ስሙን ከኢትዮጵያ ያገኘው ጃማይካዊው አትሌት አሰፋ ፖል እና የበጎ አድራጎት ሥራው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጃማይካ አውሎ ነፋስ በቀላቀለ ከፍተኛ ዝናብ (Hurricane) መመታቷን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ሲሞቱ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ ነው።
በሄሪኬን መሊሳ ምክንያት በአብዛኛው ጃማይካ መብራት እና ውሃ ተቋርጧል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ ) እንዳለው የደረሰው ጉዳት 8.8 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።
ጃማይካ ከደረሰባት ጉዳት በቀጣይ ሦስት ዓመታት እንድታገግም በሚል አይኤምኤፍ 6.7 ቢሊዮን ዶላር መድቧል።
የዓለም ባንክ ደግሞ 150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብቷል።
የጃማይካ መንግሥት እንዳለው በተፈጥሮ አደጋው ምንክንያት ከአገር ውስጥ ምርት 41 በመቶ ጉዳት ደርሶበታል።
በመላው ዓለም የሚኖሩ ጃማይካውያን አገራቸውን ለማገዝ እየተረባረቡ ይገኛሉ። በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ታዋቂ ጃማይካውያን ገንዘብ ማሰባሰብን ጨምሮ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ተሰማርተዋል።
የታዋቂ የአጭር ርቀት አትሌቶች እና የሙዚቃ ባለሙያዎች አገር የሆነችው ካሪቢያን ውስጥ የምትገኘውን አገራቸውን እና ወገናቸውን ለመርዳት ጃማይካ ሁሉም እየጣረ ነው።
እንደ ሻጊ እና አይሻ ባሬት ያሉ ድምጻውያን የሙዚቃ ኮንሰርት በማዘጋጀት ድጋፍ ለማሰባሰብ እየሞከሩ ይገኛሉ።
በበጎ አድራት ሥራ እየተሳተፉ ከሚገኙ ታዋቂ ጃማይካውያን አንዱ በ100 ሜትር ሩጫ የሚታወቀው አትሌት አሰፋ ፖል አንዱ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2005 (በ9.77 ሰከንድ) እና በ2008 (9.74) በ100 ሜትር ሩጫ የዓለም ባለ ክብረ ወሰን ነበር። አሁን ከዓለም አቀፍ የሩጫ ውድድር የራቀው አትሌቱ የ100 ሜትር የሩጫ ውድድርን ከ10 ሰከንድ ባነሰ ጊዜ በማጠናቀቅ ዝነኛ ነው።
አሰፋ ፖል በ97 ውድድሮች የአንድ መቶ ሜትር ውድድርን ከ10 ሰከንድ በታች በመጨረስ ከየትኛውም አትሌት የላቀ ነው። እአአ በ2010 በቼክ ሪፐብሊክ ያስመዘገበው 9.07 ሰከንድ የዓለም ሪከርድ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፖል በትውልድ አገሩ ጃማይካ ሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ከቢቢሲ ኒውስዴይ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።
"በጣም ያሳዝናል። እንዲህ ያለ ነገር መከሰቱ ያሳዝናል። እንደዚህ ላለ ቀውስ ዝግጁ አልነበርንም" ብሏል።
አውሎ ነፋስ የቀላቀለው ከፍተኛ ዝናብ ሲነሳ አሰፋ በጃማይካ መዲና ኪንግስተን በሚገኘው ቤቱ ነበር። ኪንግስተን ከሌሎች የጃማይካ አካባቢዎች አንጻር ብዙም አልተጎዳችም።
አሰፋ ከቢቢሲ ኒውስዴይ ጋር ባደረገው ቃለ ምለልስ በአገሩ ስለደረሰው የተፈጥሮ አደጋ እና ተጎጂዎችን ለመርዳት እየተደረገ ካለው ጥረት በተጨማሪ የስሙ ጉዳይ ተነስቶ ነበረ።
አትሌቲክስ ስፖርት ኮከቡ አሰፋ ፖል በዚህ ወቅትም ስሙን ያገኘው ከኢትዮጵያ እንደሆነ እና ታሪኩን ተናግሯል።
"አጎቴ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጋር ስለተማረ ነው ስሜን አሰፋ ያለው" ብሏል። በተጨማሪም አብዛኞቹ ጃማይካውያን የሚወዷት ሻሸመኔን ገና እንዳልጎበኘም ጠቅሷል።
ስሙን ከኢትዮጵያ ያገኘው ጃማይካዊው አትሌት አሰፋ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ በጃማይካ ደሴት ያለው ሕይወት በሄሪኬን መሊሳ ምክንያት እንዳልነበረ ሆኗል።
"በዚያ ደሴት ላይ ሕይወት እየተለወጠ ነው። መብራት፣ ውሃ፣ ምግብ የሌላቸው ሰዎች አሉ" ይላል።
በጃማይካ የደረሰውን ቀውስ የሚያሳዩ ምሥሎች እና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች "ትክክለኛውን የጉዳት መጠን አያሳዩም" የሚለው አሰፋ "ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ነው" ብሏል።
