ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ናት፤ የባሕር ተደራሽነት ካላገኘች ግን አገር መሆን አትችልም" ጠ/ሚ ዐቢይ
"ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ናት፤የባሕር ተደራሽነት ካላገኘች ግን አገር መሆን አትችልም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ የጎረቤት አገራትን ሉዓላዊነት እንደምታከብር፤ "በእነሱም ወገን ደግሞ ይኼ [የባሕር ተደራሽነት] መከበር እንዳለበት" ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ሐሙስ፣ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ያላትን ግንኙነት እንዲሁም ዲፕሎማሲውን አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ የመንግሥታቸው አቋም በሰላማዊ መንገድ እና በንግግር ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።
"ኤርትራ ሉዓላዊት አገር ናት፤ በግዴታ የኢትዮጵያ አካል እንድትሆን አንፈልግም።ያ ፍላጎት የለም፤አገር መሆን መብቷ ነው። ጂቡቲ እንዲሁም ሶማሊያ ሉዓላዊ አገራት ናቸው፤ ይኼም መከበር አለበት። ጥያቄ የለንም" ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስመልክቶ ባነሱበት ወቅት ኢትዮጵያ አገር የምትሆነው የባሕር በር 'አክሰስ' [ተደራሽነት] ካገኘች መሆኑን ጠቅሰው ይኼም በጎረቤት አገራቱ ሊከበር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
"አብሮ ለመኖር ያለው ነገር ሰጥቶ መቀበል ነው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር ተደራሽነት የሚመጣው በንግግር እንደሆነም ዐቢይ አቋማቸውን አሳውቀዋል "ይህ ባሕር የሚመጣው በገንዘብ ነው? በላንድ ስዋፕ [መሬት በመቀያየር] ነው? በምንድን ነው? ለሚለው መነጋገር ያስፈልጋል፤ በንግግር መሆን አለበት" ብለዋል።
ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ውጭ ህልውና እንደሌላት፤ እነሱም በተመሳሳይ መልኩ ህልውናቸው የተያያዘ እንደሆነ እንዲሁም የአገራቱ ምጣኔ ሃብትም ሆነ ዕጣ ፈንታ የተሳሰረ ነው ብለዋል።
ሆኖም የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የኢትዮጵያን ትልቅነት ሊገነዘቡ እንደሚገባ እና ሁከት ከማስነሳት ሊታቀቡ ይገባል ሲሉ በዛሬ ውሏቸው አሳስበዋል።
"የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ማወቅ ያለባቸው ኩሬ እና ሐይቅን መለየት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ በትናንሽ ጠጠር አትታወክም፤ አትበተንም።ኢትዮጵያ ትልቅ ባሕር፣ ትልቅ አገር ናት፤ ይሄንን መገንዘብ ያስፈልጋል። ሲፈልጉ እንደሚያውኩ ማሰብ ጥሩ አይደለም። ሁከቱ የሚጎዳው ኩሬዎችን ነው፤ ሐይቆችን አይደለም" ብለዋል።
አክለውም አገሪቷ የዘመነ ጦር፣ ከፍተኛ ሃብት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ከመላቋ አንጻር "ውጊያ አማራጭ አድርጎ ከተነሳ ለውድድር የሚቀርብ አይደለም" ሲሉም አክለዋል።
በኤርትራ በኩል ውጊያ እንደሚነሳ በርካታ ወሬዎች እንደሚነገሩ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በእኛ በኩል አንዲት ጥይት አይተኮስም" ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አስታውቀዋል።
