ቶተነሃም እና አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ተለያዩ

አንቶኒዮ ኮንቴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አንቶኒዮ ኮንቴ

አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ እና ቶተነሃም ከ16 ወራት በኋላ በስምምነት መለያየታቸውን ክለቡ አስታወቀ።

ኮንቴ በቶተነሃም የነበራቸው ቆይታ የተጠናቀቀው ከቀናት በፊት የክለቡን አስተዳደር እና የቡድኑን ተጫዋቾች የወረፈ ንግግር ካሰሙ በኋላ ነው።

ኮንቴ ከአንድ ሳምንት በፊት በነበረው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ቶተነሃም በሳውዝአምፕተን ሜዳ 3 አቻ ከተለያየ በኋላ ተጫዋቾቼ “ራስ ወዳድ” ናቸው ብለው ነበር።

በቶተንሃም የውጤት ድርቅ እጅግ የተበሳጩት አሠልጣኙ “ቡድኑ አሠልጣኝ ቢቀይርም ለውጥ አያመጣም” ብለው ነበር።

ቶተነሃም በአሁኑ ወቅት በፕሪሚየር ሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ከሌሎች ውድድሮች ተሸንፎ መውጣቱ ይታወቃል።ቶተነሃም ከቻምፒየንስ ሊጉ በኤሲ ሚላን፣ ከኤፍ ኤ ዋንጫ ደግሞ በቻምፒየንሺፕ ክለብ ሼፊልድ ዩናይትድ ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል።

የኮንቴን መሰናበት ይፋ ያደረገው ክለቡ፣ ምክትል አሰልጣኝ ክርስቲያን ስቴሊኒ በቀድሞ አማካይ ተጫዋቹ ራይን ሜሰን ድጋፍ እስከ የውድድሩ ዘመን ፍጻሜ ድረስ የቡድኑ አሰልጣኝ ይሆናሉ ብሏል።

የኮንቴ መሰናበት ስፐርስ እአአ 2019 ማሪሲዮ ፖቼቲኖን ካሰናበት በኋላ ቋሚ አሰልጣኝ ፍለጋ ሲወጣ ይህ ለ4ኛ ጊዜ መሆኑ ነው።

ኮንቴ በቶተነሃም አሰልጣኝነታቸው ቡድናቸው 3-1 ከመምራት 3 አቻ ከተለያየ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “ይህ የቶተንሃም ታሪክ ነው - 20 ዓመት ሙሉ አንድ ባለቤት ነው ያለው፤ ነገር ግን አንድም ዋንጫ አንስቶ አያውቅም። ለምን?” ሲሉ በብስጭት ጠይቀው ነበር።

“እስካሁን ድረስ ያለውን ነገር መደበቅ እፈልግ ነበር። አሁን ግን በቃኝ። እደግመዋለሁ፤ ዛሬ ያየሁትን ነገር ማየት አልፈልግም፤ ምክንያቱም በደጋፊዎቻችን ዘንድ ተቀባይነት የለውም።”

የክለቡ ሊቀ መንበር ዳኔኤል ሌቪ የክለቡ ዕቅድ በቀሩት 10 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በቂ ነጥብ ሰብስቦ በቀጣይ ዓመት የቻምፒየንስ ሊግ ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።