የጊኒ ቢሳዎን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ወታደራዊ መሪ ተሾሙ

ጄኔራል ሆርታ ንታም የሽግግር ፕሬዝዳንት ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

በጊኒ ቢሳው የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ጄኔራል ሆርታ ንታም ለአንድ ዓመት የሽግግር ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መሐላ ፈጸሙ። አጭር ነበር የተባለለት ስነ ስረዓት በጦር ኃይሉ ዋና መሥሪያ ቤት በዝግ መካሄዱ ታውቋል።

እስከ መፈንቅለ መንግሥቱ ድረስ የፕሬዚዳንቱ የጥበቃ ኃላፊ የነበሩት ንታም፣ በቃለ መሐላውም ሆነ ከሌሎች የጦር አመራሮች ጋር በነበራቸው የፎቶ ስነስርዓት ወቅት ፈገግ ሲሉ አልታየም።

በጊኒ ቢሳው የሚገኙ አንዳንድ የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች ግን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ በቅርቡ በተደረገው ምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ በጦሩ የታገዘ "መፈንቅለ መንግሥት" በራሳቸው ላይ እያቀነባበሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።

"ይህም የታቀደው የምርጫ ውጤት እንዳይወጣ ለማድረግ ያለመ ነው" ሲል የሲቪል ማኅበረሰቦች ጥምረት የሆነው ፖፑላር ፍሮንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የምርጫ ተቀናቃኙ ፈርናንዶ ዲያስም ይህንን ክስ አስተጋብተዋል።

ኢምባሎ ለክሶቹ ምላሽ አልሰጡም።

በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ በርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎችን እንዳሸነፉ ተናግረዋል። ተቺዎቻው ግን ተቃውሞዎችን ለማፈን ቀውስ እየፈጠሩ ነው ሲሉ ደጋግመው ከሰዋቸዋል።

ጦሩ የምርጫ ሂደቱን አስቁሞ ይጠበቅ የነበረውን የእሑዱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት እንዳይለቀቅ አግዷል።

ስማቸው ያልተገለጸ ወታደራዊ ምንጭ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ኢምባሎ በሠራዊቱ ዋና መሥሪያ ቤት "በጥሩ ሁኔታ መያዛቸውን" ተናግረዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ "ፕሬዝዳንት ኢምባሎ እና የታሰሩ ባለሥልጣናትን በአስቸኳይ ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ" ጠይቀዋል።

ለጊኒ ቢሳው መሪዎችም "የምርጫ ሂደት ማክበር አስፈላጊ መሆኑን" አስታውሰዋል።

በሴኔጋል እና በጊኒ መካከል የምትገኘው የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር፤ እአአ በ1974 ከፖርቹጋል ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ጦሩ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነባት እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ማዕከል በመባል ትታወቃለች።

ጊኒ ቢሳዎ ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት ቢያንስ ዘጠኝ መፈንቅለ መንግሥቶችን ወይም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች አስተናግዳለች።

መፈንቅለ መንግስቱ የምርጫውን ውጤት ለማደናቀፍ በፕዝዳንት ኢምባሎ የተካሄደ ነው ስለመባሉ ምንም አላሉም

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ረቡዕ ዕለት የጦር መኮንኖች አገሪቱን መቆጣጠር መቻላቸውን አሳውቀዋል። ቀደም ሲል የመንግሥት ምንጮች ኢምባሎ መታሰራቸውን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በዋና ከተማዋ ቢሳው የተኩስ ድምፅ ቢሰማም በተኩሱ ማን እንደተሳተፈ ወይም ስለደረሰው ጉዳት ግልጽ አይደለም።

የጦር መኮንኖቹ በመንግሥት ቴሌቪዥን ጣብያ ቀርበው የምርጫ ሂደቱን እንዳስቆሙ ተናግረዋል።

አገሪቱን ለማተራመስ "በታዋቂ የዕፅ አዘዋዋሪዎች" ድጋፍ ያላቸው ስማቸውን ያልጠቀሷቸውን ፖለቲከኞች ሴራ ለማክሸፍ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የአገሪቱ ድንበር መዝጋቱን እና የሌሊት የሰዓት እላፊ ገደብ እንዳወጁ ተናግረዋል።

የምርጫው ውጤት ሐሙስ ዕለት ይገለጻል ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ሲሆን ኤምባሎ እና ዋነኛ ተፎካካሪያቸው ዲያስ ማሸነፋቸውን ሲገልጹ ነበር።

ዲያስ ከምርጫ ታግደው በነበሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶሚንጎስ ፔሬራ ድጋፍ አግኝተዋል።

ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ኢምባሎ ለፍራንስ 24 በስልክ ጥሪ በሰጡት ቃለ መጠይቅ "ከሥልጣን ተባርሪያለሁ" ብለዋል።

የመንግሥት ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዲያስ፣ ፔሬራ እና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቦቼ ካንዴም ታስረዋል።

የጦር አዛዡን ጄኔራል ቢያጌ ና ንታን እና ምክትላቸውን ጄኔራል ማማዱ ቱሬንም በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ኅብረት እና የምዕራብ አፍሪካው ኢኮዋስ የምርጫ ታዛቢዎች "በጦር ኃይሎች መፈንቅለ መንግሥት መታወጁን በተመለከተ ጥልቅ ስጋት እንደገባቸው" ገልጸዋል።

አገሪቱ "ሥርዓቱን የጠበቀ እና ሰላማዊ" ሂደት እንደሆነ ከገለጸችው ሂደት በኋላ የምርጫውን ውጤት ይፋ ለማድረግ ተዘጋጅታ ነበር ብለዋል።

የቀድሞው የአገሪቱ ቅኝ ገዥ ፖርቹጋል ሥልጣን ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመለስ ጥሪ አቅርባለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯም "[የመፈንቅለ መንግስቱ] ተሳታፊዎች ሁሉ ከማንኛውም የተቋማዊ ወይም የሲቪክ ጥቃት እንዲቆጠቡ" አሳስበዋል።

የ53 ዓመቱ ኢምባሎ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ተከታታይ ዘመን በስልጣን የቆዩ የአገሪቱ ብቸኛ ፕሬዝዳንት በመሆን ታሪክ መስራት ፈልገው ነበር።