"ቤቶች ከውሃ በታች ተውጠዋል። ልቤ በሐዘን ተሰብሯል። ጠንካራ ያልሆነ ሰው ይሄን አይቶ አለማልቀስ አይችልም።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ውድመቱ ልቡን እንደሰበረው የሚናገረው አትሌቱ "ቀውሱ ላይ ከማተኮር ይልቅ እርዳታ መስጠት ላይ ማተኮርን መርጫለሁ" ይላል።
"ልጆች እና እናቶችን ጨምሮ ለቀናት በአፈር የተለወሱ ሰዎች ማየት ያሳዝናል። እኔና ባለቤቴ ያየነውን ማመን ነው ያቃተን። ሰዎች ቤት፣ ውሃ እና መብራት ያስፈልጋቸዋል" ሲልም አክሏል።
የደረሰው ውድመት ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር ሰዎች ወደቀደመ ሕይወታቸው እስከሚመለሱ ድረስ ጊዜ እንደሚወስድ ይናገራል።
አትሌቱ ገንዘብ በማሰባሰብ እንዲሁም አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለተጎጂዎች በማድረስም እርዳታ እየሰጠ ይገኛል። በዌስትሞርላንግ ግዛት ለተጎጂዎች ቤት በመስጠት እና በቤት ግንባታ ላይ በመሳተፍም አግዟል።
አሰፋ ልደቱን ምክንያት በማድረግ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መንገድም ዘርግቷል።
"ባለፈው ሳምንት ሁለት ቤቶች ሰጥቻለሁ። በጥቂት ሳምንታት ወይም በወሩ ቤት እና በፀሐይ የሚሠራ መብራት መስጠት ብንችል ደስ ይለኛል" ይላል።
ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ልጆቻቸውን ይዘው በወዳጅ ዘመዶች ቤት ከመጠለል ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው ጠቅሶ፤ የሚያስጠልሏቸውም ሰዎች ግን ችግር ውስጥ እንደሆኑ ተናግሯል።
"ልጆች ይዘው ነው እየተንገላቱ ያሉት። ድጋፍ ሲሰጣቸው በደስታ ያለቅሳሉ" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"በዋነኛነት ሰዎች የሚፈልጉት ውሃ ነው" የሚለው አትሌቱ ምንም እንኳን ጃማይካ በውሃ የተከበበች ደሴት ብትሆንም "የጨው ውሃ ስለሆነ መጠጣት አይቻልም። ለመጠጥ እና ሰውነት ለመታጠብም ንጹሕ ውሃ ያስፈልጋል" ብሏል።
መንግሥት መሠታዊ አቅርቦትን ዳግመኛ ለመመለስ እየሠራ ቢሆንም መብራት እና ውሃ ለማግኘት ወራት ሊወስድ እንደሚችል ይናገራል።
ቤት የሰጣቸው ቤተሰቦች በደስታ ብዛት እንዳለቀሱ የሚናገረው አትሌቱ "በደስታ እንድሞላ አድርጎኛል። ባለቤቴም በደስታ ስታለቅስ ነበር" ብሏል።
እርዳታ ለማድረስ በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች ከሰማቸው ታሪኮች መካከል የስምንት ሰዎችን ሕይወት ያተረፈውን ሰው ታሪክ ጠቅሷል።
"ስምንት ሰዎችን በማዳኑ ጀግና እየተባለ ነበር። አረጋውያን እና ሕጻናትን ጨምሮ ሰዎቹን አዝሎ በማውጣት አድኗል። ነፋሱ የአንዱን ቤት ጣሪያ ሲያፈርሰው ወደ ሌላ ክፍል እየዞሩ ነበር። ሌላኛውም ክፍል ጣሪያው ሲነቀል ወደ ሌላ ቤት ዞረዋል።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሰፋ በአገሩ ያየውን ውድመት ማመን ስላቃተው "ፊልም ነው የሚመስለው" ሲል ነው የገለጸው።
"እንዲህ ያለ ነገር ያየሁት በፊልም ብቻ በው። እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ፣ ፈጽሞ አይቼም አላውቅም።"
እርዳታ የሰጣቸው ነፍስ ያወቁ ሕጻናት ደስተኛ እንደሆኑ ተናግሯል።
"እናት እና አባታቸው መጠለያ ስላገኙ እና እነሱም ቤት ስላገኙ በጣም ነው የተደሰቱት" ሲል ገልጿል።
አብዛኞቹ ቤቶች ክፉኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በውሃ እና በአፈር እንደተዋጡ አሰፋ ተመልክቷል።
"ሁሉም ሰው እርዳታ ቢሰጠን ደስ ይለናል። ደሴታችን ትንሽ ቢሆንም ጠንካራ ሰዎች ነን። እንዲህ ባለ ከባድ ጊዜ በመደጋገፍ ወደ ደሴታችን ደስታ እንዲመለስ እንፈልጋለን።"

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሰፋ ለልጆች ዳይፐር እና ምግብ ማቅረባቸው "እጅግ እንደሚያስደስተው" ይናገራል።
"ብዙ ሰው መርዳት እንደምችል ሳይ በራሴ ኮርቻለሁ። በሩጫ ሜዳ ላይ ሲደግፉኝ፣ ሲኮሩብኝ እና ሲያበረታቱኝ የነበሩት እነዚህ ሰዎች ናቸው። ወገኖቼ ጃማይካውያንን ለመርዳት የበለጠ እንድሠራ ነው ያነሳሳኝ" ሲልም አክሏል።
በሄሪኬን መሊሳ ምክንያት 150 ሺህ ቤቶች ገደማ መውደማቸው ተገልጿል። ጃማይካ መልሳ እንድታገግም ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያሻ አትሌቱ ተናግሯል።
"ሁሉም ሰው ወደ ቤቱ እስከሚመለስ፣ ሁሉም ሰው ውሃ እና መብራት እስከሚያገኝ ድረስ እርዳታው መቆም የለበትም።"















