ጉግል የማስታወቂያ የበላይነትን ያላግባብ በመጠቀም በአውሮፓ ሕብረት ሦስት ቢሊዮን ዩሮ ገደማ ተቀጣ

የጉግል መለያ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጉግል ማስታወቂያዎችን የሚደለድለውን ስርዓት ያለአግባብ በመጠቀም በአውሮፓ ሕብረት 2.95 ቢሊዮን ዩሮ ቅጣት ተጣለበት።

ሕብረቱ አርብ ዕለት ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የራሱን ምርቶች ወደፊት በማውጣት እና ተቀናቃኞቹን በመጉዳት ፍትኃዊ የውድድር ደንብን ጥሷል ብሏል።

ቅጣቱ በድረ ገፅ ፍለጋ እና ማስታወቂያ ምክንያት በግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ላይ ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች ከፍተኛ ጫና እያደረጉ ባለበት ወቅት የመጣ ነው።

ኩባንያው ለቢቢሲ የሕብረቱ ውሳኔ "ስህተት" መሆኑን የተናገረ ሲሆን፤ ይግባኝ እንደሚልም ገልጿል።

የኩባንያው ዓለም አቀፍ የቁጥጥር ጉዳዮች ኃላፊ ሊ አን ሙልሆላንድ "ፍትኃዊ ያልሆነ ቅጣት ነው የጣለው። እና የጠየቀው ለውጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የአውሮፓ ንግዶች ገንዘብ እንዳያገኙ ከባድ የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

"ማስታወቂያ ለሚገዙ እና ለሚሸጡ ሰዎች አገልግሎት ማቅረብ ፀረ ውድድር አይደለም። ለአገልግሎታችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ አማራጮች አሉን" ሲሉም አክለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ውሳኔውን "ፍትኃዊ ያልሆነ" በሚል ተቃውመዋል።

ፕሬዝዳንቱ በአውሮፓ ቴክኖሎጂ ላይ ታሪፍ መጣል የሚያስችል ምርመራ ለመክፈትም ዝተዋል።

"ከዚህ ቀደምም እንዳልኩት አስተዳደሬ እንደዚህ አይነት አድሏዊ እርምጃዎች እንዲፈፀሙ አይፈቅድም" ሲሉ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም "የአውሮፓ ሕብረት የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ የሚፈፅመውን አሰራር በአፋጣኝ ማቆም አለበት" ብለዋል።

ትራምፕ ባለፉት ወራት የአውሮፓ ሕብረት በአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ እየጣለ ያለውን ቅጣት እና ውሳኔ በተደጋጋሚ ቢተቹም፤ የአሜሪካ መንግሥት በኦንላይን ገበያ ላይ ጉግል ያለውን የገበያ ብቸኝነት በተመለከተ ክስ አቅርቧል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ኮሚሽኑ በጉግል ላይ የጣለውን ቅጣት በአውሮፓ ሕብረት እና በአሜሪካ መካከል የንግድ ውጥረት ምክንያት አዘግይቷል የሚሉ ሪፖርቶችን አጣጥሏል።

አርብ ዕለት ይፋ በሆነው የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ውሳኔ ጉግል የራሱን ቴክኖሎጂዎች ከሌሎች በበለጠ መርጦ ለተጠቃሚዎች አቅርቧል ሲል ከሷል።

ኮሚሽኑ በምርመራ ግኝቱ ጉግል ሆን ብሎ 'አድኤክስ' የተባለውን የራሱን የማስታወቂያ መለዋወጫ ከተወዳዳሪዎቹ በላይ ተደራሽነነቱን ከፍ አድርጎ አሰራጭቷል ብሏል።

በዚህም ምክንያት ተወዳዳሪዎች እና አሳታሚዎች ከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ እንደገጠማቸው እና ገቢያቸውም መቀነሱን ገልጿል።

ተቆጣጣሪው ኩባንያው ይህን አሰራሩን እንዲያቆም እና ሦስት ቢሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ውሳኔ አሳልፏል።

የኮሚሽኑ ቅጣት እስከዛሬ ድረስ የፍትኃዊ ውድድር ደንብን ጥሰዋል ብሎ ከጣለው ቅጣቶች ትልቁ ነው።

እ.አ.አ በ2018 በሌላ የደንብ ጥሰት ጉግልን 4.34 ቢሊዮን ዩሮ ቀጥቷል።