ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ 'የቃላት ጦርነት' ለምን አሁን ተካረረ? ወዴትስ ያመራል?
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሲለዋወጡት የቆዩት 'የቃላት ጦርነት' ከመቼውም በበለጠ አሁን ላይ መካረሩን የሚጠቁሙ ምልክቶች እየተስተዋሉ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ "ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት የተወሰኑ አካባቢዎችን ተቆጣጥራለች" እንዲሁም "ታጣቂዎችን ትደግፋለች" ብላ ያቀረበችውን ክስ ኤርትራ "ሐሰተኛ እና የፈጠራ" ስትል አጣጥላለች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቅዳሜ ጥር 30/2018 ዓ. ም. ለኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ፤ የኤርትራ ሠራዊት ተቆጣጥሯቸዋል ካላቸው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች እንዲወጣ እና ለድርድር ዝግጁ እንዲሆን ጠይቋል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር ትናንት የካቲት 3/2018 ዓ. ም. በሰጠው ምላሽ፤ ኤርትራ "ትርጉም የለሽ ውዝግብ ውስጥ ነዳጅ ለመጨመር እና ሁኔታውን ለማቀጣጠል ተነሳሽነቱም ሆነ ፍላጎቱ" እንደሌላት አስታውቋል።
ህወሓት በበከሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ "የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው" ሲል ወንጅሏል።
"እንቅስቃሴው ለሌላ ዙር ጦርነት መዘጋጀት ነው" ያለው ህወሓት፤ ባለፉት ሳምንታት የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል "በአየር እና በምድር ጥቃቶችን ሲፈጽም ነበር። ይህም የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል" ብሏል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው 'የቃላት ጦርነት' አሁን ላይ እየተካረረ የመጣው በምን ምክንያት ነው? ወዴትስ ሊያመራ ይችላል? በሚለው ዙርያ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኞችን አነጋግረናል።
አሁን ላይ ነገሮች ለምን ተባባሱ?
በኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ላይ የሦስተኛ ዲግሪ መመረቂያቸውን የሠሩት በጀርመን የሚገኙት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር ነገራ ጉደታ፤ አዲስ አበባ ለአሥመራ የጻፈችው ደብዳቤ ከሰሞኑ "በትግራይ ክልል በነበረው ግጭት ኤርትራ ተሳትፋለች የሚል ግምገማ ላይ መድረሷን አመላካች ነው" ይላሉ።
ከሳምንታት በፊት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች መካከል በሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት እንደተቀሰቀሰ ተዘግቧል።
በተለይም የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡበት ፀለምት፣ እንዲሁም መጋሌ እና አብአላ አካባቢዎች "የትግራይ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ሠራዊት እና ከአማራ ሚሊሻዎች ጋር ውጊያ አካሂደዋል" የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
ዶ/ር ነገራ እንደሚናገሩት፤ በዚህ ግጭት ውስጥ "ኤርትራ ተሳትፋለች" የሚል ግምገማ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ጠንካራ ይዘት ያለው ደብዳቤ ለኤርትራ ጽፏል።
