አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ለምን ከማኅበራዊ ሚዲያ አገደች?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከታኅሣሥ 10 ጀምሮ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች በአውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ይፋ ተደርጓል።
ቀደም ብለው የተከፈቱ ገጾችም መዘጋታቸውን ለማረጋገጥ "ምክንያታዊ እርምጃዎችን" መውሰድ ይኖርባቸዋል ተብሏል።
ይህም በብዙ ወላጆች ዘንድ የተደገፈ እና በዓለም ላይ የመጀመሪያው ፖሊሲ ሆኗል።
መንግሥት እንደሚለው ከሆነ እገዳው ልጆች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሊያጋጥሟቸው የሚችሏቸውን "ግፊቶች እና አደጋዎች" ለመቀነስ ያለመ ነው።
ይህም "በስክሪን ላይ የበለጠ ጊዜ እንዲያሳልፉ የሚያበረታቱ ባህሪያትን እንዲሁም ጤናቸውን እና ደኅንነታቸውን ሊጎዱ የሚችሉ ይዘቶችን ማቅረብን" ያካትታል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ መንግሥት ባሠራው ጥናት መሠረት፤ ከ10-15 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት 96 በመቶዎቹ ልጆች ማኅበራዊ ሚዲያ ይጠቀማሉ። ከአሥሩ ውስጥ ሰባቱ ደግሞ ለጎጂ ይዘቶች እና ባህሪያት ተጋልጠዋል።
እነዚህም ሴቶችን ከሚያንቋሽሹ ጀምሮ የድብድብ፣ የአመጋገብ መዛባት እና ራስን ማጥፋትን የሚያበረታቱ ቪዲዮዎች እና ይዘቶች ናቸው።
ከሰባት ልጆች ውስጥ አንዱ ከአዋቂዎች ወይም ከትልልቅ ልጆች ስሜታዊ ትስስር የመፍጠር ሁኔታ እንዳጋጠመው ሪፖርት አድርጓል። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የተለያዩ ጥቃቶች እንደገጠማቸው ተናግረዋል።
የአውስትራሊያ የ36 ወራት የዘመቻ ቡድን ዳይሬክተር የሆኑት ግሬግ አትዌልስ ማኅበራዊ ሚዲያ የመጠቀሚያ ዝቅተኛ የዕድሜ ገደብ ከ13 ወደ 16 ዓመት እንዲያድግ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ይህ እገዳ ሳይሆን "ልጆች ራሳቸውን እንዲያውቁ የሚያስችል ጊዜ ነው። በተጨማሪም በማኅበራዊ ሚዲያ ሥነ ምኅዳር ዲጂታል ዜጎች የሚሆኑበትን ጊዜ በ36 ወራት የሚያዘገይ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ምን ዓይነት ማኅበራዊ መድረኮች ይታገዳሉ?
የአውስትራሊያ መንግሥት እስካሁን ድረስ በእገዳው ውስጥ የሚካተቱ ዘጠኝ ማኅበራዊ መድረኮችን ይፋ አድርጓል። ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕቻት፣ ትሬድስ፣ ቲክ ቶክ፣ ኤክስ፣ ዩቲዩብ፣ ሬዲት እና ኪክ ናቸው።
እገዳውን የበይነ መረብ ጌሞችን እንዲያካትት ጫና እየተደረገ ነው። እንደ ሮድብሎክስ እና ዲስኮርድ ያሉ የጨዋታ መድረኮች በቅርቡ በእገዳው ውስጥ እንዳይካተቱ ለማድረግ በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ላይ የዕድሜ ገደብን አስተዋውቀዋል።
መንግሥት ማኅበራዊ መድረኮቹን መገምገሙን እንደሚቀጥል እና ይህን ለማድረግ ሦስት ዋና ዋና መስፈርቶችን እንደሚያጤን ተናግሯል።
እነዚህም የመድረኩ ብቸኛ ወይም "ዋና ዓላማ" በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ተጠቃሚዎች መካከል የበይነ መረብ ማኅበራዊ መስተጋብርን ማስቻል ብቻ መሆኑን፤ ተጠቃሚዎች ከአንዳንድ ወይም ከሌሎች ተጠቃሚዎች ጋር መስተጋብር እንዲፈጥሩ የሚፈቅድ መሆኑን እና ተጠቃሚዎች ይዘት እንዲለጥፉ የሚፈቅድ መሆኑን ያካትታሉ።
ዩቲዩብ ኪድስ፣ ጉግል ክላስሩም እና ዋትስአፕ እነዚህን መስፈርቶች ባለሟሟላታቸው በእገዳው አልተካተቱም። ልጆች አካውንት ሳያስፈልጋቸው እንደ ዩቲዩብ ባሉ መድረኮች ላይ አብዛኛዎቹን ይዘቶች ማየት ይችላሉ።
እገዳው እንዴት ተግባራዊ ይደረጋል?
