በእንግሊዝ አሽከርካሪዎች በስህተት በፍጥነት በማሽከርከር ክስ ተቀጥተዋል ተባለ

የመንገድ ላይ ካሜራዎች

የፎቶው ባለመብት, PA Media

በእንግሊዝ በፍጥነት አሽከርክረዋል በሚል በስህተት የተቀጡ በሺዎች የሚቆጠሩ አሽከርካሪዎች ቅጣታቸው ሊሰረዝላቸው እንደሚችል ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው በተወሰኑ አውራ ጎዳናዎች እና የፍጥነት መንገዶች ላይ የተገጠሙ ተለዋዋጭ ፍጥነት መቆጣጠሪያ ካሜሪያዎች ላይ 'ቴክኒካዊ ስህተት' ከታየ በኋላ ነው።

አውራ ጎዳናዎች እና የፍጥነት መንገድን የሚያስተዳድረው ብሔራዊ ተቋም ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ 2650 በስህተት የተመዘገቡ ክስተቶችን እንዳገኘ ገልጿል።

ክስተቱ ያጋጠመው የፍጥነት ወሰን ምልክቶች በሚለዋወጡበት እና ካሜራዎች ይህን ቀርፀው በሚመዘግቡበት ጊዜ መካከል የ10 ሰከንድ መዘግየት በመኖሩ ምክንያት ነው።

ይህም አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን የጨመሩት የፍጥነት ወሰን ምልክቱ ሳይቀየር በፊት እንደሆነ አድርገው ካሜራዎቹ በማሳየታቸው ነው።

በዚህ ምክንያት የተቀጡ አሽከርካሪዎችን ፖሊስ እንደሚያነጋግር እና ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸው እንዲሁም የተያዘባቸው የጥፋት ነጥብ እንደ ሁኔታው ከመንጃ ፈቃዳቸው ማኅደር ላይ እንደሚሰረዝላቸው ተገልጿል።

ብሔራዊ የፈጣን መንገድ አስተዳዳሪው ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን፣ የተቋሙ ዋና ኃላፊ ኒክ ሃሪስ የችግሩ መፍትሔ ተለይቷል ብለዋል።

"ደኅንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው . . . ሁሉም አሽከርካሪዎች እንደ ወትሯቸው የፍጥነት ወሰን ምልክቶችን ማስተዋላቸውን መቀጠል አለባቸው። በተፈጠረው ስህተት የቅጣት ሰለባ የሆኑትን የሚመለከተው የፖሊስ ኃይል ያነጋግራቸዋል" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእንግሊዝን ፈጣን መንገድ የሚያስተዳድረው ብሔራዊ ተቋም ፣ በአንዳንድ ዋና አውራ ጎዳናዎች እና የፍጥነት መንገዶች ላይ የተገጠሙ የተለዋዋጭ ፍጥነት መቆጣጠሪያ ካሜሪያዎች ከፍጥነት ወሰን ምልክቶች ጋር አለመናበባቸውን ገልጿል።

ይህ ማለት የፍጥነት ወሰን ምልክት ከሚቀየርበት ጊዜ ካሜራው በ10 ሰከንድ በመዘግየቱ አንዳንድ አሽከርካሪዎች የፍጥነት ወሰን ምልክቱ ከመቀየሩ በፊት ከፍጥነት በላይ እንዳሽከረከሩ ተደርገው በስህተት ተለይተዋል።

ለዚህ ምክንያቱ "ድንገተኛ የሆነ የትራፊክ ፍሰት መለዋወጥ" እንደሆነ ተቋሙ ጠቅሷል።

ተቋሙ በእነዚህ መንገዶች ላይ ከአውሮፓውያኑ 2021 አንስቶ ከ6 ሚሊዮን ጊዜ በላይ የተለዋዋጭ ፍጥነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ጠቅሶ፣ ያጋጠሙት ክስተቶች ግን 2650 ብቻ እንደሆኑ ገልጿል። ይህም በእያንዳንዱ ቀን ከአንድ ክስተት ያነሰ እንደማለት ነው።

የተለዋዋጭ ፍጥነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎች ጥቅም ላይ የሚውሉት የትራፊክ መጨናነቅ እና መዘጋጋት በሚያጋጥምበት ጊዜ ሲሆን ሁልጊዜ አገልግሎት አይሰጡም።

የተፈጠረው ስህተት 10 በመቶ በሚሆኑት የእንግሊዝ አውራ ጎዳናዎች እና የፍጥነት መንገዶች ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል።

በፈጣን መንገዶች እንዲሁም ሰሜን እና ምዕራባዊ ሚድላንድን ከምሥራቅ አንግሊያ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ላይ ያሉ ሁሉም የተለዋዋጭ ፍጥነት ወሰን መቆጣጠሪያ ካሜራዎች ላይ ስህተቱ አጋጥሟል።

ተቋሙ የካሜራዎችን ሁኔታ ለማረጋገጥ ከፖሊስ ጋር እየሠራ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ማንም ሰው በስህተት እንደማይቀጣ ቃል ገብቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፖሊስ ካሜራዎች በትክክል መሥራታቸውን እርግጠኛ እስከሚሆን ድረስ አሽከርካሪዎችን መቅጣቱን አቁሟል።

የትራንስፖርት መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ "በዚህ ስህተት ተጎጂ የሆኑትን ይቅርታ እንጠይቃለን፣ ደኅንነት ችላ የሚባል ጉዳይ አልነበረም። ወደፊት ማንም ሰው በስህተት እንዳይቀጣ ከፖሊስ ጋር እየሠራን ነው" ብለዋል።

"ሕግ ማስፈፀሙ አሁንም ተግባራዊ እየሆነ ሲሆን፣ ማኅበረሰቡም ሕግ የሚጥሱ አሽከርካሪዎች ብቻ እንደሚቀጡ እርግጠኛ መሆን ይችላሉ" ብለዋል።