ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል እና ጥቃት አድራሾችን ለመክሰስ የሚረዳው መተግበሪያ

መተግበሪያው ጥቃትን ለመከታተል ይውላል

የፎቶው ባለመብት, Grit

ደቡብ አፍሪካዊቷ ሌኖራ ቲማ በዘመዷ ላይ የደረሰው አሰቃቂ ጥቃት ሕይወቷን ቀይሮታል።

የሌኖራ ዘመድ የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር ሳለች ነበር የተገደለችው። ገና 19 ዓመቷ ነበር።

አስከሬኗ እአአ በ2020 በኬፕ ታውን በሚገኝ ድልድይ ሥር ተጥሎ ተገኘ።

ከዚህ ግድያ በኋላ ሌኖራ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን የሚከታተል መተግበሪያ ለመሥራት ወሰነች።

"በቴክኖሎጂ ዘርፍ ስለምሠራ ጥቃቶች ሲፈጸሙ አይቻለሁ። በገዛ ዘመዴ ላይ ግድያ ሲፈጸም ግን የተለየ ነው። ግድያው በደቡብ አፍሪካ እንደተለመደ ነገር ነው የተወሰደው" ትላለች።

የዘመዷ ግድያ ዜና እንኳን አልሆነም።

"በአገራችን የሚደርሰው ጥቃት በርካታ ከመሆኑ ብዛት ግድያዋ ዜና ለመሆን አልበቃም።"

ገዳዩ አልታየዘም። ሌኖራ የዘመዷ ግድያ በዝምታ መታለፉም አስቆጥቷታል።

ፆታዊ ጥቃት ላይ ያተኮረ መተግበሪያ ለመሥራት ቆርጣ የተነሳቸውም ለዚህ ነው።

'Gender Rights in Tech' ወይም 'Grit' የተባለው መተግበሪያ 'ዙሪ' የተባለች ቻትቦት አለችው።

ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል በአፍሪካ ከተሠሩ መተግበሪያዎች ግንባር ቀደሙ ነው።

"ለአፍሪካውያን የሚሆን አፍሪካዊ መተግበሪያ ነው" ስትል ሌኖራ ትገልጸዋለች።

ሌኖራ ዘመዷ ከተገደለች በኋላ መተግበሪያውን ለመሥራ ወስናለች

የፎቶው ባለመብት, Grit

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መተግበሪያው የተሠራው ስለ ፆታዊ ጥቃት መረጃ ለመሰብሰብ እና ለሴቶች ድጋፍ ለመስጠት ነው። ጥቃት አድራሾች ላይ ክስ ለመመሥረትም ይውላል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሠሩ ቻትቦቶች የሰዎችን ሚና መተካት የለባቸውም የሚሉ የፆታ መብት ተሟጋቾች ቢኖሩም፤ መተግበሪያው ፆታዊ ጥቃትን በመከላከል ረገድ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ያምናሉ።

ፆታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ከሥነ ልቦና ባለሙያዎች ድጋፍ ማግኘት አለባቸው።

ሌኖራ የኬፕ ታውን ነዋሪዎችን በማነጋገር ምን ዓይነት ጥቃት እንደሚፈጸም እና በምን መንገድ ድጋፍ መስጠት እንደምትችል ለመረዳት ሞክራለች።

ስልካቸውን እና ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም እንዴት ፆታዊ ጥቃት እንደሚከላከሉ ለመገንዘብ ከ800 በላይ ሰዎችን አነጋግራለች።

ዋነኛው ጥያቄዋ ለምን እርዳታ እንዲሰጣቸው አይጠይቁም? የሚለው ነው።

ሴቶች ፆታዊ ጥቃት ሲደርስባቸው መናገር ቢፈልጉም ለፖሊስ ለማሳወቅ አይፈቅዱም።

"አንዳንድ ሴቶች ፌስቡክ ላይ ይጽፋሉ። ጥቃት ያደረሰባቸውን ሰው 'ታግ' የሚያደርጉም አሉ። ሆኖም ግን የስም ማጥፋት ክስ ይከፈትባቸዋል" ትላለች ሌኖራ።