በሁለቱ አገራት መካከል ለሁለት ዓመታት ገደማ የቆየው "የቃላት ጦርነት እና ዘለፋ እየተጋጋለ፣ እየተቦካ" ቆይቷል የሚሉት ተንታኙ፤ "የኢትዮጵያ መንግሥት በዛ ግጭት ውስጥ የኤርትራ እጅ አለበት ብሎ ስለገመገመ ወደዚህ ከፍ ያለ ደረጃ ያደረሰው ይመስለኛል" ሲሉ አብራርተዋል።
ያለፈው መስከረም መገባደጃ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጻፈው ደብዳቤ፤ የኤርትራ መንግሥት እና ህወሓት "ጽምዶ" በሚል ጥምረት ኢትዮጵያ ላይ "ጦርነት ለመክፈት" እየሠሩ ነው ሲል መክሰሱ አይዘነጋም።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ የፒኤችዲ ተማሪ ደረጄ ይመር፤ የኢትዮጵያ ደብዳቤ "ቅጽበታዊ" እንዳልሆነ ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት "የባሕር በር ለማግኘት ሜዳውን የማመቻቸት እንቅስቃሴ" አካል እንደሆነም ያምናሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ከማግኘት ጋር በተያያዘ ሲያራምደው የዘለቀው "ለኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ያስፈልጋታል" የሚል አቋም በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ "ውግዘት" ሊያስከትል የሚችል እንደሆነ ይገልጻሉ።
"ለምሳሌ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር [ምክንያት] ወደ ጦርነት ብትገባ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻርም ከአልጀርስ ስምምነት አንጻርም ቅርቃር ውስጥ ሊከታት ስለሚችል አዋጭ አይደለም" ይላሉ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪው።
ስለዚህም "የሉዓላዊነት አደጋ" ውስጥ እንደገባች እና በተባበሩት መንግሥታት ስምምነት መሠረት "ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ እርምጃ ለመውሰድ" ሁኔታዎችን እያመቻቸች እንደሆነ ያስረዳሉ።
አንድ አገር የሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ ከገባች "በማንኛውም ቅጽበት ያንን አደጋ የመቀልበስ ሙሉ ሥልጣን አላት" የሚል የተመድ አንቀጽን በመጠቀም፤ ኢትዮጵያ ከግዛት ሉዓላዊነት አንጻር "አደጋ ውስጥ እንደወደቀች" በማድረግ "ተቀባይነት ያለው አካሄድ" ለመከተል እንደሆነ ይገልጻሉ።
"የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለገባ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እየተጻረረ ስለሆነ እንዲሁም የኢትዮጵያን እንደ አገር መኖር እና አለመኖር ቅርቃር ውስጥ የሚከት የፖለቲካ ሁኔታ ስለተፈጠረ፤ ኢትዮጵያ ይሄንን ለመቀልበስ የትኛውንም የኃይል እርምጃ ብትወስድ የሚያስወቅስ ወይም በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የሚያስወግዝ ዲፕሎማሲያዊ ጫና አያስከትልም።"
ኢትዮጵያ "ነገሩን ፍትሐዊ የሚያደርግ ነገር መዝዛ ወደ ግጭት ውስጥ ብትገባ" ደግሞ ከዚያ በኋላ የሚኖረው "ኤርትራን የማባረር ብቻ አይሆንም" ይላሉ ተመራማሪው።
የኢትዮጵያ መንግሥት "ከዚህ ቀደም በአልጀርስ ስምምነት የተፈጠረው ታሪካዊ ስህተት መደገም የለበትም" የሚል አቋም ሲያራምድ እንደመቆየቱ፤ ግጭት ከተነሳ በኋላ "ቀይ ባሕርን ወይም አሰብን ያካተተ አዲስ ስምምነት ከኤርትራ ጋር ለመፈራረም" የሚያስችል "የፖለቲካ ማዕቀፍ" እንደሚያገኝ ያስረዳሉ።
ስለዚህም ከኢትዮጵያ ለኤርትራ የተላከው ደብዳቤ "ቅጽበታዊ ውሳኔ" ሳይሆን "በደንብ ታስቦበት የተላከ ነው" የሚል አስተያየት አላቸው።
