ጉግል በቱርክ የመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት 10 ሚሊዮን ሰዎችን ማስጠንቀቅ አለመቻሉን አመነ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ጉግል እአአ በ2023 በቱርክ በተከሰተው አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቱ ሰዎችን በትክክል ማስጠንቀቁ እንዳልቻለ አመነ።
በመሬት መንቀጥቀጡ ማዕከል አቅራቢያ የነበሩ 10 ሚሊዮን ሰዎች የጉግልን ጠንካራ ማንቂያ መቀበል ይችሉ ነበር ተብሏል።
ይህም ደህነንነቱ ወደ ተጠበቀ ስፍራ እንዲሄዱ እስከ 35 ሰከንድ ድረስ ጊዜ ይሰጣቸው ነበር።
ይልቁንም መጀመርያ ለተከሰተው እና 7.8 በሬክተር ስኬል ለተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ 469 ሰዎች ብቻ "እርምጃ ይውሰዱ" የሚል ማስጠንቀቂያ ተልኮላቸዋል።
ጉግል ለቢቢሲ እንደገለጸው ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ዝቅተኛ ደረጃ ማስጠንቀቂያ የተላከላቸው ሲሆን ይህም ለ"ቀላል ርዕደ መሬት" ተብሎ የተነደፈ ሲሆን ተጠቃሚዎችን እንደ ክብደቱ መጠን በተመሳሳይ መንገድ አያስጠነቅቅም።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ቀደም ሲል ስርዓቱ "ጥሩ አፈጻጸም እንዳለው" ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።
ስርዓቱ የሚሰራው በቱርክ ካሉ 70 በመቶ በላይ በሚሆኑት የአንድሮይድ ስልኮች ላይ ነው።
እአአ የካቲት 6/2023 ቱርክ በምዕራብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል በተከሰቱ ሁለት ርዕደ መሬቶች ስትናጥ 55,000 ሰዎች ሲሞቱ ከ100,000 በላይ ደግሞ ተጎድተዋል።
በመሬት መንቀጥቀጡ ወቅት በርካቶች ተኝተው ስለነበር ሕንጻዎች በላያቸው ላይ ተደርምሶባቸዋል።
የጉግል ቅድመ ማስጠንቀቅያ ስርዓት በወቅቱ በሥራ ላይ የነበረ ቢሆንም ርዕደ መሬቱ የነበረውን ጥንካሬ ዝቅ አድርጎ ገምቶታል።
"ከእያንዳንዱ የመሬት መንቀጥቀጥ በተማርነው መሰረት ስርዓቱን ማሻሻላችንን እንቀጥላለን" ሲሉ የጉግል ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
እንዴት ነው የሚሰራው?
አንድሮይድ የመሬት መንቀጥቀጥ ማስጠንቀቂያ (AEA) የሚል ስያሜ የተሰጠው የጉግል ሥርዓት፣ የአንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተምን የሚጠቀሙ በርካታ ስልኮችን እንቅስቃሴ በመከታተል ርዕደ መሬትን ይለያል።
የመሬት መንቀጥቀጦች በአንፃራዊነት በዝግታ በመሬት ውስጥ ስለሚንቀሳቀሱ ማስጠንቀቂያ ሊላክ ይችላል።
የጉግል በጣም አሳሳቢው ማስጠንቀቂያ በተጠቃሚው ስልክ ላይ ጮክ ያለ "እርምጃ ውሰድ" የሚል የማንቂያ ደወል ያሰማል።
ምንም እንኳ የግለሰቡ ስልክ ሴቲንግ አትረብሸኝ (Do Not Disturb) ላይ እንኳ ቢሆን ያንን አልፎ ስክሪኑን በመቆጣጠር መልዕክቱን ያስተላልፋል።
የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ጠንከር ያለ መንቀጥቀጥ እንደሚከሰት ሲታወቅ መላክ ያለበት ይህ ማስጠንቀቂያ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የአንድሮይድ የመሬት መንቀጥቀጥ ማስጠንቀቅያ፣ ቀላል ርዕደ መሬት ሲከሰት ለተጠቃሚዎች ለማሳወቅ የተነደፈ "ተጠንቀቁ" የሚል ማስጠንቀቅያም አለው።
ይህ ሴቲንጉ 'አትረብሸኝ' ላይ ያለን ስልክ አልፎ አይሰማም።
የቱርክ ርዕደ መሬት የተከሰተው አብዛኞቹ ተኝተው በነበረበት ወቅት፣ ከለሊቱ 10፡17 ላይ ስለነበር 'እርምጃ ውሰዱ' የሚለው ማንቂያ በጣም አስፈላጊ ነበር።
ምክንያቱም ቱርካውያኑን ሊቀሰቅሳቸው እና ከአደጋ ሊታደጋቸው የሚችለው ይህ ከባድ የማንቂያ ደወል ብቻ ነበር።