የደቡብ አፍሪካ አስተዳደራዊ መዋቅር ሴቶችን ከጥቃት መከላከል ካለመቻሉም ባሻገር ጥቃት ሲደርስባቸው እንዲናገሩ የሚያበረታታም አይደለም።

'ግሪት' መተግበሪያን ሞዚላ፣ ጌትስ ፋውንዴሽን እና ፓትሪክ መክገቨርን ፋውንዴሽን በገንዘብ ደግፈውታል።

በነጻ አገልግሎት የሚሰጠው መተግበሪው 13,000 ተጠቃሚዎች እንዳሉት ሌኖራ ትናገራለች።

ባለፈው የመስረከም ወር ብቻ 10,000 ሴቶች ድጋፍ ጠይቀዋል።

መተግበሪያው ሦስት ዋና ዋና ጥቅሞች ይሰጣል። በመጀመሪያ ደረጃ በፊት ገጹ ላይ እርዳታ መጠየቂያ ቁልፍ አለው።

አንዲት ሴት ይሄንን ቁልፍ ስትጫን የ20 ሰከንድ ድምጽ ይቀዳል። ከዚያም ሙያዊ እርዳታ ለሚሰጡ የግል ተቋማት ጥቆማ ያደርሳል።

በእነዚህ ተቋማት የሚሠራ ባለሙያ በአፋጣኝ ስልክ በመደወል ድጋፍ ይሰጣል አልያም ባለሙያዎችን ይልካል።

በተጨማሪም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ወደየትኛው መጠለያ መሄድ እንደሚችሉ ጥቆማ ይሰጣል።

ሌኖራ

የፎቶው ባለመብት, Grit

"ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች እንዲያምኑን እንፈልጋለን። መረጃ እንዲሰጡን ስንጠይቅ ቀላል እንዳልሆነ እንረዳለን" ትላለች።

ሁለተኛው የመተግበሪያው ክፍል 'ዘ ቮልት' ይባላል። ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች መረጃ የሚያከማቹበት ሲሆን በምሥጢራዊ ቁልፍ ይዘጋል።

መረጃው ክስ ሲመሠረት ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

ፎቶዎች፣ ስክሪንሾቶች፣ የድምጽ ቅጂዎች እና ሌሎችም ማስረጃዎች እንዳይጠፉ በምሥጢር ቆልፎ ማስቀመጥ ይቻላል።

"አንዳንዴ ሴቶች የደረሰባቸውን ጉዳት ፎቶ ያነሳሉ። የሚደርሷቸውን የዛቻ መልዕክቶችም ያስቀምጣሉ። እነዚህ በቀላሉ ሊጠፉ የሚችሉ ማስረጃዎች ናቸው" ስትል ሌኖራ ታስረዳለች።

በሦስተኛ ደረጃ፤ ዙሪ የተባለችው የመተግበሪያው ቻትቦች ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች ታደምጣለች፤ ትመክራለች፤ ተጨማሪ እርዳታ የሚያገኙበትን መንገድም ትጠቁማለች።

"መተግበሪያውን የሚጠቀሙ ሰዎችን የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች አሉ። እነዚህም- ቻትቦቱ የሴት ድምጽ ይኑረው ወይስ የወንድ? ድምጹ የሮቦት ይምሰል? ቻትቦቱ እንደ ጠበቃ ይሁን ወይስ እንደ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ? ቻትቦቱ እንደ ጋዜጠኛ ይሁን ወይስ እንደ ባለሥልጣን? የሚሉት ናቸው።"

አንዳንድ ተጠቃሚዎች ዙሪ 'እንደ አክስት ያለ ሚና' እንዲኖራት ይሻሉ። ታማኝ እና ድጋፍ ሰጪ እንድትሆን ይፈልጋሉ።

ቻትቦቷ አስፈሪ ወይም ፈራጅ እንዳትሆን በሚል 'የአክስት' ባህሪ እንድትላበስ እንደሚፈልግ ሌኖራ ትናገራለች።

ዙሪ የተሠራችው በዋናነት ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከል ቢሆንም ወንዶችም አግልግሎቷን እያገኙ ነው።

