የመካከለኛው ምሥራቅ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ እና በቀጣናው እያካሄዱ ያሉት ሰሞነኛ ጉብኝት

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረት ከመቼውም በላይ በተካረረበት እንዲሁም በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ዋነኛ መነጋገሪያ በሆነበት ወቅት የአፍሪካ ቀንድ እና የአረብ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝቶች ተበራክተዋል።

ግብፅ እና ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተፋጠጡበት እንዲሁም ቀጣናዊ የኃይል አሰላለፍን የሚለውጡ ክስተቶች የበዙበት ወቅት እንደመሆኑ በአፍሪካ ቀንድ እና በአረብ አገራት የሚደረጉ ጉብኝቶች ከዲፕሎማሲያዊ ትስስር የዘለለ አንድምታ ሊኖራቸው ይችላል።

ለመሆኑ የየትኞቹ አገራት ባለሥልጣናት ወደ የትኞቹ አገራት ተጓዙ? በባለሥልጣናት መካከል ስለተደረጉ ውይይቶችስ ምን ተባለ?

ትናንት ረቡዕ ኢትዮጵያ የገቡት የሳዑዲ አረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሁለትዮሽ እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጿል።

የውይይታቸው ዝርዝር ይዘት ይፋ ባይደረግም "በቁልፍ ዘርፎች ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር" እንዲሁም "የሁለቱም አገራት ፍላጎት በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መተባበር" ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስታውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘው ከልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

ከሳዑዲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ጋር በተደረገው ውይይት "ሁለቱ አገራት የአፍሪካ ቀንድን ሰላም እና መረጋጋትን ለማስጠበቅ" በጋራ ለመሥራት እንደተስማሙ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ስለ ቀጣናዊ ደኅንነት እንዲሁም የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብት ትስስር መወያየታቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን በቀጣይ ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንደሚጓዙ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ኤርዶዋን በአገራቸው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ ባለፈው ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ እና ግብፅ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣዩ ሳምንት የሚኖረው የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉዟቸውም "በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሰላምን የማስፈን" ዓላማ እንዳነገበ የአናዶሉ ዘገባ ይጠቁማል።

ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባበቢያ ሰነድ በመፈራረሟ በሁለቱ አገራት መካከል ተፈጥሮ የነበረው መቃቃር በቱርክ ጣልቃ ገብነት መርገቡ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያም የሶማሊያም ወዳጅ የሆነችው ቱርክ ተከታታይ ድርድሮች በማዘጋጀት ሁለቱን አገራት ለማቀራረብ ሞክራለች።

ባለፉት ሳምንታት የተካሄዱ ቀጣናዊ ጉብኝቶችን ስንመለከት የሶማሊያ እና የግብፅ ይጠቀሳል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታሕ አል ሲሲ ካይሮ ውስጥ ባደረጉት ውይይት ያላቸውን "የደኅንነት ትብብር ለማጠናከር" መስማማታቸው ተዘግቧል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት፤ ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "የሶማሊያን አንድነት የሚጋፋ የትኛውንም ተግባር በጋራ እንቃወማለን" ብለዋል።

ግብፅ በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ሥር ወታደሮቿን ለመላክ በያዘችው ዕቅድ መሠረት ተግባራዊ እንደምታደርግ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ተናግረዋል።

ረቡዕ ዕለት ግብፅ በሶማሊያ ያሰማራችው ሠራዊት ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ያካተተ ወታደራዊ ትዕይንት ሲያሳይ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና ግብፅ መከላከያ ሚኒስትር ተገኝተዋል።

ሶማሊያ የግዛቷ አካል እንደሆነች ለምትመለከታት ሶማሊላንድ እስራኤል የአገርነት ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ ካይሮ እና ሞቃዲሾ የጋራ አቋም ይዘው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በሌላ በኩል የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ "ሶማሊላንድ ከጋዛ የሚፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን ለማስፈር እና ለእስራኤል የጦር ሰፈር ለመስጠት ተስማምታለች" ማለታቸውን ሶማሊላንድ አስተባብላለች።

