ጃማይካ ወንጀልን የሚያሞግስ ይዘት አለው ያለችውን ሙዚቃ አገደች

በመድረክስሙ “ዲ ጂኒየስ” በመባል የሚታወቀው እና ሙዚቃው የታገደበት የግራሚ አሸናፊው ሙዚቀኛ ማክግሪጎር

የፎቶው ባለመብት, TWITTER

የጃማይካ ብሮድካስት ባለሥልጣን አደንዛዥ ዕጽን እና የጦር መሣሪያን ጨምሮ "ሕገ ወጥ ድርጊቶችን የሚያሞግሱ" ይዘቶች አሏቸው የተባሉ ሙዚቃዎች እንዳይተላለፉ አገደ።

በጃማይካ የወጣው አዲስ ሕግ የቴሌቪዥን እና የራዲዮ ሙዚቃን ጨምሮ የተለያዩ "ሕገ ወጥ" ይዘቶችን ማስተዋወቅ እንደማይችሉ መደንገጉን ተከትሎ ነው ባለሥልጣኑ እርምጃውን የወሰደው።

ማጭበርበር፣ አደንዛዥ ዕጽ መጠቀም እና የጦር መሣሪያን በሕገ ወጥ መንገድ መጠቀምን "ማስተዋወቅን" ሕጉ አግዷል።

አንዳንድ አርቲስቶች እገዳው ከልክ በላይ የጠበቀ ነው ሲሉ የተቹ ሲሆን፤ ጥበብ የሕይወት ነፀብራቅ መሆኑን ከግምት ያልከተተ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።

ወንጀል በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣባት ጃማይካ ባለፈው ዓመት በደቡብ አሜሪካ እና ካሪቢያን አገራት ውስጥ ከፍተኛ የግድያ መጠን ከተመዘገበባቸው አገራት አንዷ ነች።

የአገሪቱ የብሮድካስት ባለሥልጣን ሕገ ወጥ ተግባራትን የሚያወድሱ ዘፈኖችን ለማሰራጨት የሕዝብ መገናኛ ብዙኃንን መጠቀም "ወንጀል የጃማይካ ባህል እና በማኅበረሰቡ ውስጥም ተቀባይነት ያለው ባህሪ ነው" የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲሰርጽ ሊያደርግ ይችላል ሲል ገልጿል።

መገናኛ ብዙኃኑን "ለማጽዳት" በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዓይነት "ሕገ ወጥ ወይም የወንጀል ድርጊቶች" መከልከላቸውን ባለሥልጣኑ ገልጿል።

ይህንን ሕግ ለማክበርም መገናኛ ብዙኃኑ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ሲልም አስታውቋል።

አፀያፊ ይዘት በወጣቶች መካከል የወንጀል ድርጊትን መደበኛ ያደርገዋል የሚለው ስጋት ለለውጦቹ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

አንዳንድ የጃማይካ አርቲስቶች እርምጃውን መተቸታቸውን ቀጥለዋል።

"አርቲስቶች በዙሪያቸው ስለሚያዩት ነገር እንዳይዘፍኑ መከልከል አይቻልም" ሲል የሙዚቃ ማናጀር እና ፕሮዲዩሰር የሆነው ሮሜይች በኢንስታግራም ገጹ ላይ ተናግሯል።

"ጃማይካ ልጆች ያሏት ብቸኛዋ አገር ናት? እነዚሁ ልጆች ተመሳሳይ ዘፈኖችን ከሌላ ቦታ መስማት ይችላሉ" ሲልም ሞግቷል።

በመድረክ ስሙ “ዲ ጂኒየስ” በመባል የሚታወቀው እና ሙዚቃው የታገደበት የግራሚ አሸናፊው ሙዚቀኛ ማክግሪጎር የተሰማውን ንዴት በትዊተር ገጹ ላይ አጋርቷል።

"ጥሩ! ወንጀል እና ጥቃት በአስማታዊ ሁኔታ አሁን ይቆማሉ" ሲል የባለሥልጣኑን ውሳኔ ተችቷል። አክሎም ወጣቶች በራዲዮ ሳይሆን በበይነ መረብ የበለጠ ሙዚቃን እንደሚሰሙም አመልክቷል።

በጃማይካ አንድ ሙዚቃ ሲታገድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። እአአ በ2009 ወሲብን፣ ጥቃትን፣ ግድያን ወይም የጦር መሣሪያን የሚያሞግሱ ሙዚቃዎች ታግደው ነበር።

የብሮድካስት ባለሥልጣኑ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መከበር ይገባዋል ያለ ሲሆን፤ ነገር ግን ወንጀለኝነትን የሚያበረታቱ እና ኃላፊነት የጎደላቸው ይዘቶች መቆም አለባቸው ሲል ገልጿል።