ምግብ እየተመገብን ቡና መጠጣት ምን የጤና ችግር ያስከትላል? የባለሙያዎች ምክር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቁርስዎን አልያም ምሳዎን እየበሉ አንድ ስኒ ወፍራም ቡና መጠጣት ለምደው ይሆናል።
ምግብዎን እየተመገቡ አልያም ተመግበው እንደጨረሱ ቡና መጠጣት እንደሌለብዎ የነገረዎ ሰው ካለ እውነቱን ነው።
ቡና ውስጥ ከ1000 በላይ የኬሚካል ውህዶች ያሉ ሲሆን ካፌይን፣ ፖሊፌኖልስ እና ታኒንስ የተሰኙት የምግብ ንጥረ ነገሮች ከሰውነታችን ጋር የሚዋሃዱበትን መንገድ እንደሚያስተጓጉሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
መልካሙ ዜና ይህ ዓይነት ችግር የሚገጥማቸው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ነው።
ያ ብቻም ሳይሆን ህመም የማስከተል አቅሙ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ንጥረ ነገሮች በምግብ እና መጠጥ ውስጥ የሚገኙ በሰውነት ውስጥ አንዳንድ አስፈላጊ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ናቸው። ጤናማ እንድንሆን የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ያስፈልጉናል።
በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሥነ ምግብ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት አሌክስ ሩኒ "ሁሉም ወደ ሰውነታችን የሚገባው ንጥረ ነገር ሙሉ በሙሉ 'ይቋረጣል' ማለት አይደለም፤ የተወሰነ መስተጓጎል ብቻ ሊኖር ይችላል።"
በእርግጥ ተፅዕኖው በቡናው ጥንካሬ ላይ የተመሠረተ ነው።
የምንወስደው ንጥረ ነገር መጠን እና ዕድሜ፣ የምግብ መፈጨት፣ የጤና ሁኔታ እና ዘረመል የመሰሉ ግለሰባዊ ተጋላጭነቶችም አስተዋጽኦ እንዳላቸው ሩኒ ያስረዳሉ።
የምናወራው እንደ ካልሺየም፣ አይረን እና ቫይታሚን ቢ ስላሉ ንጥረ ነገሮች ነው ሲሉም ያክላሉ።
በኦሪገን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የጤና ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤሚሊ ሆ "የእርስዎ የንጥረ ነገር ደረጃ ቀድሞውንም በቂ ከሆነ ሊጨነቁ አይገባም፤ ነገር ግን እጥረት ያለባቸው ወይንም ዝቅተኛ የንጥረ ነገር በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኝ ከመጠን ያለፈ ቡና የሚጠጡ ከሆነ ተጨማሪ መመናመን ሊያስከትል ይችላል" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አይረን
ከ1980ዎቹ ጀምሮ ሳይንቲስቶች ቡናን ምግብ እየተመገቡ መጠጣት ሰውነትዎ አይረንን በቀላሉ ለማዋሀድ አስቸጋሪ እንደሚያደርግበት ደርሰውበታል።
የሥነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት ሆ፣ ቡና ፖሊፊኖልስ (polyphenols) የተባለ ንጥረ ነገር እንደያዘ ያስረዳሉ።