ልጆች እና ወላጆች እገዳውን በመጣሳቸው አይቀጡም። ይህንን በማስፈጸም የሚከሰሱት የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ናቸው። ለከባድ ወይም ተደጋጋሚ ጥሰቶች እስከ 32 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ቅጣት ይጣልባቸዋል።
እነዚህ ኩባንያዎች ልጆች ከመድረኮቻቸው እንዲወጡ ለማድረግ እንዲሠሩ መንግሥት ጠይቋል። በትክክል ባይጠቅስም ዕድሜ የሚጠይቁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም "ምክንያታዊ እርምጃዎችን" መውሰድ አለባቸው ብሏል።
የመንግሥት መታወቂያዎችን፣ የፊት ወይም የድምጽ መለያ እና የዕድሜ ግምትን ጨምሮ በርካታ አማራጮች ቀርበዋል።
መንግሥት የተለያዩ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ ማኅበራዊ መድረኮቹን እያበረታታ ነው። መድረኮቹ ተጠቃሚዎቹ የራሳቸውን ዕድሜ በማወጅ ወይም ወላጆች ለልጆቻቸው ዋስትና በመስጠት ላይ መተማመን እንደማይችሉ ገልጿል።
ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ትሬድስን የያዘው ሜታ ከታህሳስ 4 ጀምሮ የታዳጊዎችን መድረክ መዝጋት እንደሚጀምር አስታውቋል። በስህተት የታገዱ ሰዎች ዕድሜያቸውን ለማረጋገጥ የመንግሥት መታወቂያ መጠቀም ወይም የቪዲዮ ሰልፊ ማቅረብ እንደሚችሉ ኩባንያው ተናግሯል።
ሌሎቹ የታገዱ ማኅበራዊ መድረኮች እገዳውን እንዴት እንደሚያስከብሩ እስካሁን አልገለጹም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተግባራዊ ይሆናል?
ኩባንያዎች ምን ዓይነት ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ግልጽ ግንዛቤ በሌለበት የማኅበራዊ ሚዲያ እገዳው ውጤታማ ይሆናል ወይ? የሚለውን ለመናገር አስቸጋሪ ነው።
የዕድሜ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂዎች አንዳንድ ተጠቃሚዎችን በስህተት ሊያግዱ እና ሌሎች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ተጠቃሚዎችን ደግሞ ሊቀበሉ እንደሚችሉ ስጋቶች ተነስተዋል።
የአውስትራሊያ መንግሥት ሪፖርት እንደሚያሳየው የፊት ግምገማ ቴክኖሎጂ ለትክክለኛው የሥነ ሕዝብ ጥናት አስተማማኝ ዘዴ አይደለም።
ለሚፈጸሙ ጥሰቶች የተቀመጡት ቅጣቶች በቂ ናቸው ወይ? የሚለውም ጥያቄ አስነስቷል።
የቀድሞው የፌስቡክ ሥራ አስፈፃሚ ስቴፈን ሼለር "ሜታ 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አንድ ሰዓት ከ52 ደቂቃ ያህል ብቻ ይወስድበታል" ሲሉ ለአውስትራሊያ አሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
ተቺዎች በበኩላቸው እገዳው በአግባቡ ቢተገበር እንኳ በልጆች ላይ የሚደርሰውን የበይነ መረብ ጉዳትን አይቀንሰውም ይላሉ።
በሌላ በኩል የፍቅረኛ ማፈላለጊያ ድረ ገጾች እና የጌም መድረኮችበእገዳው አልተካተቱም።
ልጆች ራሳቸውን እንዲያጠፉ እና ከአካለ መጠን ካልደረሱ ልጆች ጋር "ስሜታዊ" ውይይቶችን እንዲያደርጉ አጋልጠዋል ተብለው በቅርቡ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሳቡት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቻትቦቶችም አልተካተቱም።
ሌሎች ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ወዳጅ ያፈሩ ታዳጊዎች ብቻቸውን እንደሚቀሩ በመግለጽ ልጆች በማኅበራዊ ሚዲያ እንዴት እንደሚጠቀሙ ማስተማር የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን በማንሳት ይከራከራሉ።
የአውስትራሊያ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር አኒካ ዌልስ እገዳው "ፍጹም" ላይሆን እንደሚችል አምነዋል።
"በዚህ ሒደት ውስጥ ትንሽ ያልተስተካከለ ነገር ያለ ይመስላል። ትላልቅ ማሻሻያዎች ሁልጊዜም መሰናክል ያጋጥማቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
የመረጃ ጥበቃዎች ስጋት ናቸው?