ከመሬት መንቀጥቀጡ በኋላ ባሉት ወራት ውስጥ ቢቢሲ ይህ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸውን ተጠቃሚዎችን ማነጋገር ፈልጎ ነበር ።
በመጀመሪያ ዓላማው የቴክኖሎጂውን ውጤታማነት ለማሳየት ነበር።
ነገር ግን በወራት ጊዜ ውስጥ በመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተባቸው የዞን ከተሞች እና አካባቢዎች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎችን ብንናነጋግርም፣ የመሬት መንቀጥቀጡ ከመከሰቱ በፊት 'እርምጃ ውሰድ' የሚል ማንቂያ የደረሰው ሰው ማግኘት አልቻልንም።
ይህንኑ ግኝቶቻችንን በዚያው ዓመት መጨረሻ ላይ አትመናል።
'ቀርነቶች'
የጉግል ተመራማሪዎች በሳይንስ ጆርናል ላይ "አልጎሪዝሙ ላይ የተገኙ ቀርነቶች" (Limitations) በሚል ምን ስህተት እንደተፈጠረ በዝርዝር ጽፈዋል።
ስርዓቱ የመጀመሪያውን የመሬት መንቀጥቀጥ፣ በ4.5 እና 4.9 መካከል ያለ መንቀጥቀጥ ነው ብሎ የተነበየ ቢሆንም በወቅቱ ግን በትክክል ርዕደ መሬቱ በሬክተር ስኬል 7.8 ሆኖ ተመዝግቧል።
በዕለቱ ለሁለተኛ ጊዜ ትልቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰትም እንዲሁ ዝቅተኛ ግምት የተሰጠው ሲሆን፣ ስርዓቱ በዚህ ጊዜ ለ 8,158 ስልኮች 'እርምጃ ይውሰዱ' የሚል ማንቂያዎችን ሲልክ፣ ከ 4 ሚሊዮን በታች ለሆኑ ተጠቃሚዎች ደግሞ የ ተጠንቀቁ ማንቂያዎችን ልኳል።
ከመሬት መንቀጥቀጡ በኋላ የጉግል ተመራማሪዎች አልጎሪዝሙን ቀይረው የመጀመሪያውን የመሬት መንቀጥቀጥ እንደገና አስመስለው ሞክረውታል።
በዚህ ጊዜ ስርዓቱ በጣም ተጋላጭ ለሆኑት 10 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እርምጃ ይውሰዱ የሚል የማንቂያ ጥሪዎችን መላክ ችሏል።
በተጨማሪም ከአካባቢው ርቀው ለሚኖሩ 67 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች፣ ተጠንቀቁ የሚል ማንቂያዎችን ማደራጀት ችሏል።
ጉግል ለቢቢሲ እንደተናገረው "እያንዳንዱ የመሬት መንቀጥቀጥ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶች ተመሳሳይ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ትላልቅ የመሬት መንቀጥቀጦችን ለመለየት አልጎሪዝሙን ማስተካከል ያስፈልጋል" ብሏል።
ነገር ግን በኮሎራዶ የማዕድን ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ኤልዛቤት ሬዲ ይህን መረጃ ለማግኘት ከሁለት ዓመት በላይ መፍጀቱ አሳሳቢ ነው ይላሉ።
"ይህን ያህል ጊዜ በመውሰዱ በጣም ተበሳጭቻለሁ" ብለዋል።
"ስለ አንድ ትንሽ ክስተት እየተነጋገርን አይደለም፤ ሰዎች ሞተዋል፤ እና እኛ በምንፈልገው መንገድ የዚህን ማስጠንቀቂያ አፈጻጸም አላየንም።"
ጉግል ሥርዓቱ አጋዥ እንጂ የአገራዊ ስርዓቶች ምትክ አይደለም ብሏል።
ሆኖም አንዳንድ ሳይንቲስቶች አገሮች ሙሉ በሙሉ ባልተሞከረ ቴክኖሎጂ ላይ እምነት እየጣሉ ነው ብለው ይሰጋሉ።
የፓሲፊክ ሰሜናዊ ምዕራብ ሴይስሚክ ኔትወርክ ዳይሬክተር ሃሮልድ ቶቢን ለቢቢሲ፤ "ምን ያህል በጥሩ ሁኔታ እንደሚሰራ በጣም ግልፅ መሆን ፍፁም ወሳኝ ነው ብዬ አስባለሁ።አንዳንድ ቦታዎች ጉግል እየሠራው ስለሆነ የራሳቸውን ስርዓት ላለመፍጠር ይወስናሉ?" ሲሉ ጠይቀዋል።
የጉግል ተመራማሪዎች የድህረ ክስተት ትንተና ስርዓቱን በተሻለ ሁኔታ አሻሽሏል፤ እና የአንድሮይድ ቅድመ ማስጠንቀቅያ በ 98 አገሮች ውስጥ ማንቂያዎችን ልኳል።
ቢቢሲ ጉግልን በጎርጎሮሳዊው 2025 በምያንማር በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት እንዴት የቅድመ ማስጠንቀቅያው እንደሰራ ቢጠይቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።