አክለውም "የኤርትራ ሕዝብ ወንድም ሕዝብ ነው። የእኛን ሰላም መፈለግ በዚያ ምጥጥን መታየት አለበት" ሲሉ አስረድተዋል።
ከጎረቤት አገራት ጋር ከሞላ ጎደል ሰላማዊ ግንኙነት ኢትዮጵያ እንደምትፈልግ ገልጸው "ሰላም ነው የምንፈልገው" ብለዋል።
ሆኖም "በሰላም የማያኖር ነገር ካለ ራሳችንን እንከላከላለን። ኢትዮጵያ አትበታተንም፤ ራሷን ለመከላከል በቂ አቅም አላት" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ኤርትራ ተጥሎባት የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መነሳቱን ተከትሎ ሠራዊቷን መልሳ በማጠናከር በአካባቢው በተለይም በኢትዮጵያ መረጋጋት እንዳይኖር እያደረገች ነው ሲል አንድ የአሜሪካ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሪፖርት አመልክቷል።
ኤርትራ ግን የቀረበባት ክስ የፈጠራ እና ማሳበቢያ ነው በማለት በአካባቢው ለተፈጠረው ውጥረት ተጠያቂያዋ ኢትዮጵያ ናት ስትል ከስሳለች።
'ዘ ሴንትሪ' የተባለው የአሜሪካ የመብቶች ተከታታይ መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ሰኞ ዕለት ባወጣው ሪፖርት ኤርትራ ተጥሎባት የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ከሰባት ዓመት በፊት ከተነሳ በኋላ ሠራዊቷን መልሳ በመገንባት እና በማጠናከር "በጎረቤቶቿ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት እየፈጠረች ነው" ብሏል።
"የትግራይ ክልል ወደ ጦርነት እንዳይገባ የሃይማኖት አባቶች ሚናችሁን ተወጡ"
ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህወሓት መካከል የተፈጠረው ክፍፍል ጋር ተያይዞ የትግራይ ክልልን ያማከሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ለትግራይ ሕዝብ ያመጣውን ፋይዳ በመዘርዘር በዚህ ውሏቸው አስረድተዋል።
ስምምነቱ ለትግራይ ሕዝብ እፎይታ እንዲሁም የትግራይ ወላጆች ልጆቹን በየቀኑ ከማጣት ታድጎታል ብለዋል። ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች አገራት ደግሞ መንግሥት እያሸነፈ ቢሆንም ሰላምን በመምረጥ አዲስ ባህልን የፈጠረ ነው በማለት አወድሰውታል።
በክልሉ በጦርነቱ እንዲቋረጡ የተደረጉ የቴሌኮም፣ ባንኮች፣ አየር መንገድ እና ሌሎች አገልግሎቶች መጀመር እንዲሁም ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ወደ ራያ እና ጸለምት መቶ በመቶ መመለሳቸው የስምምነቱ ተግባራዊነት ስኬት መሆኑንም ነው ጠ/ሚ ዐቢይ የጠቀሱት።
ሆኖም አሁንም ተፈናቃዮች ወደ ወልቃይት አለመመለሳቸው ቀሪ ያልተሳካ ተግባር ነው ሲሉ ሕዝቡን ወደቀዬው መመለስ አሁንም መንግሥት እንደሚያተኩርበት ገልጸዋል።
ሌላኛው በስምምነቱ መሠረት ተግባራዊ ያልሆነ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ መልሶ ማቋቋም እና ወደ ማኅበረሰቡ መቀላለቀል ሊፈጸም የሚገባው እንደሆነ ተናግረዋል።
የትግራይ ሕዝብ በፍጹም ጦርነት አይፈልግም ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክልሉ "ወደ ጦርነት እንዳይገባ" የሃይማኖት አባቶች ፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራን እና ኤምባሲዎች ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በትግራይ ወደ "ውጊያ ከተገባ ነገሮች ይበላሻሉ" እንዲሁም ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ እንደሚሆን ነው ዐቢይ ያስጠነቀቁት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ጦርነት ቢቀሰቀስ "ዓለም ደንታ የለውም፤ ብዙ ውጊያ እያስተናገደ ስለሆነ፤ ጆሮም የለውም፣ ጊዜም የለውም። ዓለም ጊዜ ቢኖረው ኖሮ ሱዳንን ያዳምጥ ነበር" ብለዋል።
