ጉግል የተጠቃሚዎችን የግላዊ መረጃ ጥበቃ መብትን በመጣሱ 425 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተፈረደበት

ጎግል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ፌደራል ፍርድ ቤት ጉግል የተጠቃሚዎችን የግላዊ መረጃን ጥበቃ መብትን (ፕራይቬሲ) በመተላለፍ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ደንበኞቹ መረጃዎችን በመሰብሰቡ 425 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተወሰነበት።

ፍርድ ቤቱ ጉግል የአካውንታቸውን መከታተያ አጥፍተው ከነበሩት ተጠቃሚዎች ጭምር ግላዊ መረጃዎቻቸውን መሰብሰቡን አስታውቋል።

ችሎቱ ጉዳዩን ማየት የጀመረው ጎግል በድረ ገጽ እና በመተግበሪያው ላይ የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ ለመጠበቅ የሰጠውን ዋስትና መተላለፉን በመግለጽ ክስ ከተመሠረተበት በኋላ ነው።

ክሱ እንደሚያስረዳው ጉግል መረጃዎቹን ለመጠቀም በማሰብ ከሞባይል ተጠቃሚዎች የግል መረጃዎችን ሰብስቧል።

ክሱን የመሠረቱት ግለሰቦች ከ31 ቢሊየን ዶላር በላይ የጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀው ነበር።

የጉግል ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ይህ ውሳኔ ምርቶቻችን እንዴት እንደሚሠሩ ግንዛቤ ያስገባ አይደለም፤ ስለዚህ ይግባኝ እንላለን። የግላዊነት መሳሪያዎቻችን ሰዎች መረጃዎቻቸውን እንዲቆጣጠሩ ያደርጋቸዋል፤ ስለዚህ ግላዊነትን የሚለውን (personalisation) ሲያጠፉ ያንን ምርጫቸውን እናከብራለን" ብለዋል።

ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጉግል ከቀረቡበት ከሦስቱ የግላዊ መረጃ ጥበቃ ጥሰቶች በሁለቱ ተጠያቂ መሆኑን ገልጾ ኩባንያው በክፋት ድርጊቱን አልፈጸመም ብሏል።

የሕግ ክሱ በ2020 ሐምሌ ወር ላይ ሲመሠረት 98 ሚሊዮን የሚጠጉ የጉግል ተጠቃሚዎችን እና 174 ሚሊዮን መሳሪያዎችን ይመለከት ነበር።

ከሳሾቹ የጉግል መረጃ የመሰብሰቢያ አሠራር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የስማርት ስልኮች መተግበሪያዎችን፣ የታክሲ ትራንስፖርት አገልገሎት የሚሰጡትን ኡበር እና ሊፍት፣ የኢ ኮሜርረስ ኩባንያዎቹን አሊባባ እና አማዞንን እንዲሁም የሜታ ማኅበራዊ መድረክ ትስስሮች፣ ኢንስታግራም እና ፌስቡክን እንደሚያካትት ጠቅሰው ነበር።

ጉግል በበኩሉ ተጠቃሚዎች በ'ሴቲንጋቸው' ውስጥ የድረገጽ እና የመተግበሪያ እንቅስቃሴያቸውን ሲያጠፉ ጉግል አናሌቲክስን የሚጠቀሙ ንግዶች ድረ ገጾች እና መተግበሪያዎች የአጠቃቀማቸውን መረጃ ሊሰበስቡ ይችላሉ፤ ነገር ግን ይህ መረጃ የተናጠል ተጠቃሚዎችን እንደማይለይ እና የግላዊነት ምርጫቸውን እንደሚያከብር ተናግሯል።

በሌላ ዜና በዚህ ሳምንት ጉግልን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው አልፋቤት የአክስዮን ድርሻው በዘጠኝ በመቶ ዕድገት አሳይቷል።

ይህ የሆነው የአሜሪካ ፍርድ ቤት አልፋቤት የጎግል ክሮምን ድረ ገጽ ማሰሻን መሸጥ እንደሌለበት ነገር ግን ለሌሎች ኩባንያዎች የተወሰኑ መረጃዎችን ማጋራት እንዳለበት ከወሰኑ በኋላ ነው።

ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ የመጣው ጉግል ለረዥም ዓመት በገበያው ላይ የበላይነትን ይዞ መቆየቱን ተከለትሎ በፍርድ ቤት ክርክር ከተነሳ ከዓመታት በኋላ ነው።

የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ ጉግል ክሮምን እንዲሸጥ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ውሳኔ መሠረት የቴክኖሎጂ ኩባንያው ጎግል ክሮምን ይዞ ሊቆይ ይችላል።