ተቺዎች፤ የተጠቃሚዎችን ዕድሜ ለማወቅ አስፈላጊ የሆነው ሰፊ የመረጃ አሰባሰብ እና ማከማቻ ምናልባትም የተሳሳተ አያያዝ ሊኖረው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አንስተዋል።
አውስትራሊያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የመረጃ ምዝበራዎች አጋጥመዋታል። ምሥጢራዊ የግል መረጃዎች የተሰረቁበት እና የተሸጡበት ወይም የታተሙበት አጋጣሚ አለ።
መንግሥት ግን ሕጉ ለግል መረጃ ጥበቃ "ጠንካራ እርምጃዎችን" ያካትታል ብሏል።
እነዚህ መረጃዎች ከዕድሜ ማረጋገጫ ውጪ ለሌላ ነገር ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደማይችል እና ይህ ከተደረገ በኋላ የግለሰቦች መረጃ መጥፋት እንዳለበት ተገልጿል። ጥሰቶች ከተፈጸሙም "ከባድ ቅጣት" እንደሚጣል ተደንግጓል።
ማኅበራዊ መድረኮች ለዕድሜ ማረጋገጫ የመንግሥት መታወቂያዎችን ከመጠቀም ውጭ አማራጭ ማቅረብ እንዳለባቸው ገልጿል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ምን ምላሽ ሰጡ?
የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች በህዳር 2024 እገዳው መታወጁ አስደንግጧቸዋል። ለመተግበር አስቸጋሪ፤ ህጉን ለመጣስ ቀላል እና ለተጠቃሚዎች ጊዜ የሚወስድ እንዲሁም የግል መረጃን ለአደጋ የሚዳርግ እንደሆነ ተከራክረዋል።
ልጆችን ወደ ድብቅ የኢንተርኔት አጠቃቀም እንደሚያስገባ እና ወጣቶችን ከማህበራዊ ግንኙነት እንደሚያስወጣ ጠቁመዋል። የስናፕቻት ባለቤት የሆነው ስናፕ እና ዩቲዩብ የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች አይደለንም ብለዋል።
የዩቲዩብ ዋና ኩባንያ የሆነው ጎግል ሕጋዊ ተቃውሞ ለማስነሳት እያሰበ መሆኑ ተዘግቧል። ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጠው ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ሜታ ቀደም ብሎ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ቢገልጽም፣ እገዳው ታዳጊዎች "በሚጠቀሙባቸው ብዙ መተግበሪያዎች ላይ ወጥነት የሌላቸው ጥበቃዎች" እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ በመግለጽ ተከራክሯል።
በጥቅምት ወር በፓርላማ ክርክር ላይ የተገኙት ቲኪቶክ እና ስናፕ እገዳውን እንደሚቃወሙ ነገር ግን ተግባራዊ እንደሚያደርጉት ተናግረዋል።
በእገዳው ውስጥ የተካተተው ብቸኛው የአውስትራሊያ ኩባንያ ኪክ በበኩሉ "የተለያዩ እርምጃዎችን" እንደሚያስተዋውቅ እና ከባለስልጣናት ጋር "ገንቢ በሆነ መንገድ" መሥራቱን እንደሚቀጥል ገልጿል።
"ከትልልቅ የቴክኖሎጂ መድረኮች ለአንዱ ከሚሠራ ግለሰብ ጋር ተነጋግሬ ስለምን እንደሚጨነቁ ጠየቅኳቸው። ይህ ለእኛ ዓለም አቀፍ የወረርሽኝ አደጋ ነው ብለዋል። ከአውስትራሊያ ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ስለሚዛመተው ነገር ይጨነቃሉ። እናም ይህንን ጉዳይ በአውስትራሊያ ለማስቆም ይፈልጋሉ" ሲሉ አትዌል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሌሎች አገሮች ተመሳሳይ እገዳዎች አሏቸው?
ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ማኅበራዊ ሚዲያን እንዳይጠቀሙ የሚከለክለው እገዳ በዓለም ላይ የመጀመሪያው ነው። ሌሎች አገሮች በቅርበት ይከታተሉታል።
ለልጆች የስክሪን ቆይታ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ጊዜን ለመገደብ እና ጎጂ ቁሳቁሶችን እንዳያገኙ ለማድረግ የተለያዩ መንገዶች ተሞክረዋል። በማኅበራዊ መድረኮቹ ላይ ግን ሙሉ በሙሉ እገዳ አላስቀመጡም።
ዩናይትድ ኪንግደም በሐምሌ ወር በጀመረችው አዳዲስ የደኅንነት ሕግ፤ የበይነ መረብ ኩባንያዎች ወጣቶች ሕገ ወጥ እና ጎጂ ይዘቶችን እንዳያዩ ለመከላከል እርምጃዎችን ተግባራዊ ካላደረጉ ከፍተኛ ቅጣት ወይም የሥራ አስፈጻሚዎቻቸው እስር ይጠብቃቸዋል።
ሌሎች የአውሮፓ አገራት በተወሰነ ዕድሜ ገደብ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን መጠቀምን በወላጆች ይሁንታ ብቻ አንዲሆን ፈቅደዋል።
በመስከረም ወር የፈረንሳይ ፓርላማ አማካሪ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ከማኅበራዊ ሚዲያ እንዲከለክሉ እና ከ15 እስከ 18 ዓመት ለሆኑ ሕጻናት የማኅበራዊ ሚዲያ "እገዳ" እንዲጣል መክሯል።
ዴንማርክ ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት ማኅበራዊ ሚዲያን የማገድ ዕቅድ እንዳላት አስታውቃለች። ኖርዌይም ተመሳሳይ ዕቅድ ለመተግበር እየሞከረች ነው።
የስፔን መንግሥት ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት ሕጋዊ አሳዳጊዎቻቸው እንዲፈቅዱላቸው የሚጠይቅ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ ልኳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካዋ የዩታ ግዛት ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት የወላጅ ፈቃድ ሳይሰጥ ማኅበራዊ ሚዲያን ለመከልከል የተደረገው ሙከራ ባለፈው ዓመት በፌዴራል ፍርድ ቤት ታግዷል።
ልጆች እገዳውን ለማለፍ ይሞክራሉ?
ቢቢሲ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው ታዳጊዎች እገዳው ከመጣሉ በፊት በውሸት ዕድሜ አዳዲስ አካውንቶችን እየከፈቱ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች እንደዚህ ዓይነት አካውንቶችን ፈልገው እንዲያስወግዱ አስጠንቅቋል።
ታዳጊዎቹ፤ አማራጭ የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎችን ለመጠቀም ወይም እገዳውን ለማለፍ የሚረዳቸውን አማራጭ ለማግኘት በበይነ መረብ ላይ እየተመካከሩ ነው።
አንዳንድ ታዳጊዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ከወላጆቻቸው ጋር ወደ ጋራ አካውንቶች ቀይረዋል።
የዕድሜ ቁጥጥር ደንብ ከተተገበረ በኋላ በዩኬ እንደተከሰተው ሁሉ የቪፒኤን አጠቃቀም መጨመር እንደሚኖር አስተያየት ሰጪዎች ተንብየዋል።
የአውስትራሊያ የማኅበራዊ ሚዲያ የዘመቻ ቡድን ዳይሬክተር የሆኑት ግሬግ አትዌልስ "አዎ፣ ልጆች ይህን ለማለፍ መንገድ ያገኛሉ። ይህ ማለት ግን ሕጉ መኖር የለበትም ማለት አይደለም። አሁንም ለደኅንነታቸው የሚጠቅሙ ደንቦች አሉን" ብለዋል።