ሆኖም "የዓለምን ሁኔታ እና የዘመኑን ውጊያ ባለመገንዘብ፣ የሚያግዙን ሰዎች እና ሃገራት አሉ ብለው" ውጊያ ለመክፈት የሚፈልጉ አሉ ብለዋል።
ሆኖም "በትላልቅ ውጊያዎች መደጋገፍ ችግር ሆኗል፤ ከራስ ተርፎ ሰው ለማገዝ የሚያስችል አይደለም ሲሉ ያለውን የዓለምን ምጣኔ ኃብት መዋዠቅ እንደ ምክንያትነት ጠቅሰዋል።
"እነዚህ አገራት እንኳን እናንተን እራሳቸውን ማገዝ አይችሉም። ሞራል ቲፎዞነት እና ማገዝ ለየብቻ ነው። ስታዲየም ተቀምጦ ማጨብጨብ እና ኳስ ሜዳ ገብቶ መጫወት ለየብቻ ነው፤ እገዛ እናገኛለን ብሎ ማሰብ ስሁት ግምገማ ነው" ሲሉ ወቅሰዋል።
እነዚህ ውጊያ መክፈት የሚፈልጉ አካላት ያሏቸው "የዘመኑን የውጊያ ስልት ባለመረዳት እንደ ድሮው ተራራ መያዝ፣ ተራራ መልቀቀቅ ብቻ ማሰብ ልክ አይደደለም" ሲሉ ከተቿቸው በኋላ "ኢራንን እና እስራኤልን ያዋጋው ተራራ አይደለም፤ ዘመን ተቀይሯል" ብለዋል ለፓርላማው።
አክለውም "መንግሥት በሸኔ እና በፋኖ ተወጥሯል እንዲሁም መንግሥት ወታደር ስለተበታተነበት ጊዜው አሁን ነው" የሚሉ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው፤ እነዚህ ሰዎች ግን የሶማሊያን እና የጣልያን ወረራዎችን በማስታወስ ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለው ሊቃኙት ይገባል ብለዋል።
ትግራይን የሚያስፈልጋት ሰላም "ችግሮችን በውይይት መፍታት ይቻላል" ያሉት ዐቢይ፤ በትግራይ በድጋሚ "ወደ ጦርነት እንዳይገባ "የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን በመወጣት ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
"የሃይማኖት አባቶች፣ የሁሉም እምነት አባቶች እዚህ ተወካዮች አላችሁ። ሌላ ምንም ስራ የላችሁም። ትግራይ ወደ ግጭት እንዳይገባ፣ ወደ ጦርነት እንዳይገባ፤ ስራችሁን በፍጥነት አሁን ጀምሩ። ከተጀመረ በኋላ ብትናገሩ ዋጋ የለውም" ካሉ በኋላ ወደ ጦርነት ከተገባ ሁኔታዎች ይበላሻሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አክለውም "ከተጀመረ፤ ከዚህ በፊት የምናውቀው አይደለም። ነገር ይበላሻል። አሁን ሚናችሁን ተወጡ። በእኛ በኩል በትግራይ ምድር አንድ ጥይት መተኮስ ፍላጎት የለን። ከቻልን ማልማት ነው የምንፈልገው"
የአገሪቱ ሰላም እና ፀጥታ መጓደል
የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በግጭት መናወጥን አስመልክቶ ጥያቄ ከምክር ቤት አባላት የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የአገሪቱ ሰላምና የፀጥታ መጓደል ዋነኛ መንስዔ "የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በአገሪቱ ውስጥ የስንፍና ፖለቲካ ተንሰራፍቷል ያሉት ዐቢይ "ሰነፍ ፖለቲከኞች" ሲሉ የጠሯቸውን ግለሰቦች ከቀድሞ መሳፍንት እና መኳንንት ጋር በማነጻጸር "ሳይሠሩ መካፈል የሚፈልጉ ናቸው" ሲሉ ተችተዋቸዋል።
"አውርቶ አደር" በሚል ቃል የጠሯቸው እነዚህ ፖለቲከኞች ሥራ ሳይሠሩ፣ አገልግሎት ሳይሰጡ መብላት የሚወዱ ግጭት ጠማቂ ናቸው" ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኃይል ፍላጎትን የማስፈጸም ገፊ ምክንያት የሆነው ድህነት እንዲሁም ኋላ ቀርነት እና ዘረኝነት አባባሽ ችግሮች ናቸው ሲሉ፤ ለአገሪቱ ሰላም እና ፀጥታ መጓደል የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል ይላሉ።
እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የውጭ ጣልቃ ገብነት ታክሎበት በብሔራዊ ጥቅም ላይ የመደራደር ሁኔታ፣ "የእኛ የባንዳነት ስሪት" ጋር ተጨምሮ ችግሩ ተባብሷል ሲሉ አክለዋል።
ለማኅበረሰቡም ባስተላለፉት መልዕክት "አትግደሉኝ ብቻ ሳይሆን፣ አትግደሉልኝ እናንተም አትሙቱልኝ በሏቸው" ብለዋል።
አክለውም "ልጆቼን ፈተና እንዳይፈተኑ እንዳይማሩ አትከልክሉ፣ እንዳንሠራ አታድርጉ፣ ማዳበሪያ እንዳይመጣ አታድርጉ ማለት አለበት። ይህንን ሰሞኑን የአማራ ሕዝብ በቅርቡ አሳይቷል፤ ሰላም እና ልማት እፈልጋለሁ ብሏል፤ በቃኝ ብሏል። ይህ ለሁሉም ግልፅ መልዕክት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
"በዚህ ዓመት 8.1 በመቶ አጠቃላይ ዕድገት ተመዝግቧል"
ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ በዘንድሮው ዓመት የኢትዮጵያ ማንሰራራት ዘመን በሚል በተጀመረው የሥራ ውጥን አገሪቷ በርካታ ውጤቶችን የተጎናጸፈችበት እንደሆነ ገልጸዋል።
"ዘንድሮ ታላላቅ ውጤቶች የተመዘገቡበት፤ አመርቂ ውጤቶች የታዩበት እና በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው የማያውቁ ድሎች የተጎናጸፍንበት ዓመት ነው" በማለት ለዚህም ለምክር ቤቱ አባላት እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው የጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ሪፎርሙ [ማሻሻያው] የተጀመረው አብዮት መር በሆነ መልኩ ሳይሆን የነበረው ሳይፈርስ በጎደለው ላይ የመሙላት በሚል ታቅዶ ነው የተሰራው ብለዋል።
መንግሥታቸው ኢትዮጵያ ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እንድትገባ የሆኑ ምክንያቶች በዋናነት የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራትን ለመጠገን ነው ብለዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቱ አገሪቱ እያለፈችበት በነበረው በሥራ አጥነት፣ በዋጋ ግሽበት እንዲሁም የንግድ ሚዛኑ መጓደል ሊገለጽ እንደሚችል አስረድተዋል።
ሌሎች ወደ ማሻሻያው እንዲገቡ የሆናቸው ምክንያት ብለው የጠቀሷቸው በግሉ ዘርፍ የነበረው አለመነቃቃት እና ምቹ አለመሆን፤ በግብርና እና ኢንዱስትሪ የነበረው የምርታማነት ውስንነት አንዲሁም በገበያ ተወዳዳሪ አለመሆንን ጠቅሰዋል።
የዓለም የንግድ ሥርዓት መዛባት እንደገጠመው እና የዓለም ዕድገትም እየዋዠቀ መሆኑን በሰፊው ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የ8.1 በመቶ አጠቃላይ ዕድገት አምጥታለች ብለዋል።
አይኤምኤፍ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ተንብዮ የነበረው "ዕድገት 4.8 ቢሆንም ዕድገቱ ከትንበያው ዝቅ ብሎ 3.8 በመቶ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱ ከሰሃራ በታች ከፍ ያለ ዕድገት እንዳመጣች አመልክተዋል።
በዘንድሮውም ዓመት 8.4 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ መንግሥታቸው እየሠራ እንደሆነ ነው የገለጹት። በዚህም የብልጽግና መንግሥት ብዝኃ ዘርፍ በማድረግ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስ በአገልግሎት የታየው መመንደግ እንደሆነ አስረድተዋል።
