አሜሪካውያን በገና እና በአዲስ ዓመት ዋዜማ በከባድ የአየር ሁኔታ እየተፈተኑ ነው

ልጁን አቅፎ በበረዶ በተሸፈነ መንገድ ላይ የሚሄድ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከፈረንጆች ገና እና ከአዲስ ዓመት መባቻ በፊት ባሉት ቀናት በአሜሪካ ከተከሰተው ከባድ ቅዝቃዜ እና የክረምት ወጀብ ጋር በተያያዘ ቢያንስ 12 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ።

በረዷማው እና ከፍተኛ ቅዝቃዜን የያዘው ወጀብ 200 ሚሊዮን በሚሆኑ አሜሪካውያን የዕለት ከዕለት ሕይወት እና እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖን አሳድሯል።

በዚህም ሳቢያ ከ1.5 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የተቋረጠባቸው ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የአውሮፕላን በረራዎች አርብ ዕለት ተሰርዘዋል።

ይህ ከባድ የቅዝቃዜ ወጀብ ከአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት እስከ ካናዳዋ ኩቤክ የሚዘልቅ 3,200 ኪሎ ሜትሮችን በሚሸፍን ቦታ ላይ የተከሰተ ነው።

የአከባቢ አየር ግፊት ሲቀንስ የሚከሰተው ከፍተኛ አውሎ ንፋስ [ቦምብ ሳይክሎን] በአሜሪካ እና በካናዳ ድንበር ላይ ባለው የታላላቅ ሐይቆች አካባቢ ከፍተኛ እና በረዶ የቀላቀለ ንፋስን አስከትሏል።

ከአሜሪካ በተጨማሪ ይህ ከባድ የአየር ሁኔታ በካናዳ የኦንቶሪዮ እና የኩቤክ ግዛቶች ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ አድርጓቸዋል።

እንዲሁም የተቀሩት የካናዳ አካባቢዎች በከባድ ቅዝቃዜ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ከባድ የክረትም ወጀብ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

የአሜሪካ ብሔራዊ የአየር ንብረት አገልግሎት አርብ ዕለት ያወጣው የአየር ሁኔታ አመላካች መረጃ፣ ተቋሙ አስካሁን ካወጣቸው “ከፍተኛው የክረምት ማስጠንቀቂያ እና ምክር” መካከል አንዱ እንደሆነ ተነግሯል።

ኤልክ ፓርክ በተሰኘችው የአሜሪካ አነስተኛ ከተማ የቅዝቃዜው መጠን ከዜሮ በታች 45 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የደረሰ ሲሆን የሚችጋን ቅዝቃዜ ደግሞ ከታች ወርዷል።

ቅዝቃዜው አርብ ዕለት ከዜሮ በታች 17 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ምሽት ላይ አካባቢው በበረዶ ተሸፍኖ ነበር።

በበረዶ የተሸፈኑ እንስሳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢቢ ያነጋገራት ኤሚሊ የተባለች የመጠጥ ቤት ሠራተኛ “በጣም ቀዝቃዛ ነው። አስቸጋሪ ጊዜ እያሳለፍን ነው” ብላለች።

በደቡባዊ ዳኮታ ግዛት ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ነዳጅ ስላለቀባቸው ሙቀት ለማግኘት ሲሉ ልብሶችን በእሳት እያነደዱ መሆናቸውን የማኅበረሰቡ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

በፔንስለቬኒያ እና ሚችጋን ከፍተኛ በረዶ ሊጥል እንደሚችል ትንብያ ተሰጥቷል። በተመሳሳይ በቡፋሎ እና ኒው ዮርክም ከፍ ያለ መጠን ያለው በረዶ ይጥላል ተብሏል።

ብሔራዊው የአየር ተንበያ ተቋም እንዳለው ከስምንት ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች በከባዱ የክረምት ወጀብ ማስጠንቀቂያ ውስጥ ይቆያሉ።

በኒው ኢንግላንድ፣ በኒው ዮርክ እና በኒው ጀርሲ የባሕር ዳርቻዎች ላይ ጎርፍ ተከስቷል።

ቀላል አየር ሁኔታ የሚያስተናግዱት ሉዊዚያና፣ አላባማ፣ ፍሎሪዳ እና ጆርጂያ ጠንከር ያለ ቅዝቃዜ ሊያስተናግዱ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።

ከአየር ፀባዩ ጋር በተያያዘ እየተከሰተ ባለው የትራፊክ አደጋ ሞት እየተመዘገበ ነው። በኦሃዩ በተሽከርካሪዎች መካከል በተከሰተ አደጋ የሁለት አሽከርካሪዎች ሕይወት አልፏል።

በሚከፈለው ዝቅተኛ ገንዘብ ምክንያት ጎዳናዎች ላይ የተከማቸውን በረዶ የሚጠርጉ ተሽከርካሪዎች ሹፌሮች እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት በመላው አሜሪካ የጉዞ መስተጓጎል በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሷል።

በርካታ ሰዎች የፈረንጆችን ገና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር ጉዞ ለማድረግ በሚነሱበት በአሁኑ ወቅት፣ አርብ ዕለት ብቻ ከ5,600 በላይ በአሜሪካ ውስጥ የሚደረጉ በረራዎች መሰረዛቸውን፣ የአውሮፕላን ጉዞዎችን የሚከታተለው ፍላይትአዌር የተባለው ድረገጽ አመልክቷል።

በተጨማሪም አርብ ምሽት በመላዋ አሜሪካ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደተቋረጠባቸው ተነግሯል።

የአሜሪካ ብሔራዊ የአየር ንብረት አገልግሎት በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት በታሪክ ከፍተኛ የሚባለው የቅዝቃዜ መጠን ሊደረስበት ወይም ሊታለፍ ይችላል ብሏል።

ለአስርት ዓመታት ከፍተኛ ተብለው የተመዘገቡ የቅዝቃዜ መጠኖች በዚህ ክረምት ተደግመዋል።

በዴንቨር ኮሎራዶ የቅዝቃዜ መጠኑ እንደ አውሮፓውያኑ ከ1990ዎች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዜሮ በታች ወደ 4 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ወይም 24 ፋራናይት ባለፈው ሐሙስ ወርዷል።

ቢቢሲ ያነጋገረው የ34 ዓመቱ መነሻው ስኮትላንድ የሆነ እና አሁን በዴንቨር የሚኖር ሰው “በሕይወቴ ያየሁት ከባዱ ቅዝቃዜ ነው” ብሏል።

ዊቺታ ካንሳስ ከአውሮፓውያኑ 2000 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዜሮ በታች 32 ፋራናይት የሆነ ከባድ ቅዝቃዜ አዘል ንፋስ አስተናግዳለች።

በናሽቪል ቴኒሲ ከ26 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች ተመዝግቧል።

በካስፐር ዋዮሚንግ ደግሞ ባለፈው ማክሰኞ 32 ፋራህናይት የቅዝቃዜ መጠን በማስመዘገብ በታሪክ ከፍተኛውን ቅዝቃዜ አጋጥሟታል።