቸው የኢራን ቀጥተኛ ጥቃት አግባብ የሆነ የእስራኤል ምላሽ ያገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የተከቀሰቀው ጦርነት ስድስት ወራት አልፈውታል።
እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ባለችው ጥቃት አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ33 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።