ዐቢይ ሌላኛው ስኬት ብለው የጠቀሱት 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከሴፍትኒት ተረጂነት መላቀቃቸውን በመጥቀስ ነው።
ባለፈው ዓመት 27 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በሴፍትኔት እርዳታ ታቅፈው እንደነበር ጠቅሰው በተሠራው ሥራ አብዛኛው ከተረጂነት ወጥቷል ብለዋል። ቀሪው ከአራት ሚሊዮን ያነሱትንም ከተረጂነት በማውጣት "የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ አለብን" ሲሉም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማዕድን እና ጋዝ ማውጣትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያቸው አገሪቷ በሶማሌ ክልል በመጪው መስከረም ወር ለመጀመሪያ ጊዜ የጋዝ ምርት ለገበያ እንደምታቀርብ ገልጸዋል።
ጋዝ ለማውጣት በተለያዩ ዘመናት ተሰማርተው የነበሩ ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው በፈቃዱ ብር ይፈልጉ እንደነበር አስታውሰው ይህ አሠራር አያወጣም በሚል አዳዲስ ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ ገብተዋል ብለዋል።
አዲስ የጋዝ ማውጫ ፋብሪካም በሶማሌ ክልል መጠናቀቁን ገልጸው አገሪቷ ከጥቂት ወራት በኋላ የጋዝ ምርት ታቀርባለች ብለው "ሰርቶ አዳሪ እንጂ አውርቶ አዳሪ አለመሆናችንን በማሳየት እንቀጥላለን" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ 5.1 ቢሊዮን ለማሳካት በዚህ ዓመት አቅዳ የነበረ ቢሆንም ከታሰበው በላይ 8.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል ብለዋል።
በአጠቃላይ የአገሪቱ የውጪ ገቢ 32 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ የገለጹት ዐቢይ ይህም ከሬሚታንስ 7 ቢሊዮን ዶላር፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ከአገልግሎት 8.3 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው ዓመት አገሪቷ ከአገርም ሆነ ከውጭ በአጠቃላይ 900 ቢሊዮን ብር ስታስገባ አጠቃላይ ወጪዋ ደግሞ 1.2 ትሪሊየን እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 300 ሚሊዮን ብር ልዩነት አለው ብለዋል።
ዐቢይ 46 ሺህ የሚጠጉ የግብር ተመዝጋቢዎች ግብር እየከፈሉ እንዳልሆነ እንዲሁም ንግድ ፈቃድ ከወሰዱት መካከል ግብር እየከፈሉ ያሉት 37 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ብለዋል።
በግብር ላይ የሚታየውን ክፍተት ለማስተካከል ሪፎርም እየተደረገ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አከፋፈሉን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱ ያለባትን ዕዳ በተመለከተ በዘንድሮው ዓመት 92 ቢሊዮን ብር መከፈሉን ጠቅሰዋል።
በዛሬው ውሎ ከበርካታ አባላት ለተነሰው የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ዓመቱን ሙሉ ብድር ሳይወሰድ ዓመቱን ማጠናቀቁ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
በተጨማሪም የዋጋ ግሽበቱ በዝቅተኛ ገቢ በሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳያሳድር መንግሥታቸው 350 ቢሊዮን ዶላር ድጎማ አድርጓል ብለዋል። ሆኖም የዋጋ ግሽበቱ ሁለት አሃዝ መሆኑም በዚህ የፓርላማ ውሎ ተገልጿል።