ቡና እየጠጡ የሚመገቡ ከሆነ እነዚህ ፖሊፊኖልስ በምግብ መፍጫ ሥርዓትዎ ውስጥ እንደ አይረን ባሉ ማዕድናት ላይ ይጣበቃሉ።
ይህ ከተከሰተ ሰውነትዎ አይረንን በአግባቡ ወደ ደም ስሮችዎ እና አንጀትዎ ማዋሀድ አይችልም።
ምክንያቱም አይረን በቀላሉ ወደ ደም ስር ውስጥ ገብቶ ለመዋሀድ ነጻ መሆን አለበት። ይልቁንም አይረን ቡና ውስጥ ከሚገኘው ንጥረ ነገር ጋር ተጣብቆ በመቆየት ከሰውነትዎ በቆሻሻ መልክ ይወገዳል።
ይህ በይበልጥ ከእጽዋት እና ፍራፍሬዎች ለምናገኘው አይረን (non-heme iron) በጣም ወሳኝ ነው።
ይህ ዓይነቱ አይረን ቀድሞውኑም ወደ ሰውነታችን ገብቶ ለመዋሀድ ከባድ ነበር። የቡና ፖሊፊኖልስ በተለይ ክሎሮጅኒክ አሲድ የሚባለው ይህን ዓይነቱን አይረን የበለጠ ከመዋሀድ ሊያስተጓጉለው ይችላል።
ስለዚህ ቡና እየጠጡ ከአትክልት ወይንም ፍራፍሬ የተዘጋጀ ምግብ የሚመገቡ ከሆነ የተወሰነው አይረን በሰውነትዎ ጥቅም ላይ ላይውል እንደሚችል እና በቀላሉ እንደ ቆሻሻ እንደሚወገድ ማወቅ ይጠቅምዎታል።
ይህ ሁሉ ማለት የአይረን እጥረት፣ አኒሚያ ያለባቸው ሰዎች እነዚህን በአይረን የበለፀጉ ምግቦች ሲመገቡ ቡናን ወድያውኑ እንዳይጠጡ ለማስገንዘብ ነው።
"በአይረን የበለፀጉ ምግቦችን ከመመገብዎ አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ ወይንም ከተመገቡ ከሁለት ሰዓት በኋላ ቡና መጠጣት ይመከራል" ይላሉ አሌክስ ሩኒ።
የወር አበባ እያዩ ያሉ እና ነፍሰ ጡር ሴቶች ደግሞ ምንጊዜም የአይረን መጠናቸው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል።
በርካታ አይረን እንዲሁም ለአይረን እጥረት፣ አኒሚያ የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ስለሆነ የሚጠጡት ቡና ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካልሺየም
ካሊሺየም ለአጥንት ጤንነት ወሳኝ የሆነ ንጥረ ነገር ነው።
ይኹን እንጂ ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 49 የሚሆኑ የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች መውሰድ ከሚጠበቅባቸው የካልሺየም ንጥረ ነገር በታች በምግባቸው ውስጥ እንደሚያካትቱ ጥናቶች ያሳያሉ።
ይህም በዕድሜያቸው አመሻሽ ላይ የአጥንት መልፈስፈስ እንዲያጋጥማቸው ያደርጋል።
ኩላሊታችን በደማችን ውስጥ የሚገኝን ትርፍ ውሃ በሽንት መልክ ያስወግዳል።
ይህም በሰውነታችን ውስጥ የሶዲየም፣ ፖታሺየም እንዲሁም ካልሺየም መጠን የተመጣጠነ እንዲሆን ያደርጋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ካፌይን ኩላሊታችን እና አንጀታችን ካልሺየምን ሲያጣሩ እና ወደ ሰውነታችን ሲያስገቡ በማስተጓጎል እንቅፋት ይፈጥራል።
በምግባቸው ውስጥ የሚያካትቱት የካልሺየም መጠን አነስተኛ ለሆነ ሰዎች ወይንም ከአጥንት ጋር የተያያዘ የጤና ችግር ላለባቸው ሰዎች ይህ አደገኛ ነው።
