ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ኢትዮጵያ የመስፋፋት ፍላጎት የላትም" አሉ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የረመዳን ጾም መጀመርን በማስመልከት የካቲት 9/2018 ዓ.ም. በአረብኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕከት "ኢትዮጵያ የመስፋፋት ፍላጎት የላትም" አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ መልዕክታቸው ላይ ኢትዮጵያን "የታማኝነት የእውነት ምድር" ሲሉ የጠሯት ሲሆን "የጎረቤቶቿን ደህንነት አደጋ ላይ እንደማትጥል" ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ጦርነት ይቀሰቀሳል በሚል ውጥረት ባየለበት ወቅት ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት "የኅልውና ጉዳይ ነው" ስትል ከገለፀች ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሮ ወደ ቃላት ጦርነት አድጓል።

"እንደ እውነት ምድር ወራሽነታችን ለመላው ዓለም ማረጋገጥ የምንፈልገው ኢትዮጵያ መሬት የመውረር፣ የመስፋፋት ፍላጎት እንደሌላት እና የጎረቤቶቿን ደህንነት አደጋ ላይ እንደማትጥል ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውሃ ሃብታችንን ተጠቅሞ ለመልማት ያለን ፍላጎት "በምንም መልኩ የሌላውን ድርሻ የመቀነስ አይደለም" ሲሉ ለግብፅ ምላሽ በሚመስል መልኩ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስተዳደር እና የውሃ ሙሌት ላይ ለዓመታት ድርድር ሲያደርጉ ቢቆዩም ሁሉንም የሚያስማማ መቋጫ ላይ ሳይደርሱ ቀርተዋል።

አባይ ታላቅ "መለኮታዊ ስጦታ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ "ከግጭት መድረክ ይልቅ የትብብር ድልድይ" ይሆናል በማለት ሁሉም ከዚህ ወንዝ "በፍትህ እና እኩልነት መጠቀም አለበት" ብለዋል።

ግብፅ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በመቃወም ለዓመታት ብሔራዊ ጥቅሜ ይነካል የሚል ስጋቷን እስከ ዋይት ሐውስ ድረስ አስተጋብታለች።

ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ታማኝ ሆና ትኖራለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ማንንም አትጎዳም፤ በኢፍትሃዊነት ፊት በዝምታም አትቀመጥም፤ የማንንም ድርሻ ለማሳነስ አትፈልግም" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ከ130 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝቧን ከድህነትን ለማውጣት ትግል እያደረገች መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "አካባቢዋን የምትመለከተው በውህደት እንጂ በመስፋፋት አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

"ደህንነቱ የተጠበቀ እና ፍትሃዊ የባህር ዳርቻ ለማግኘት ያለን ፍላጎት የሰብዓዊ ፍላጎቶችን እና የሕዝብ ቁጥር መጨመርን የሚያገለግል ፕሮጀክት የማጠናቀቅ ጥሪ ነው።"

አክለውም የኢትዮጵያ ባሕር በር የማግኘት እንቅስቃሴ "በሌላ ዕይታ የጎረቤቶችን ሉዓላዊነት የማይጋፋና የሌሎችን ጥቅም የማይጎዳ የአጋርነት ግብዣ ነው" ብለዋል።

የሰላም ቋንቋ የጦርነት ከበሮን የሚተካበት ጊዜ መጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ሃብቶች ከምሽግ ጉድጓድ ቁፋሮ ወደ ተቋማት ግንባታ" የሚሸጋገሩበት ጊዜ መድረሱን ገልጸዋል።

የጦር መሳሪያዎችን ከማምረት ወደ መሬት ማልማት፣ እና የሰውን ልጅ ከመግደል ወደ ማስተማር፣ ማሰልጠን እና ማብቃት" የምንሸጋገርበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ወር መጨረሻ ለኤርትራ በፃፈችው ደብዳቤ የኤርትራ ሠራዊት ተቆጣጣሯቸዋል ካላቻቸው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች እንዲወጣ እና ለድርድር ዝግጁ እንድትሆን ጠይቃለች።

ለዚህ ምላሽ የሰጠችው ኤርትራ በበኩሏ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የተፃፈውን ደብዳቤ "ሐሰት እና የፈጠራ" ስትል ውድቅ አድርጋለች።