እስራኤል ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አገር ናት። ዕውቅናውን ከሰጠች ከጥቂት ቀናት በኋላ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሳር በሐርጌሳ፣ ሶማሊላንድ ይፋዊ ጉብኝት አካሂደዋል።

ሶማሊላንድ ከሶማሊያ ተነጥላ አገር መሆኗን ካወጀች በኋላ በከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣን ደረጃ የተካሄደ ቀዳሚው ጉዞ መሆኑን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዱራሕማን ሞሐመድ አብዱላሒ ወደ እስራኤል ይፋዊ ጉብኝት ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ዘገባዎችም ወጥተዋል።

ያለፈው ጥር ላይ የሶማሊያ መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተደረጉ ሁሉም የሁለትዮሽ ስምምነቶች እንዲቋረጡ መወሰኑን አይዘነጋም።

ውሳኔው ከባሕረ ሰላጤዋ አገር ጋር የተደረጉ "የወደብ ሥራዎችን፣ የመንግሥት ተቋማትን፣ እንዲሁም የፀጥታ እና የመከላከያ ትብብርን" እንደሚመለከት ተገልጿል።

ይህንን ተከትሎም፤ ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ እና ከፊል ራስ ገዟ ጁባላንድ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተፈጸሙ የወደብ ስምምነቶችን ለማቋረጥ መወሰኑን ውድቅ አድርገዋል።

ከሁለት ቀናት በፊት ሶማሊያ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር "ወታደራዊ ስምምነት" እንደተፈራረመች ተገልጿል።

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አሕመድ ሞሊም ፊቂ ከሳዑዲው አቻቸው ልዑል ካሊድ ቢን ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝ ጋር በሪያድ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

ሶማሊያ ከሳዑዲ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ላይ ከመድረሷ ከሦስት ሳምንታት በፊት ከኳታር ጋርም ተመሳሳይ ስምምነት መፈረሟ አይዘነጋም።

ከሰሞኑ የተካሄደው ሌላኛው ጉብኝት የግብፅ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ወደተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረጉት ነው።

አል-ሲሲ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼኽ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል ናሕያን በአቡ ዳቢ አግኝተዋል።

ሁለቱ መሪዎች አቡዳቢ ውስጥ በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ውጥረት እንዲሁም በፍልስጤም እና በእስራኤል ጉዳይ ላይ መወያየታቸው ተዘግቧል።

የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ መሪዎቹ "ቀጣናዊ መረጋጋት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ማክበር ላይ የሚመሠረት ነው" ብለዋል።

በቀጣናቸው ያለው ውጥረት የሚባባስ ከሆነ ሁሉም አገራት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም አሳስበዋል።

የግብፁ ፕሬዝዳንት ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከመሄዳቸው በፊት ከቱርክ እና ከሶማሊያ አቻዎቻቸው ጋር ውይይት አድርገዋል።

በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ከተጓዙ የምዕራባውያን አገራት ባለሥልጣናት መካከል የዩናይትድ ኪንግደም የኮመንዌልዝ፣ ልማት ጉዳዮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር ይገኙበታል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ የሚኒስትሯ ጉብኝት እየጨመረ የመጣውን የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች ቁጥር ለመግታት በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ያተኮረ ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ክርስቶፈር ላንዳው እና የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪንም ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር "ስለ ቀጣናዊ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች" መምከራቸው ይታወሳል።

በሌላ በኩል፤ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ 2018 ዓ. ም. ባሉት ወራት ውስጥ ሦስት ይፋዊ የሥራ ጉብኝቶች አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቱ ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ተጉዘዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በተደጋጋሚ ወደ ግብፅ ከማቅናታቸው በተጨማሪ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲም ወደ አሥመራ ሄደው ሶማሊያን የጨመረ የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ ትብብር መመሥረታቸው ይታወሳል።

ሌላኛውን ጉብኝታቸው ያደረጉት በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው ሱዳን፤ የጋበዟቸውም የሱዳን ጦር አዛዥ ጄነራል አብደል ፋታሕ አል ቡርሐን መሆናቸው ተዘግቧል።

ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያም የኤርትራም ወዳጅ ወደሆነችው ሳዑዲ አረቢያም መጓዛቸው አይዘነጋም።