በአፍጋኒስታን ሦስት ሴቶችን ጨምሮ በርካቶች ሕዝብ በተሰበሰበበት ስታዲየም በግርፋት ተቀጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአፍጋኒስታን ሦስት ሴቶችን ጨምሮ 12 ሰዎች በእግር ኳስ ስታዲየም ውስጥ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች በተሰበሰቡበት በግርፋት ተቀጥተዋል።
በግርፋት የተቀጡት ሰዎች ዝሙት፣ ሌብነት እና የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት መፈጸምን ጨምሮ ሌሎች “ሥነ ምግባርን የሚጥሱ ወንጀሎች” ላይ በመሳተፈቸው እንደሆነ የታሊባን ባለሥልጠናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስላማዊ መሠረት ያለው ታሊባን መሰል ቅጣቶችን ሲፈጽም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ይህ የታሊባን እርምጃ እንደ እወሮፓውያኑ በ1990ዎቹ ሲተገብራቸው ወደነበራቸው ጠንካራ ቅጣቶች ዳግም እየተመለሰ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው ተብሏል።
ግርፋቱ በተፈጸመባት በምሥራቃዊ የአፍጋኒስታን ክፍል የምትገኘው የሎጋር ግዛት ባለው የታሊባን አስተዳደር ቃል አቀባይ የሆኑት ኦማር ማንሱር ሙጃሂዲ ከቅጣቱ በኋላ ሦስቱ ሴቶች መለቀቃቸውን ገልጸዋል።
ቅጣቱ ከተፈጸመባቸው ወነወዶች መካከል የተወሰኑት ደግሞ ወደ እስር ቤት መግባታቸውን ተናግረዋል። ወደ እስር የተመለሱት ምን ያህሉ እንደሆኑ ግን አልተጠቀሰም።
ቃጣቱን የተቀበሉት ሰዎች ከ21 እስከ 39 ጊዜ ለሚሆን ጊዜ የተገረፉ ሲሆን፣ ሌላ የታሊባን ባለሥልጣን ከፍተኛው የግርፋት መጠን 39 እንደሆነ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ በምትገኘው ታካር በተባለው ግዛት 19 ሰዎች በግርፋት መቀጣታቸውን ሪፖርቶች አመልክተዋል።
በሎጋር ግዛት ይህ ቅጣት ከመፈጸሙ ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ የታሊባን ከፍተኛ መሪ ሂባቱላ አኩንዳዛ፣ የተወሰኑ የወንጀል ድርጊቶችን የሚመለከቱ ዳኞች ውሳኔ ሲሰጡ ቡደኑ ከሚመራበት ጥብቅ እስላማዊ የሸሪያ ሕግን መሰረት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።
ምንም እንኳን በታሊባን በግለጽ ባይጠቀስም የዚህም እስላማዊ ሕግ ትርጓሜ በሕዝብ ፊት ሰዎችን መግደልን፣ የሰውነት አካልን መቁረጥን እና በድንጋይ መወገርን የሚያጠቃልል ነው።
ከፍተኛ መሪው የሰጡት ትዕዛዝ ታሊባን ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን ከተመለሰ በኋላ ጥብቅ ሃይማኖታዊ ቅጣቶችን እና ሥርዓቲቹን እንደሚያላላ ቢገልጽም እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች ግን በተቃራኒው ሆነዋል።
በዚህም መሠረት ቅጣቶች በሃይማኖታዊው ሕግ እንዲሆኑ እንዲሁም ሴቶች ትምህርትን ጨምሮ ከተለያዩ ተግባራት እንዲታገዱ አድርጓል።
ታሊባን እንደ አውሮፓውያኑ ከ1996 እስከ 2001 አፍጋኒስታንን በስተዳደረበት ወቅት በካቡል በሚገኘው ስታዲየም ሰዎችን በሕዝብ ፊት በመግረፍ እና በመግደል ተደጋጋሚ ውግዘት ይደርስበት ነበር።