አንዳንድ ወንዶች እንዴት ብስጭትን መቆጣጠር እንደሚችሉ ከዙሪ ምክር ይጠይቃሉ። ጥቃት የደረሰባቸው ወንዶችም በግልጽ ከዙሪ ጋር ይነጋገራሉ።

ሌኖራ እንደምትለው፤ ብዙዎች በሰዎች ላለመገመት ሲሉ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር ማውራትን ይመርጣሉ።

ደቡብ አፍሪካ የከፋ ፆታዊ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል አንዷ እንደሆነች የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።

በሌሎች አገራት ሴቶች ላይ ከሚፈጸም ግድያ (femicide) የደቡብ አፍሪካ አምስት እጅ ይበልጣል።

እአአ ከ2015 እስከ 2020 በየቀኑ በአማካይ ሰባት ሴቶች እንደተገደሉ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ገልጿል።

ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል የምትሠራው ሊሳ ቬትን እንደምትለው፤ ቴክኖሎጂ ፆታዊ ጥቃትን ለማስቆም ጥቅም ላይ መዋል አለበት።

ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እንደ ብቸኛ አማራጭ መጠቀም ላይ ግን ጥያቄ ታነሳለች።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ድጋፍ ቢሰጥም የተሳሳተ ምክር ያቀረበባቸውም አጋጣሚዎች መኖራቸውን ትጠቅሳለች።

"ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሕጋዊ ምክር ሲሰጥ ያሰጋኛል። ጠቃሚ መረጃ መስጠት ቢችልም ውስብስብ ጉዳዮችን አይረዳም። ሰዎችንም አይተካም። ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ደኅንነት እንዲሰማቸው የሚያደርግ እና የሚያምኑት ሰው ያስፈልጋቸዋል" ትላለች ባለሙያዋ።

'ግሪት' መተግበሪያ በፈረንሳይ፣ ፓሪስ በተካሄደው ቴክኖሎጂ እና የፆታ ጥቃት ላይ ያተኮረ ውይይት ላይ ቀርቧል።

በውይይቱ የ31 አገራት መሪዎች ፆታዊ ጥቃት መከላከልን ዋነኛ የፖሊሲ ትኩረት አቅጣጫ ለማድረግ ተስማምተዋል።

በቻተም ሀውስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተመራማሪ ሔዘር ኸርበርት "ሰው ሠራሽ አስተውሎት የፆታ መድልዎን፣ ፆታዊ ጥቃትን፣ ፆተኛነትን እና እኩልነት ማጣትን ለመቅረፍ ይረዳል" ትላለች።

"የአንበሳውን ድርሻ የምንይዘው ግን ሰዎች ነን" ስትልም ታስረዳለች።

ሌኖራ እንደምትለው መተግበሪያዎች ሲሠሩም ይሁን ከተሠሩ በኋላ ያላቸው ተደራሽነት በቆዳ ቀለም እና በፆታ የመገደብ ዕድሉ ሰፊ ነው።

እአአ በ2018 የወጣው የወርልድ ኢኮኖሚክ ሪፎርም ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ 22% የሚሆኑት የሰው ሠራሽ ባለሙያዎች ሴቶች ናቸው።

"ሰው ሠራሽ አስተውሎት በተለምዶ የሚያስተጋባው የወንዶችን ድምጽ ነው። በዋናነት ደግሞ የነጭ ወንዶችን ድምጽ" ትላለች ሌኖራ።

"መተግበሪያ ፈጣሪዎች በብዛት ሴቶች እና በተለይም ጥቁር ሴቶች መሆን ያለባቸው ለዚህ ነው። እነዚህ ሴቶች ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እኩልነት ያልሰፈነበትን የዓለም ደቡባዊ ክፍል መወከልም አለባቸው። ቴክኖሎጂ የዓለምን እውነታ ማሳየት የሚችለው በዚያ መንገድ ነው።"