ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ፤ የኤርትራ ጦር በትግራይ በተቆጣጠራቸው ስፍራዎች ጥሰቶች እየፈጸመ ነው ስትል ለተመድ ከሰሰች
የኤርትራ ጦር አባላት በኢትዮጵያ ድንበር ያሉ አካባቢዎችን አሁንም ተቆጣጥረው እንደሚገኙ እና የከፉ ጥሰቶች መፈጸም መቀጠላቸውን ሪፖርቶች እየወጡ እንደሆነ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሰሰች።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው "የከፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በድንበር አካባቢዎች እንደሚፈጸሙ ሪፖርቶች መውጣታቸውን" ቀጥለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
አምባሳደር ጸጋአብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኤርትራ ሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ላይ ያቋቋመው ልዩ ተከታታይ (ራፖርተር) ሥልጣን መራዘምን በተመለከተ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት ነው ይህንን የተናገሩት።
ኤርትራ በበኩሏ አለም አቀፉ በሚያውቀው ድንበር ተወስና እንዳለች ገልጻ ይህንን የአምባሳደሩን ወቀሳ አጣጥላለች።
አምባሳደር ጸጋ አብ ኤርትራ እየወሰደችው ያለው እርምጃ የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያበላሽ ብቻ ሳይሆን "በኢትዮጵያ ላይ ቀጥታ ስጋት የጫረ ነው" ብለዋል።
አምባሳደሩ ለዚህም ማጠናከሪያ በኤርትራ የሰብዓዊ መብቶች ይዘቶች ላይ አተኩሮ የወጣውን ሪፖርት ማጣቀሻ አድርገዋል።
ይህ ሪፖርት በመንግሥታቱ ስር የኤርትራን ሰብዓዊ መብቶች የሚከታተሉት መሐመድ አብደልሰላም ባቢከር የተጠናቀረ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከሰኔ 9 እስከ ሐምሌ 4 በሚያደርገው ጉባዔ ላይ ቀርቧል።
የኤርትራ መከላከያ ኃይል በትግራይ በተቆጣጠራቸው ስፍራዎች ግድያዎች እና ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየፈጸመ ስለመሆኑ ይኸው ሪፖርት ይጠቅሳል።
በትግራይ እየተፈጸሙ የተባሉት ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ አፈና እና እገታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን በግዳጅ ማፈናቀል እንደቀጠለ "የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ይዞታዎች" በሚል በወጣው ሪፖርት ተካቷል።
በተጨማሪም ዘረፋዎች፣ ንብረት ማውደም፣ ስቅይት፣ ኢሰብዓዊ ይዞታዎች ህጻናትን ጨምሮ ወጣቶችን በግዳጅ ለውትድርና እየመለመሉ ነው የሚሉ ሪፖርቶች እንደደረሱትም ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በኤርትራ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በእንቅስቃሴያቸው ላይ ገደብ እንደተጣለባቸው አመልክቷል።
ከእነዚህም መካከል የሰዓት እላፊን ጨምሮ የትግራይ ክልል ወደሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ለመጓዝ በሞከሩ ላይ ቅጣቶች እንደሚጠብቃቸው፣ ዛቻዎች እንደሚደርሷቸው ይኸው ሪፖርት ጠቅሷል።
እነዚህ ገደቦች ማኅበረሰቦች እንዲነጣጠሉ ማድረጉን መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዳያገኙ ማድረጉንም ተጠቅሷል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ከግዳጅ ውትድርና እና መሰወርን በመፍራት እየተሰደዱ መሆኑ ተጠቅሷል።