"በኦስቲዮፖሮሲስ (Osteoporosis) ኢንተርናሽናል የታተመው እና በብዙዎች የሚጠቀሰው ጥናት ካፌይን የአጥንት ጥንካሬን በማስተጓጎል ለመሳሳት ሊያጋልጥ ይችላል" ይላል ሩኒ።
"ነገር ግን ካፌይን በአጥንት መሳሳት ላይ ያለው ተጽዕኖ ላይ ሌሎች በርካታ ጥናቶች ሊደረጉ ያስፈልጋል።"
ካልሺየም በሰውነታችን ውስጥ ሊጠራቀም ይችላል። ስለዚህ ሰውነታችን የሚያስፈልገውን ያህል በየዕለቱ መውሰድ አይጠበቅብንም።
ነገር ግን በተወሰኑ ወራቶች መካከል ዕድሜያቸው ከ19 እስከ 64 የሚገኙ ሰዎች በየዕለቱ 700 ሚሊ ግራም ካልሺየም መውሰድ ይኖርባቸዋል።
ሌላው ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ ካፌይን ኩላሊታችን ውሃን የሚያጣራበት እና የሚያስወግድበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ነው።
በዚህም የተነሳ የሚሸኑበትን ፍጥነት ሊጨምር ይችላል።
"ይህም በውሃ ውስጥ በቀላሉ የሚሟሙ ቫይታሚኖችን (እንደ ቫይታሚን ቢ ያሉ) እንዲሁም እንደ አይረን እና ካልሺየም ያሉ ንጥረ ነገሮችን ቶሎ ከሰውነታችን እንዲወገዱ ሊያደርግ ይችላል" ይላሉ ሆ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቫይታሚን ቢ
"ቡና በኩላሊት አሠራር እና የንጥረ ነገሮች ውህደት ላይ ተጽዕኖ ስላለው፣ ብዙ ቡና መጠጣት (በቀን አራት እና ከዚያ በላይ ስኒ) ፈሳሽ ቶሎ ቶሎ ከሰውነታችን እንዲወጣ ያደርጋል።
"እንዲሁም በዚያ የተነሳ በውሃ ውስጥ በቀላሉ የሚሟሙ ቪታሚኖች፣ ቪታሚን ቢን ጨምሮ ከሰውነታችን ውስጥ በቀላሉ ያወጣሉ" ይላሉ ሩአኒ።
ቫይታሚን ቢ በውሃ ውስጥ የሚሟማ በመሆኑ በሰውነታችን ውስጥ አይከማችም፤ የትኛውም ከሚፈለገው በላይ የሆነ ቫይታሚን ቢ በሽንት መልክ ይወገዳል።
የጤና ባለሙያዎች በፕሮባዮቲክ የበለፀጉ፣ እንደ ኪሚቺ ያሉ ምግቦችን ቡና እየጠጣን ልንመገባቸው አይገባም ሲሉ ይመክራሉ።
ፕሮባዮቲክስ ለምግብ መፈጨት ሥርዓት ጤናማነት ጠቃሚ የሆኑ ሕያው ባክቴሪያዎች ናቸው።
ይሁን እንጂ ፕሮባዮቲክ የያዙ መድኃኒቶችን ወይንም እንደ እርጎ እና ኪሚቺ ያሉ በፕሮባዮቲክ የበለፀጉ ምግቦችን የሚወስዱ ከሆነ ከትኩስ ቡና ጋር መውሰድ አይኖርብዎትም።
"በብሮባዮቲክ ውስጥ የሚገኘው ሕያው ባክቴሪያ ለሙቀት ስሱ በመሆኑ ለከፍተኛ ሙቀት፣ እንደ ትኩስ ቡና ላሉ፣ የምናጋልጣቸው ከሆነ በጨጓራ እና አንጀታችን ውስጥ በሕይወት የመቆየት ዕድላቸውን ይቀንሰዋል። በዚህም የተነሳ ውጤታማነታቸው ይቀንሰል" ይላሉ ሩኒ።
ቡናን በሻይ መተካት አዋጭ ነው?
ቡና እርግፍ አድርገው ትተው ሻይ ለመጠጣት የሚወስኑ ከሆነ አንዳንድ የተነሱት ጠቃሚ ነጥቦች ለሻይም እንደሚሠሩ ልብ ማለት ተገቢ ነው።
"በሻይ ውስጥ ያለው ፖሊፌኖልስ በንጥረ ነገሮች ላይ ያለው ተጽዕኖ ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ንጥረ ነገሮች ወደ ሰውነትዎ የሚዋሃዱበት መንገድ ግድ የሚልዎ ከሆነ ሻይ የሚወስዱበትን ሰዓት ልብ ሊሉ ይገባል" ይላሉ ሆ።