በትግራይ ጦርነት ሠራዊቶቻቸውን አንድ ላይ ያሰለፉት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከፕሪቶሪያ ስምምነት ወዲህ የገቡበት መቃቃር ከኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ጥያቄ ጋር በተያያዘ የበለጠ ተጋግሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥር 26/2018 ዓ. ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የባሕር በር "በባሌም ሆነ በቦሌ ማግኘቷ አይቀርም" ማለታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች የቀይ ባሕርን ጉዳይ ሲያነሳ ቆይቷል። የኤርትራ መንግሥት ከቀይ ባሕር ጋር በተያያዘ የተደረጉ ንግግሮችን "ቅዠት" በሚል ማጣጣሉ አይዘነጋም።
ያለፈው ጥር ወር መባቻ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ "ከኤርትራ በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የተላኩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጥይቶችን ያዝኩ" ማለቱን ተከትሎ ኤርትራ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት "ጦርነት ለመጀመር ሰበብ እየፈለገ ነው" ብላለች።
ለንደን የሚገኙት የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሕማን ሰይድ አቡ ሐሺም፤ የሁለቱ አገራት የደብዳቤ እና መግለጫ ልውውጥ "ወደ መጠራጠር እና ውጊያ የሚያመራ ነው" ይላሉ።
ኢትዮጵያ የኤርትራ ወታደሮች በግዛቷ እንደሚገኙ ብትገልጽም፤ በየትኞቹ አካባቢዎች ላይ እንደሚገኙ ግልጽ አለመደረጉ "ትንኮሳ እንደተፈለገ" እንደሚያሳይ ያምናሉ።
"እውነት ያለው ቢሆን ኖሮ የትኞቹ አካባቢዎች እንደሆኑ ተለይተው በሽምግልና እና በንግግር መፍታት ይቻል ነበር። በኤርትራ ላይ ውጊያ በሚከፈትበት ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች እንዳሉ ለማስመሰል ነው" ሲሉም ይገልጻሉ።
የቀይ ባሕር ጥያቄ ለሁለቱ አገራት መካረር የራሱን ሚና እንደተጫወተ ጠቅሰው፤ ጥያቄው "በኤርትራ ሉዓላዊ መሬት ላይ ለመግባት ከሆነ ማንኛውም አገር የሚቀበለው አይደለም" ይላሉ።
መካረሩ ወደ የት ያመራል?
አሁን ያለው መካረር ወዴት ሊያመራ ይችላል? በሚል የተጠየቁት ዶ/ር ነገራ፤ የለየለት አስከፊ ጦርነት የመፈጠር ዕድሉ አነስተኛ (less likely) ቢሆንም፤ ፈጽሞ የማይሆን (unlikely) ሊባል እንደማይቻል ይናገራሉ።
"ከዚህ ቀደም በባድመ ጦርነት እንደነበረው ግንባር ለግንባር አየር ለአየር [የመዋጋት] ዕድሉ አነስተኛ ነው የምለው ለአሁን ነው። በጊዜ ሒደት፣ ከአንድ ሁለት ዓመት በኋላ ወይም መሃል ላይ ስህተት ከተፈጠረ ጦርነት ሊፈነዳ ይችላል።"
የአልጀርስ ስምምነት ከተፈረመ አንስቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን እስከ መጡበት ጊዜ ድረስ ያለው ሰላምም ጦርነትም ያልነበረበትን ወቅት በማጣቀስ አሁንም ሁለቱ አገራት አንዳቸው የሌላቸው "አማጺያን በመደገፍ ቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ" እንደሆኑ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ የኤርትራ ወታደሮች ሉዓላዊ ግዛቷን ጥሰው በኃይል የተቆጣጠሯቸው ሥፍራዎች መኖራቸውን ስትገልጽ የአሁኑ የመጀመረያዋ አይደለም።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው፤ የኤርትራ ጦር አባላት በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ያሉ ሥፍራዎችን ተቆጥጥረው እንደሚገኙ እና "የከፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በድንበር አካባቢዎች እንደሚፈጸሙ ሪፖርቶች መውጣታቸውን" ቀጥለዋል ሲሉ ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያ፤ የኤርትራ መንግሥት ሉዓላዊነቷን እና ድንበሯን ከመጣስ እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጓን ብትገልጽም ጥሰቶቹ መቼ እንደተከሰቱ በግልጽ አልተመለከተም።