በሁለቱ ዓመት የትግራይ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከኢትዮጵያ ጋር ወግነው የተዋጉት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ እንደሚገኙ እና እንዲወጡ ተደጋጋሚ ጥሪዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል።
በኤርትራ-ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን ለኢትዮጵያ በተወሰኑ ግዛቶች በኢሮብ ግዛት በሚገኙት እገላ፣ ወራእትሌ፣ አሊቴና አካባቢዎች፤ እንዲሁም በምሥራቅ ትግራይ ጉሎ መኸዳ፣ሰበያ እና ዛላምበሳ እና በሰሜን ምዕራብ በኩል በሽራሮ ግንባር ታሕታይ አዲያቦ የኤርትራ ኃይሎች እንደሚገኙ ሪፖርቱ ያመለክታል።
በአልጀርስ ስምምነት እና በኤርትራ እና የኢትዮጵያ ድንበር ኮሚሽን የተወሰነውን የድንበር ማካለል ሁለቱ አገራት እንዲያከብሩ ተጠይቋል።
በተጨማሪም አገራቱ በሚወዛገቡባቸው ስፍራዎች ያሉ ነዋሪዎችን መብት እንዲጠብቁ እና የኮሚሸኑንን ውሳኔ ተግባራዊ በሚያደርጉበትም ወቅት ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ እንደሆነም አሳስቧል።
የኢትዮጵያው ተወካይ በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ለሰላም ቁርጠኛነቷን በማሳየት ተደጋጋሚ ጥሪ ብታደርግም ኤርትራ የዓለም አቀፍ ሕግን በከፍተኛ መልኩ መጣሷን ቀጥላለች ብለዋል።
ዲፕሎማቱ እንደማሳያም የጠቀሱት የኤርትራ ኃይሎች የኢትዮጵያን ግዛቶች ይዘው እንደሚገኙ እና "ጦርነት ለመጀመር አይቀሬ ስጋት ደቅናብናለች" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ጦርነቱ እየተሳተፉ ነው መባላቸውን "መሠረተ ቢስ" በማለት ሲያጣጥሉ እንዲሁም የኤርትራ ወታደሮች የሉም በማለት ሲናገሩ መቆየታቸው አይዘነጋም።
ኤርትራ በሚቀርቡባት ጥሰቶች ላይ ነጻ ምርመራ እያደረገ ያለውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ የሰብዓዊ መብት ተከታታይ እንዲዘጋ ከሰሞኑ ብትጠይቅም ምክር ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት በኤርትራ ሰብዓዊ መብት ይዞታዎች ላይ ያቋቋመው ልዩ ራፖርተር ሥልጣን እንዳይራዘም ያቀረበችውን ጥያቄ ኢትዮጵያን ጨምሮ 25 አገራት ተቃውመውት ውድቅ የተደረገው አርብ፣ ሰኔ 27/2017 ዓ.ም. ነበር።
ለኤርትራ ኩባ፣ ቻይና፣ ቦሊቪያ እና ሱዳን ድጋፍ የሰጧት ሲሆን ኳታርን ጨምሮ 18 አገራት ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።
ኤርትራ የምትከሰሰስባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች "መዋቅራዊ እንዳልሆኑ" በመግለጽ በማደግ ላይ ባሉ አገራት እንዳለው "የአቅም ውስንንት" ማንሳቷ ተዘግቧል።
ሆኖም የመንግሥታቱ ድርጅት ተከታታይ አካል የሥልጣኑ ዘመን ለአንድ ዓመት እንዲራዘም የቀረበውን ሃሳብ ኢትዮጵያን ጨምሮ አገራቱ በሰጡት ድምጽ በቀላሉ አልፏል።
ከበርካታ አፍሪካ አገራት ተለይታ ሥልጣኑ እንዲራዘም የጠየቀችው ኢትዮጵያ በአምባሳደሯ በኩል ያጋጠመን "ልዩ ሁኔታ" ይሄንን አቋም እንዲወስዱ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን "የቀጣናውን መረጋጋት ላይ ስጋት የሚፈጥሩ ናቸው" ሲሉ አምባሳደር ጸጋ ተናግረዋል።
ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት አምባሳደሩ በኢትዮጵያ "ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ደኅንነት፣ የሰብዓዊ መብቶች እና የሰብዓዊ እርዳታ ግዴታዎችን ለመወጣት ኤርትራ ስጋት ደቅናባታለች" ማለታቸውን ከኢትዮጵያ "የቀድሞ አቋም ጋር የሚቃረን እና ወጥነት የሌለው" ነው ስትል ኤርትራ ተችታለች።
ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ "ልዩ ራፖርተሩ ገንቢ ውይይት እና ትብብርን ያደናቅፋል" በሚል የሥልጣን ዘመኑ በአስቸኳይ እንዲቋረጥ መጠየቋን በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ ተወካይ ሐብቶም ዘርዓይ መናገራቸውን የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐምሌ 1/ 2017 ዓ.ም በገጹ አውጥቷል።
"ይህ ወጥነት አለመኖር በሚያሳዝን ሁኔታ የምክር ቤቱን ትውስታ እንዲሁም ዕውቀትን የሚዘልፍ ነው" ማለታቸውን መግለጫው ያስረዳል።
"የኤርትራ ኃይሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ ድንበሮቻቸው ተወስነው እንዳሉ" ያተተው ይህ መግለጫ "ከዚህ የተጻረሩ ጉዳዮች ሐሰተኛ እንዲሁም ግጭቶችን ለማነሳሳት እና ምክንያታዊ ለማድረግ ተንኮል በተሞላ ሁኔታ የተነደፉ ናቸው" ብሏል።
አምባሳደር ጸጋ በበኩላቸው ኤርትራ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ድጋፍ ጨምሮ ከብዙ ዓመታት ገንቢ የዲፕሎማሲያዊ ጥረት በኋላ "ትርጉም ያለው ለውጥ ባለማየታችን በጣም አዝነናል" ሲሉ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በቆየው ተቀባይነቷ ከኤርትራ የመጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን አስጠልላ እንደምትገኝ ገልጸው፤ ሆኖም ይህ ሁኔታ "የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት፣ ፀጥታ እና የሕዝብ ደኅንነት ለማዳከም እና ማኅበራዊ ትሰስርን ለመበጣጠስ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው" ብለዋል።
ኤርትራ በበኩሏ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ የኤርትራ ወደቦችን "ከተቻለ በሕጋዊ መንገድ አስፈላጊ ከሆነ በወታደራዊ ኃይል" ለመቆጣጠር በግልጽ እና በተደጋጋሚ ፍላጎቷን አሳውቃለች በማለት ወቅሳለች።
"ሰብዓዊ መብት እና ብሔራዊ ደኅንነት" የሚሉ ትርክቶች እነዚህን "ሕገወጥ ፍላጎቶችን ማሟያ ሽፋን ናቸው" ሲሉ የኤርትራው ተወካይ ተችተዋል።
በኤርትራ በኩል ውጊያ እንደሚነሳ በርካታ ወሬዎች እንደሚነገሩ በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "በእኛ በኩል አንዲት ጥይት አይተኮስም" ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አስታውቀዋል።
አክለውም "የኤርትራ ሕዝብ ወንድም ሕዝብ ነው። የእኛን ሰላም መፈለግ በዚያ ምጥጥን መታየት አለበት" ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ከሞላ ጎደል ሰላማዊ ግንኙነት እንደምትፈልግ ገልጸው "ሰላም ነው የምንፈልገው" ብለዋል።
ሆኖም "በሰላም የማያኖር ነገር ካለ ራሳችንን እንከላከላለን። ኢትዮጵያ አትበታተንም፤ ራሷን ለመከላከል በቂ አቅም አላት" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ኤርትራ ተጥሎባት የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መነሳቱን ተከትሎ ሠራዊቷን መልሳ በማጠናከር በአካባቢው በተለይም በኢትዮጵያ መረጋጋት እንዳይኖር እያደረገች ነው ሲል አንድ የአሜሪካ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሪፖርት አመልክቷል።
ኤርትራ ግን የቀረበባት ክስ የፈጠራ እና ማሳበቢያ ነው በማለት በአካባቢው ለተፈጠረው ውጥረት ተጠያቂያዋ ኢትዮጵያ ናት ስትል ከስሳለች።
'ዘ ሴንትሪ' የተባለው የአሜሪካ የመብቶች ተከታታይ መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ሰኞ ዕለት ባወጣው ሪፖርት ኤርትራ ተጥሎባት የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ከሰባት ዓመት በፊት ከተነሳ በኋላ ሠራዊቷን መልሳ በመገንባት እና በማጠናከር "በጎረቤቶቿ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት እየፈጠረች ነው" ብሏል።