አሜሪካ የእርዳታ ገንዘብ የምታቆም ከሆነ የአንድ ሚሊዮን ህፃናት ሕይወት ሊያልፍ ይችላል ተባለ

በመላው ዓለም 500 ሚሊዮን ህፃናት ክትባት እንደሚያስፈልጋቸው ጋቪ ገልጿል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በመላው ዓለም 500 ሚሊዮን ህፃናት ክትባት እንደሚያስፈልጋቸው ጋቪ ገልጿል

አሜሪካ የገንዘብ ድጋፏን የምታቋርጥ ከሆነ መከላከል በሚቻል በሽታዎች አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናት ሕይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል ዓለም አቀፍ የጤና ተቋም አስጠንቅቋል።

በማደግ ላይ ላሉ አገራት ወሳኝ ክትባቶችን በማቅረብ የሚታወቀው ጋቪ የተባለው ድርጅት ኃላፎ ዶ/ር ሳኒያ ንሽጣር የአሜሪካ እርዳታ መቋረጥ "በዓለም አቀፍ የጤና ደኅንነት ላይ አስከፊ ተፅዕኖ" ይኖረዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኃላፊው ይህን ያሉት የድርጅቱ ሦስተኛ ለጋሽ አገር የሆነችው አሜሪካ ድጋፏን ለማቋረጥ መወጠኗን ኒው ዮርክ ፖስት መዘገቡን ተከትሎ ነው።

ጋቪ እስካሁን የእርዳታ መቋረጥ ማሳወቂያ ከአሜሪካ ያልደረሰው ሲሆን ለ2025 እንቅስቃሴው የሚሆን 300 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ እንዲሁም የረጅም ጊዜ እርዳታ ለማግኘት ከዋይት ሀውስ እና ከኮንግረስ ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ተናግረዋል።

አሜሪካ ለጋቪ እ.አ.አ ከ2026 እስከ 2030 ድረስ ለድርጅቱ 15 በመቶ ድርሻ ያለው 1.6 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታ ነበር።

ባለፈው ጥር ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በባህር ማዶ የምታደርገው ወጪ አሜሪካን ያስቀደመ እንደሚሆን በግልፅ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የልማት ዘርፍ በዓለም ዙሪያ የሰብዓዊ መርሀ-ግብሮች ላይ ትልቅ ተፅዕኖ በማምጣት ስሙ ይነሳል።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በአጭሩ ዶዥ እየተባለ በሚጠራው የኤለን መስክ ወጪ ቅነሳ መስሪያ ቤት በመጀመሪያ ኢላማ ውስጥ ከገቡት መሀል ሲሆን፤ በትራምፕ አስተዳደር የ90 ቀናት የእርዳታ እግድ ተጥሎበታል።

የጋቪ የገንዘብ አቅርቦት የሚቆም ከሆነ በመላው ዓለም ክትባት ከሚያስፈልጋቸው 500 ሚሊዮን ህፃናት ውስጥ75 ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናት ክትባት አያገኙም የሚሉት ኃላፊው፤ ይህም ማለት እንደ ፈንጣጣ፣ ቲቢ፣ የሳንባ ምች እና ፖሊዮ በመሰሉ መከላከል በሚቻል በሽታዎች ሞት ይከሰታል ብለዋል።

በሌላ አነጋገር መንግሥታት እና የጤና ኤጄንሲዎች ኢቦላ፣ ኮሌራ እና ኤምፖክስ የመሰሉ በሽታዎችን ለመከላከል እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ የክትባት ክምችታቸው ላይ ጠባሳ ያርፋል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድንም እርዳታ የሚቋረጥ ከሆነ ሊደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ በሚመለከት ከጋቪ ጋር ይስማማል።

የቡድኑ የአሜሪካየመርሃ-ግብር ኃላፊ ካሪ ቴቸር "የዚህ ፖለቲካዊ ውሳኔ ውጤት አስከፊ ይሆናል" ብለዋል።

የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ጋቪን ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ እና በዋነኛ መርኃ-ግብሮች የአሜሪካ እርዳታ መቋረጥ ባሳደረው ጫና ዙሪያ ከዋሽንግተን ባለስልጣናት ጋር እተነጋገረ መሆኑን ገልጿል።