ኒኪ ሄሊ ዕጩ ፕሬዝዳንት ለመሆን በዋሽንግተን በተደረገ ምርጫ በትራምፕ ላይ ድል አገኙ

ኒኪ ሄሊይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኒኪ ሄሊይ

የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ለመሆን ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እየተፎካከሩ ያሉት ኒኪ ሄሊ በዋሽንግተን በተካሄደው የውክልና ምርጫ ትራምፕን አሸነፉ።

ባለፉት ጥቂት ወራት የፓርቲውን ውክልና ለማግኘት እየተደረገ ባለው ምርጫ ትራምፕ አስካሁን ሲያሸንፉ የቆዩ ሲሆን፣ የዋሽንግተኑ ውጤት ለሄሊ የመጀመሪያው ድል ነው።

ኒኪ ሄሊ በአሜሪካ ታሪክ በሪፐብሊካን ፓርቲ የመጀመሪያ ዙር የዕጩነት ምርጫ ሂደት በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ሴት ሆነዋል።

ነገር ግን አስካሁን በተካሄዱት የውክልና ምርጫዎች ትራምፕ ሄሊን በሰፊ ልዩነት እየመሩ በመሆናቸው በሚመጣው ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር እንደሚፎካካሩ ይጠበቃል።

ኒኪ ሄሊ በዋሽንግተኑ ምርጫ በማሸነፋቸው 19 የሪፐብሊካን ፓርቲ የውክልና ድምጾችን ማግኘት ቢችሉም፣ አስካሁን 247 ድምጽ ካገኙት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የሚቀራረብ አይደለም።

በዋሽንግተኑ ምርጫ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደር የሆኑት ሄሊ በ62.9 በመቶ ድምጽ ሲያሸንፉ፣ ትራምፕ 33.2 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።

የዋሽንግተን አካባቢ የፓርቲ ባለሥልጣናት 2,035 የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች በውክልና ምርጫው ተሳታፊ እንደነበሩ መናገራቸውን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።

የሄሊ ምርጫ ዘመቻ ቃል አቀባይ ኦሊቪያ ፔሬዝ-ኩባስ “የመንግሥት ኃላፊነቱን አለመወጣት በቅርበት የሚያውቁት የዋሽንግተን ሪፐብሊካኖች ትራምፕን እና ያስከተሉትን ቀውስ አለመቀበላቸውን ማሳየታቸው የሚያስደንቅ አይደለም” ብለዋል።

የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ውጤቱ መገለጹን ተከትሎ የሄሊን አሸናፊነት አጣጥለውታል።

ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ለመሆን በየግዛቱ የተደረጉትን ምርጫዎች አስካሁን አሸንፈው ነገ ማክሰኞ ለሚካሄደው ወሳኝ ምርጫ ተዘጋጅተዋል።

ምንም እንኳን አስካሁን በተካሄዱት የውክልና ምርጫዎች ኒኪ ሄሊ በዶናልድ ትራምፕ የበላይነት ቢወሰድባቸውም፣ ነገ ማክሰኞ እስከሚካሄደው ወሳኝ የድምጽ አሰጣጥ ድረስ ዕጩ ለመሆን እንደሚወዳደሩ አሳውቀዋል።

በሚመጣው ዓመት ኅዳር በሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጆ ባይደን ለሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን ዲሞክራቶችን የሚወክሉ ይሆናል።

በሪፐብሊካኖች በኩል ዕጩ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመቅረብ ዶናልድ ትራምፕ እና ኒኪ ሄሊ እየተፎካከሩ ቢሆንም አስካሁን ባለው ውጤት ትራምፕ በሰፊ ልዩነት የበላይነት ይዘዋል።