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ደብዳቤ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ሰሜን ምሥራቅ ድንበር ከዚህ ቀደም ከተቆጣጠሩት አካባቢ የበለጠ ዘልቀው እንደገቡ ከስሳለች።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ፤ "በሚያሳዝን ሁኔታ፣ በኤርትራ ላይ ከሁለት ዓመታት በላይ በቆየው የጥላቻ ዘመቻ አካሄድ እና አዙሪት ውስጥ ሌላ አሳዛኝ ተግባር ነው" ሲል የኢትዮጵያ መንግሥትን ደብዳቤ ኮንኗል።
የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪው ደረጄ "በኢትዮጵያ በኩል ሦስተኛ አደራዳሪ ወገን እንዲገባ ፍላጎት" እንዳለ ይገምታሉ።
"ሦስተኛ አደራዳሪ አካል በሚገባበት ጊዜ ጉዳዩ የድንበር ብቻ አይደለም። ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ወገኖች አሰብ ወይም ቀይ ባሕርን ያካተተ አዲስ ስምምነት መፈጠር አለበት የሚሉ ብዙ ጫናዎች ሲያደረሱ ነበር" ሲሉ ያብራራሉ።
"ወደ አልጀርስ ስምምነት የተገባው ዋጋቸው ወይም ሕጋዊነታቸው የወደቁ የቅኝ ግዛት ውሎች ተይዘው ነው። [የኢትዮጵያ መንግሥት] ያ ታሪካዊ ስህተት እንደይደገም እና [ስምምነቱም] በሕግ ዋጋ እንደሌለው አጽንኦት ተሰጥቶት፤ በሦስተኛ አካል በኩል ከኤርትራ ጋር ድንበሩን ያካተተ አዲስ ስምምነት እንዲኖር ይፈለጋል" ሲል ያብራራል።
ኢትዮጵያ "ከጦርነት ያልተናነሰ መወጣጠር እንዲፈጠር ጫና በመፍጠር" የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንዲኖር ማድረግ እንደምትሻም ያክላሉ።
ዶ/ር ነገራ፤ የሁለቱ አገራት መካረር ወደ ወታደራዊ ግጭት ቢያመራ "ጦርነቱ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ብቻ አይሆንም፤ ቀጣናዊ ይሆናል፤ አስከፊም ይሆናል" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
በአንድ በኩል ግብፅ እና ሶማሊያ የኤርትራን መንግሥት ሲደግፉ በሌላ ወገን እስራኤል እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢትዮጵያን እንደሚደግፉ ይናገራሉ።
በሌላ በኩል፤ ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የነዳጅ ግብይት እና የኢንቨስትመንት ትስስር ቢኖራትም፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በኢትዮጵያ ወገን መሰለፍ ወደ ኤርትራት መንግሥት ፊቷን እንድታዞር ሊያስገድድ እንደሚችል ዶ/ር ነገራ ያክላሉ።
የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሕማንም ከዶ/ር ነገራ አስተያየት ጋር የሚመሳሰል ዕይታ አላቸው።
"ይሄ ግጭት ከተጀመረ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ተወስኖ የሚቀር አይሆንም። ሌሎች አገራትም ይህንን አጋጣሚ እንደ ዕድል ተጠቅመው፣ ጣልቃ ገብተው ፍላጎታቸውን ለማስጠበቅ ለመንቀሳቀስ ይገደዳሉ" ይላሉ።
በግጭቱ ኢራን እንዲህም እንደ ቻይና ያሉ ኃያላን አገራት ጣልቃ እንደሚገቡ ጠቅሰው ይህም "በቀጣናው የሚገኙ አገራትን ድህነት ውስጥ እንዲኖሩ የሚያስገድድ ነው" በማለት ያስረዳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ያሉ አገራትን "ወደ መበታተን" የሚያመራ ግጭት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።
በኤርትራም ተመሳሳይ የሆነ ምስቅልቅል ሊያስከትል እንደሚችል ያክላሉ።