የደቡብ አፍሪካ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ፆታዊ ጥቃትን የሚያወግዝ አገር አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲካሄድ ጠየቁ

ሰላማዊ ሰል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ ስለ ፆታዊ ጥቃት ሪፖርቶች አካቷል

የደቡብ አፍሪካ የሴቶች መብት ተሟጋች ተቋማት ፆታዊ ጥቃት አገር አቀፍ ቀውስ ተብሎ እንዲታወጅ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርጉ ነው።

አገር አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲካሄድ በይፋ ጥያቄ ያቀረቡት ተቋማቱ ንቅናቄውን የጀመሩት በማኅበራዊ ሚዲያ ነበር።

በሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃት በተባባሰባት ደቡብ አፍሪካ የቡድን 20 አገራት ጉባዔ ከመጀመሩ አስቀድሞ ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ ታቅዷል።

ንቅናቄውን እንዲወክል የተመረጠውን ወይን ጠጅ ቀለም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው መለያ በማድረግ ታዋቂ ሰዎች ድጋፋቸውን እያሳዩ ነው።

ወይን ጠጅ ቀለም ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል የሚደረግ ንቅናቄን የሚወክል ተደርጎ ይወሰዳል።

በከፍተኛ መጠን ፆታዊ ጥቃት ከሚደርስባቸው አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች።

በመላው ዓለም ካለው አማካይ አሐዝ በበለጠ በደቡብ አፍሪካ ሴቶች በአምስት እጥፍ እንደሚገደሉ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ይጠቁማል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እአአ በ2025 ከጥር እስከ መጋቢት 137 ሴቶች ሲገደሉ፤ ከ1,000 በላይ ሴቶች መደፈራቸውን የአገሪቱ የወንጀል አሐዝ ያሳያል።

ዛሬ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ሴቶች ከሥራ እና ከትምህርት ቀርተው እኩለ ቀን ላይ ለ15 ደቂቃ መሬት ላይ በመሆን በፆታዊ ጥቃት የተገደሉ ሴቶችን እንዲዘክሩ ተጠይቋል።

"ሐዘን እና ተቃውሞን" ለማሳየት ሴቶች ጥቁር እንዲለብሱም የንቅናቄው አዘጋጆች አሳስበዋል።

'the G20 Women's Shutdown' የሚል ስያሜ የተሰጠው ንቅናቄው የተዘጋጀው በዋናነት 'ውሜን ፎር ቼንጅ' በተባለው ስብስብ ነው።

መንግሥት ፆታዊ ጥቃትን በተመለከተ የሚወስደውን እርምጃ እንዲያጠናክር ለመጠየቅ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ፊርማቸውን አኑረዋል።

የአገሪቱ አደጋ መከላከል እና ቁጥጥር ተቋም ፆታዊ ጥቃትን ብሔራዊ ቀውስ ብሎ ለማወጅ አልፈቀደም። ከሕግ አንጻር ጥያቄው ያልተሟላ እንደሆነም ጠቅሷል።

የቡድን 20 አገራት ከጉባዔው በፊት ስለ ማኅበራዊ ጉዳዮች ውይይት ሲያደርጉ፤ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እአአ በ2019 አገሪቱ ፆታዊ ጥቃትን እና ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያን (femicide) አገር አቀፍ ቀውስ ብላ ማወጇን ተናግረዋል።

ሆኖም ግን እምብዛም ለውጥ እንዳልመጣ እና መንግሥት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባው የመብት ተሟጋቾች ገልጸዋል።

የውሜን ፎር ቼንጅ ቃል አቀባይ ካሜሮን ካሳምባላ እንደምትለው፤ "ብዙ ጥሩ የሆኑ ሕጎች እና አዋጆች" ቢወጡም መንግሥት "እየተገበራቸው አይደለም፤ ግልጽነትም ይጎድለዋል"።

"ፆታዊ ጥቃትን ባህላችን ውስጥ አስገብተነዋል። መንግሥት ተገቢውን እርምጃ ሲወስድ ነው ለውጥ ማየት የምንጀምረው። አገሪቱ ምን ዓይነት አቋም እንዳላት የሚወስነው መንግሥት ነው" ብላለች።

የግራሚ ተሸላሚዋ ድምጻዊት ታይላ ንቅናቄውን በመደገፍ ፊርማቸውን ካኖሩ መካከል አንዷ ናት።

ንቅናቄውን ለማጉላት ወይን ጠጅ ቀለም ያለው የልብ ቅርጽ፣ ልብስ እንዲሁም ጥፍር ቀለም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው የለጠፉም በርካቶች ናቸው።

"የወይን ጠጅ ንቅናቄ" ወይም purple movement" የሚል ስያሜ የተሰጠውም ለዚህ ነው።

አንድ ደቡብ አፍሪካዊ መምህርት ለቢቢሲ እንደገለጸችው፤ ወደ ጆሀንስበርግ ሄዳ የንቅናቄው ተሳታፊ ለመሆን ከሥራ እረፍት ወስዳለች።

ንቅናቄው የፆታዊ ጥቃትን "ለመቀነስ" አንድ እርምጃ እንደሆነ ታምናለች።

አንዳንድ ሴቶች በንቅናቄው ለመሳተፍ ሲጠይቁ ከአለቆቻቸው አወንታዊ ምላሽ አለማግኘታቸው ተገልጿል።

'ገርልስ ኦን ፋየር' የተባለ ንቅናቄ የጀመረችው ለኔት ኦክስሊ እንደምትለው ሴቶች መሣሪያ በመያዝ ራሳቸውን መከላከል አለባቸው።

በደቡብ አፍሪካ ራስን ለመከላከል ፈቃድ አውጥቶ መሣሪያ መግዛት ሕጋዊ ነው።

ለኔት በጀመረችው እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት አብዛኞቹ ሴቶች የተደፈሩ፣ ጥቃት የደረሰባቸው እንዲሁም የተዘረፉ ናቸው።

እአአ በ2020 ከተደፈረች በኋላ ንቅናቄውን የተቀላቀለችው ፕሩደንስ "ተወኝ ብዬ ጮህኩ፣ አለቀስኩ፣ ሊሰማኝ ግን አልፈቀደም" ትላለች።

ከተደፈረች በኋላ የተወሰደው የዘረ መል ናሙና ስለጠፋ ክሷ በፍርድ ቤት ውድቅ እንደተደረገም ትገልጻለች።

"ችግሩ የፖሊሶች ብቻ ሳይሆን አገር አቀፍ ነው" ትላለች ፕሩደንስ።

የንቅናቄው አባላት ሽጉጥ መተኮስ ቢማሩም "የመጨረሻ አማራጭ" ተደርጎ እንደሚወሰድ ለኔት ገልጻለች።

"ጉዳዩ ራስን በጥይት ስለመከላከል ብቻ አይደለም። ሴቶች ዝምታን አቁመው ስለራሳቸው ያላቸውን አመለካከት እንዲለውጡ እፈልጋለሁ። ትግሉን ባያሸንፉም ቢያንስ መታገል አለባቸው።"