ጉግል ገልፍ ኦፍ ሜክሲኮን 'ገልፍ ኦፍ አሜሪካ' በማለቱ በሜክሲኮ ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ጉግል ገልፍ ኦፍ ሜክሲኮ ተብሎ የሚጠራውን የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤን በበይነ መረብ ካርታው ላይ 'ገልፍ ኦፍ አሜሪካ' ብሎ እንዳይጠቅስ በተደጋጋሚ የጠየቀችው ሜክሲኮ ጉግል ላይ ክስ አቀረበች።
የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሸንባም ጉግልን መክሰሳቸውን አስታውቀዋል። ክሱ የት እንደተመሠረተ ግን አልገለጹም።
ጉግል ስለ ጉዳዩ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ባለፈው ሳምንት በሪፐብሊካን የሚመራው የአሜሪካ ምክር ቤት በፌደራል መንግሥት ገልፍ ኦፍ ሜክሲኮ ስሙ እንዲለወጥ ውሳኔ አሳልፏል።
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ቀናቸው ካሳለፉት ውሳኔ አንዱ ገልፍ ኦፍ አሜሪካ ብሎ ስያሜውን መለወጥ ነበር።
"አብዛኛውን ሥራ በአካባቢው የምታከናውነው አሜሪካ ናት። ስለዚህ የእኛ ነው" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
የሜክሲኮ መንግሥት ግን የትራምፕ የስያሜ ለውጥ የሚሠራው በአሜሪካ ሥር ለሚገኘው የአካባቢው ክፍል ብቻ እንደሚሆን አስታውቋል።
"አሜሪካ በሥሯ ያለውን ቦታ ስያሜ መለወጧን ጉግል እንዲከተል ነው የምንፈልገው" ሲሉ የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሸንባም ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቷ አሜሪካ አጠቃላይ የአካባቢውን ስም መለወጥ እንደማትችልም አክለዋል።
ከሦስት ወራት በፊት ፕሬዝዳንቷ ለጉግል በጻፉት ደብዳቤ ስያሜውን እንዲያስተካከል ጠይቀዋል። ከዚያ በኋላም ማስተካከያው ካልተደረገ ክስ እንደሚመሠርቱ አስጠንቅቀው ነበር።
ጉግል የባሕረ ሰላጤው አካባቢ ስያሜ በአሜሪካ በይፋ ለውጥ ሲደረግበት ያንን ተከትሎ በበይነ መረብ ካርታው ላይ ለውጥ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
አሜሪካ፣ ኩባ እና ሜክሲኮ የሚያዋስኑት የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ስያሜው የተለወጠው አሜሪካ ላሉ የበይነ መረቡ ተጠቃሚዎች እንደሆነ እና ሜክሲኮ ያሉ ተጠቃሚዎች የሚያዩት ስያሜ ላይ ግን ለውጥ እንዳልተደረገ ጉግል ገልጿል።
የአሜሪካው የዜና ወኪል አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ገልፍ ኦፍ አሜሪካ በሚል ስም አካባቢውን ላለመጥራት መወሰኑ ለወራት ከዋይት ሐውስ ጋር ቅራኔ ውስጥ ከቶታል። መገናኛ ብዙኃኑ ከዋይት ሐውስ መታደም የሚችላቸው ክንውኖችም ተገድበዋል።
የፌደራል ዳኛ ግን ኤፒ ላይ ያነጣጠረ እርምጃ መውሰድ እንዲቆም አዘዋል።
አሜሪካ በአካባቢው የውሃ ክፍል ያሉ ሌሎች ቦታዎችን የምትጠራበትን ስም እንደምትለውጥም ትራምፕ ገልጸዋል።
ፐርሺያን ገልፍ (ፋርስ ባሕረ ሰላጤ) የሚባለውን አካባቢ አረቢያን ገልፍ ወይም ገልፍ ኦፍ አረቢያ ብለው የመሰየም ዕቅዳቸውን በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት ወቅት ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ "እነዚህ ትርጉም አልባ ጭምጭምታዎች ሐሰተኛ ናቸው" ብለው እንደሚያምኑ እና የስያሜ ለውጥ የሚመጣ ከሆነ ግን "ኢራናውያን በቁጣ እንደሚነሱ" ተናግረዋል።












