ጉግል 'ዐይን ላይ የሚደረግ ኮምፒውተር' የተባለ በኤአይ የሚሠራ ስማርት መነጽር ለገበያ ሊያቀርብ ነው

የፎቶው ባለመብት, Google
ጉግል በመጪው የአውሮፓውያን ዓመት በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የሚሠራ ስማርት መነጽር ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታወቀ።
ከዚህ ቀደም ስማርት መነጽር ለማቅረብ ያደረገው ጥረት ባይሳካም በቅርቡ እንደ አዲስ መነጽሩን የሚያስተዋውቅ ይሆናል።
ጉግል በአውሮፓውያኑ 2013 መነጽሩን ሲያስተዋውቅ የወደፊቱ ቴክኖሎጂ ማሳያ ተደርጎ ተወስዶ ነበር። መነጽሩ ከዐይን በላይ ጎልቶ የሚታይ ስክሪን የተገጠመለትም ነበር።
መነጽሩ በ2015 (እአአ) ከገበያ ውጪ ቢደረግም አሁን ግን በድጋሚ ለማቅረብ ጉግል ወስኗል።
ሜታ ባለፈው ዓመት የካቲት ላይ ስማርት መነጽር ያስተዋወቀ ሲሆን፤ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ገዝተውታል።
የጉግል ስማርት መነጽር ከሌሎች የጉግል ምርቶች ጋር የተሳሰሩ ናቸው። መነጽሩን የሚያደርጉ ሰዎች እንደ ጄምኒ ያሉ የጉግል መተግበሪያዎችን መጠቀም ይችላሉ።
ጄምኒ በጽሑፍ እና በድምጽ ለጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ የጉግል ቻትቦት ነው።
ጉግል ለገበያ ከሚያቀርባቸው መነጽሮች አንደኛው ስክሪን የሌለው ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ በመነጽሩ ሌንስ ላይ ስክሪን የተገጠመለት ነው።
የቴክኖሎጂ ተንታኝ ፓውሎ ፔስካቶሬ "ጉግል ከቀደመው ስህተት መማር አለበት። ከዚህ ቀደም መነጽሩን ያስተዋወቀው መውጣት ከነበረበት ጊዜ ቀድሞ ነው" ብለዋል።
ጄምኒ ቻትቦት ስኬታማ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የጉግል ስማርት መነጽር ውጤታማ ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images
ከጉግል ቀድሞ ስማርት መነጽርን ለገበያ ካቀረበው ሜታ ጋር ፉክክር ይጠብቀዋል።
ሜታ ስማርት መነጽሩን የሠራው ከታዋቂው መነጽር አምራች ሬይ-ባን ጋር በመጣመር ነው።
የገበያ ትንታኔ የሚሠራው ካውተንርፖይንት ሪሰርች እንዳለው ከ2025 ወዲህ የስማርት መነጽር ገበያ ተነቃቅቷል።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሠራ መነጽር ገበያ ካለፈው ዓመት በ250 በመቶ ጨምሯል።
በአውሮፓውያኑ 2013 ለገበያ የቀረበው የጉግል ስማርት ስልክ በቀኝ ሌንሱ ላይ ካሜራ የተገጠመለት ነበር።
መነጽሩን በመጠቀም ምሥል ማንሳት፣ ድምጽ መቅዳት እና ሌሎችም ዲጂታል እንቅስቃሴዎች ማድረግ ይቻላል።
ስማርት መነጽሩ ይፋ ከተደረገ በኋላ የግል መረጃ ደኅንነትን ይጥሳል በሚል ትችቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።
ጉግል መነጽሩን ማምረት እንደሚያቆምም አስታውቆ ነበር። ከዚያም መነጽሩን አሻሽሎ እንደ አዲስ ለገበያ አውሏል።
የቢቢሲ የቴክኖሎጂ ዘጋቢ ሮሪ ሴላን-ጆንስ የጉግልን የመጀመሪያ የስማር ስልክ ምርት "የከሸፈ" ሲል ነበር የገለጸው።
'ዐይን ላይ የሚደረጉ ኮምፒውተሮች' በሚል የተገለጹት ስማርት መነጽሮች ስኬታማ የሚሆኑት ውበት እና አገልግሎትን ካጣመሩ ብቻ እንደሆነ አክሏል።
"መነጽሩ ሲደረግ የሚያምር መሆን አለበት። ለመጠቀም ምቹም እንዲሆን ያስፈልጋል" ይላል።
የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ስማርት መነጽሮች ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆኑ ከመነጽር አምራቾች ጋር ተጣምረው ይሠራሉ።
ሆኖም ግን የግል መረጃ ጥበቃ እና የመነጽሮቹ አጠቃቀም ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች አሁንም በቂ ምላሽ አላገኙም።















