ኤርትራ ሠራዊቷን በአስቸኳይ ከግዛቷ እንድታስወጣ እና ለድርድር ዝግጁ እንድትሆን ኢትዮጵያ ጠየቀች

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኤርትራ ሠራዊት ተቆጣጣሯቸዋል ካላቸው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች እንዲወጣ እና ለድርድር ዝግጁ እንዲሆን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠየቀ።

ሚኒስቴሩ ቅዳሜ ጥር 30/2018 ዓ.ም. ለኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር በመጣስ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኙ አካባቢዎችን ተቆጣጥራ እንደምትገኝ ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የደብዳቤውን ትክክለኛነት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ደብዳቤው የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ የኤርትራ ጦር ከግዛቱ ለቅቆ እንዲወጣ መጠየቁን አስታውሶ፤ ይህ ጥያቄው ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ "የባሕር አገልግሎት ጉዳዮችን እና በአሰብ ወደብ በኩል የባሕር መዳረሻን ጉዳይ ጨምሮ ሁሉንም የጋራ ጥቅም ጉዳዮችን ለመፍታት በቅን ልቦና በድርድር ለመሳተፍ ፈቃደኛ" መሆኑን አስታውቋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የተጻፈው እና ለኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳላህ በተላከው በዚህ ደብዳቤ፣ የኤርትራ ሠራዊት "ለረዥም ጊዜ" የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በመጣስ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።

በዚሁ ደብዳቤ ላይ ሁለቱ አገራት በሚያዋስናቸው አካባቢዎች የኤርትራ መንግሥት በስም ላልተጠቀሱ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች "ቀጥታ የቁሳቁስ ድጋፍ እና እርዳታ" እንደሚያቀርብ በመጥቀስ ወንጅሏል።

በደብዳቤው ላይ የታጣቂ ቡድኖቹ በስም ባይጠቀሱም ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ ለህወሓት እና ለፋኖ ታጣቂዎች ድጋፍ ያደርጋል ሲል መወንጀሉ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በደብዳቤው ላይ የኤርትራ መንግሥት በሉዓላዊነቱ እና በድንበር ላይ ከሚፈጽመው ጥሰት በተደጋጋሚ እንዲታቀብ ቢጠይቅም ጥረቱ ሰሚ አለማግኘቱን ገልጿል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ሁለቱን አገራት በሚያዋስናቸው ድንበር አካባቢ "የታዩት ለውጦች የኤርትራ መንግሥት ተጨማሪ የጥፋት መንገድን መምረጡን ያመለክታል" ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤው ላይ አመልክቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤርትራ መንግሥት በደብዳቤው ላይ በስም ካልተጠቀሳቸው ታጣቂዎች ጋር የኤርትራ መንግሥት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛልም ብሏል።

በሰሜን ምሥራቃዊ የኢትዮጵያ ድንበር የኤርትራ ጦር ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው መግባታቸው እና በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ድንበር ደግሞ "የኤርትራ ጦር ከአማፂ ቡድኖች ጋር እያደረገው ያለው የጋራ ወታደራዊ እርምጃ ጸብ ጫሪነት ብቻ ሳይሆን ፍፁም የሆነ ወረራ ነው" ሲል ድርጊቱን አውግዟል።

አክሎም "ይህን ተቀባይነት የሌለውን ሁኔታ ለማቆም የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ ግዛት በአስቸኳይ እንዲያስወጣ እና ከአማፂ ቡድኖች ጋር ያለውን ትብብር እንዲያቆም በይፋ እንጠይቃለን።"

"የሁለቱን ሀገራት የጋራ ብሔራዊ ጥቅምን ባስከበረ መልኩ በላቀ የመከባበር ስሜት ለመመካከር ዝግጁ ነን" ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ፣ አሁን በኤርትራ በኩል የተከፈተው ትንኮሳ ግን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታውቋል።

አክሎም "ኤርትራ ሠራዊቷን በአስቸኳይ እንድታስወጣና ለሰላማዊ ድርድር ዝግጁ እንድትሆን በይፋ እንጠይቃለን" ሲል በአጽንኦት ተናግሯል።

ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ሁለቱም አገራት በማያባራ ግጭት ላይ እንደኖሩ የሚያብራራው ደብዳቤው፣ ይህ ዓይነቱ የግጭት አዙሪት "በውይይት እና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እልባት ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል እንዳለ" በመግለጽ፤ በኤርትራ በኩል በጎ ምላሽ ከተገኘ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩነቶችን በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አብራርቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር ላቀረብነው ሕጋዊ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ካገኘን የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር ላይ ጉዳዮች እና በአሰብ ወደብ በኩል ወደ ባሕር በር ጉዳይን ጨምሮ አጠቃላይ የጋራ ጉዳዮች ላይ ሁሉን አቀፍ እልባት እንዲያገኝ በቅን ልቦና ድርድር ለማድረግ ፈቃደኛ ነው" ብሏል።

በኤርትራ መንግስት በኩል እስካሁን ለዚህ ደብዳቤ የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ የለም።

የጋራ መከባበር እና መተሳሰብ ግንኙነትን ለመፈተሽ ቆርጠን ተነስተናል ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ፣ ቀና ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋውን ገልጿል።

በዚህ ዓመት መጀመርያ መስከረም ወር መገባደጃ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጻፈው ደብዳቤ የኤርትራ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) "ጽምዶ" በሚል ጥምረት ኢትዮጵያ ላይ "ጦርነት ለመክፈት" እየሰሩ ነው ሲል ከስሷል።

በጥር ወር መጀመርያ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የኤርትራ መንግሥት "ከኢትዮጵያ የውስጥ ባንዳዎች እና ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር" በትግራዩ ህወሓት በኩል የተላኩ ያላቸውን ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ የጎረቤት አገር ኤርትራ መንግሥት በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች የተለያዩ ዓይነት የጦር መሣሪያ ጥይቶችን እየሰጠ ነው ስትል በተደጋጋሚ ከስሳለች።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር እንዲሁ የኤርትራ ጦር አባላት በኢትዮጵያ ድንበር ያሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ እና የከፉ ጥሰቶች መፈጸም መቀጠላቸውን ሪፖርቶች እየወጡ እንደሆነ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መገልጿ አይዘነጋም።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው "የከፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በድንበር አካባቢዎች እንደሚፈጸሙ ሪፖርቶች መውጣታቸውን" ቀጥለዋል ሲሉ ነበር በወቅቱ የተናገሩት።